ኢትዮጵያ የፈረመችው ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ስምምነት እንዲሁም የዓለም ንግድ ድርጅት አባላት ሒደትን መነሻ በማድረግ ብሎም ባለሀብቶች በየዘርፋቸው የመወዳደር አቅም እንዲኖራቸው ለማስቻል እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ያስታወቀው፣ ሐሙስ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው 15ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ዘንድሮ በምክር ቤቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሥራዎች መካከል የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ኢትዮጵያ በመፈረሟ ምክንያት የሚመጡ የውጭ ተወዳዳሪዎችን ለመቋቋም ከወዲሁ ባለሀብቶችን የማብቃት ሥራና ተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡
ከአኅጉር አቀፍ የንግድ ስምምነቱ በተጨማሪ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን መንግሥት እንደ አዲስ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ፣ ገበያው ለውጭ ተወዳዳሪዎች ከተከፈተ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ትልቅ ፈተና ስለሚጠብቀው፣ በዚህ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ አሁን ባለው አቅምና ቁመና የሚመጣውን ውድድር ሊቋቋም ስለማይችል፣ አቅሙን በምን መንገድ መገንባት እንደሚያስፈልግ ምክር ቤቱ ይገልጻል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥም ይህንኑ የሚያጠናክር ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ንግድ ምክር ቤቱ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ መጫወት የሚጠበቅበትን ጉልህ ሚና ለማጉላት መንቀሳቀስ የምክር ቤቱ አጀንዳ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ በቅርቡ ለመንግሥት እንደሚያቀርበው ካስታወቀውና በኢኮኖሚው መስክ የግሉ ዘርፍ ስለሚኖረው ሚና አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ዝግጅት እያካሄደ እንደሚገኝም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
ወ/ሮ መሰንበት በምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ምክር ቤቱ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና መሰናክል የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት መከተል አለበት ያላቸውን፣ የግሉን ዘርፍ ማዕከል ያደረጉ የአምስት ዓመት የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ለመንግሥት ለማቅረብ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
በግሉ ዘርፍ ላይ የተጋረጡ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመቀነስ ብሎም ጠንካራና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ዕውን ለማድረግ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ ነጋዴዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቡ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ከመንግሥት ጋር በሚደረጉ የምክክር መድረኮች ላይ ሚዛናዊና ተዓማኒነት ያላቸው የፖሊሲ አማራጮችን ለማቅረብ ይረዳ ዘንድ ምክር ቤቱ በጥናት የተደገፈ ሁሉን አቀፍ የፖሊሲ አድቮኬሲ ሥራ እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመወጣት የሚያስችሉ መፍትሔ አመላካች ሐሳቦች በመለየት የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ እንዲኖር ግፊት ማድረግ አጀንዳው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ስለመሆኑም ተመልክቷል፡፡ ለዚህም የ2025 ፖሊሲ ፕላን ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት ማቅረብና ከዚህ አንፃር ሰፊ አድቮኬሲ ሥራዎች እንደሚሠሩም የንግድ ምክር ቤቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡
የግሉን ዘርፍ ማዕከል ያደረገው የአምስት ዓመቱ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ፣ የመጀመሪያውንና ዋናውን ምዕራፍ ጨምሮ፣ ወሳኝ የተባሉ ስምንት ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችና 42 የፖሊሲ ትልመ ሐሳቦችን በመለየት የተካተቱበት ሥራ እንደተጠናቀቀ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፖሊሲ ትልመ ሐሳቦችን የመተንተን፣ ወሳኝ ጉዳዮችን በቅደም ተከተል የማስቀመጥና የውጤት መለኪያዎችና አመላካቾችን የማስቀመጥ ሥራዎች በውጭ አማካሪዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የፖሊሲ ጥናቱን ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የንግዱን ኅብረተሰብ ለማወያየት እንደሚጠራ ያስታወቀው ምክር ቤቱ፣ በሚቀርቡለት ግብረ መልሶች አዳብሮ የፖሊሲ ሰነዱን ለመንግሥት ያቀርባል ተብሏል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው ከቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ እስካሁን ባለው ሒደት ንግድ ምክር ቤቱ የግል ዘርፉን ሚና ለማጉላት ያከናወናቸው ሥራዎች ቢኖሩም፣ በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ መንግሥት የግሉን ዘርፍ ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ላይ ዝቅተኛ አሳታፊነት የነበረበትን ሥርዓት ሲያራምድ እንደቆየ አመልክቷል፡፡
ምክር ቤቱ የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ለማገዝ፣ በመንግሥት የሚዘጋጁ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ማሻሻያዎች ለግሉ ዘርፍ ምቹ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ከባቢ ሁኔታ እንዲፈጠሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያጋጥሙት ችግሮች እንዲፈቱ፣ የግሉ ዘርፍ ዕድገትን ለማጎልበትና በልማት ሥራዎች ላይ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ ምክር ቤቱ ለጉባዔው በሪፖርት አሰምቷል፡፡
ዓምና ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በንግድ ምክር ቤቱ ሥር የሚገኘው የንግድ ጉዳዮች የግልግል ተቋም፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ሲያጋጥሙት በነበሩ ችግሮች ላይ ላቀረባቸው አቤቱታዎች የሰጣቸው መፍትሔዎች ተጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የግልግል ተቋሙ በ2011 ዓ.ም. 28 ጉዳዮች በግልግል፣ ስድስት ጉዳዮች በድርድር እንዲፈቱ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ሌላው ዓበይት ክንዋኔ ተብለው በንግድ ምክር ቤቱ ከቀረቡት ውስጥ፣ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ያደረገው እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ ለሕንፃ ግንባታ የሚውል ገቢ የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩንና በተያዘው በጀት ዓመትም ግንባታ እንደሚያስጀምር አስታውቋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሦስት የዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን እንዳካሄደ፣ ከዚህም ስድስት ሚሊዮን ብር ገቢ እንዳሰባሰበ ገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ የንግዱን ማኅበረሰብ መብትና ጥቅሞች ለማስጠበቅ የአገሪቱን ወቅታዊ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የፋይናንስ፣ እንዲሁም በተመድ ዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም ሒደት ላይ ዘርፉ የሚጫወታቸውን ሚናዎችና ያሉትን ዕድሎች ብሎም የሚገጥሙትን ችግሮች ሊያመለክቱ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችም እንዲዘጋጁ ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡ ለኤግዚቢሽንና ተጓዳኝ ሥራዎች የተሟላ አገልግሎት በመስጠት 76.2 ሚሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 98 በመቶ ማሳካት ስለመቻሉ ተመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤቶች የሥራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ እንደ አንድ ተግዳሮት የሚታየውና በብዙዎች ንግድ ምክር ቤቶች ከዓመታዊ የአባልነት መዋጮ ወቅቱን ጠብቆ አለመክፈል ነው፡፡
ከአባላቱ መዋጮ በማሰባሰብ ቀዳሚ መሆኑ የሚነገርለት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትም ቢሆን የአባላት መዋጮን በዕቅዱ ልክ ማሰባሰብ እንደቻለ በሰሞኑ ሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡
የአባላት ጉዳዮችን በተመለከተ በሰፈረው መረጃ መረዳት እንደሚቻለውም በበጀት በድምሩ 3,758 አባላት ወቅታዊ የአባልነት ክፍያ እንዲከፍሉ በማድረግ 6.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረግ መቻሉን ጠቅሷል፡፡ ይህ ክንውን ግን ከዕቅድ አንፃር ሲታይ 62 በመቶ ነው፡፡
በ2011 በጀት ዓመት ከአዳዲስና ከነባር አባላት 3.1 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ማሰባሰብ የተቻለው 1.4 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ በድምሩ ከአዳዲስና ከነባር አባላት 13.5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 7.8 ሚሊዮን የሰበሰበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከአባላት መሰብሰብ የቻለው 58 በመቶ ብቻ በመሆኑ አባላት መዋጮ ረገድ ያለው ክፍተት ያሳያል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት የተዘመገቡ 15 ሺሕ አባላት እንዳሉት ይታመናል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ እንዳወቅ አብቴ (ኢንጂነር) በበኩላቸው የንግዱ ማኅበረሰብና ዘርፎች ያልተፈቱላቸው በርካታ ማነቆዎች እንዳሉበት ጠቅሰዋል፡፡ በዘርፉ ዕድገት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ አልቀረም ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ የንግድ መሠረተ ልማት፣ የንግድ ቦታ አቅርቦት፣ የንግድና የታክስ ሥርዓቱና ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የመሳሰሉት ላይ የንግድ ኅብረተሰብ በርካታ ያልተመለሱለት ጥያቄዎችና ተግዳሮት ናቸው በማለት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ተባብሮ መሥራት ግድ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አሉ የተባሉትን ተግዳሮቶችና ችግሮች የሚፈቱና የዘርፉን አዳጊ ፍላጎቶች የሚሟሉት በመንግሥት ብቻ ያለመሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው ‹‹መንግሥት የግሉ ዘርፍ በጋራ በመመካከር በመነጋገርና አጋርነትና ትብብር በመፍጠር አብረን ሥንሠራ ብቻ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡