Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አባት እንጂ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

‹‹ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አባት እንጂ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በዘንድሮ በጀት ዓመት መንግሥት ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባቸዋል ያሏቸው ዝርዝር ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማብራራትና የመንግሥታቸውን አቋም ለመግለጽ በምክር ቤቱ ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢሕአዴግ ውህደትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ከኢሕአዴግ ትቀድማለች ብለዋል፡፡

የኢሕአዴግ ውህደትን በተመለከተ በአባላቱ ውስጥ እየተሰማ ያለውን ቅራኔ ያጣጣሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አባወራ ሲሞት ልጆች ይበተናሉ እንደሚባለው፣ ኢሕአዴግ ከተዋሀደ ወይም ከተበተነ አገር ይፈርሳል ማለት ከድንቁርና የሚመነጭ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኢሕአዴግ ውህደትን በተመለከተ፣ ‹‹የእኛ ስምምነት ካለበት ሰላም ያመጣል፣ እኛ ከሌለን ግን ኢትዮጵያ የለችም ትፈርሳለች ማለት ትክክል አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል።

‹‹ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አባት እንጂ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ አንድ ቢሆንም ባይሆንም ኢትዮጵያ ትቀጥላለች፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ምርጫን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የዘንድሮን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ፈተና ቢሆንም፣ የዘንድሮውም ሆነ ከአምስት ዓመት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ችግር አልባ ሊሆን እንደማይችል በመጥቀስ ምርጫው መካሄድ ባለበት ወቅት መከናወን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በመጪው ግንቦት ወር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡ አንድ የምክር ቤቱ አባል፣ ምርጫውን ለማካሄድ አስቸጋሪ የሚያደርጉ ነባራዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ከዘረዘሩ በኋላ፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች፣ ኢሕአዴግን በውህደትና በመበተን ሰንገው የያዙ ውስጣዊ ሁኔታዎች፣ ምርጫና የፓርቲዎች ምዝገባን በተመለከተ በቅርቡ በወጣው አዋጅ ላይ ፓርቲዎች ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑ ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

በመሆኑም አሁን ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ምርጫውን በዚህ ዓመት ማድረግ አዋጭ ነው ወይ ሲሉ የምክር ቤት አባሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹በዘንድሮውም ሆነ በሚቀጥለው ችግር አልባ፣ ተግዳሮት የሌለው ምርጫ ማድረግ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ያሉበት ምክንያትም ዴሞክራሲ ልምምድ የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት መጋቢት 2010 ዓ.ም. በኋላ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በተካሄዱ ሕዝባዊ መድረኮች፣ “የእኔ የመጨረሻ ግብ ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ማድረግ ነው፤” ሲሉ በሥልጣን ቆይታቸው ትልቅ ትኩረት የሚያደርጉበት ጉዳይ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገልጹ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአገሪቱ የሚስተዋለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ እንዳልሆነ እየተገነዘቡ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ባመረጋጋት የታጀበ አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የዘንድሮ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት እምነት ይዘዋል፡፡

የመጨረሻ ግባቸው የዘንድሮ ምርጫን ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክሲያዊ እንዲሁም ተዓማኒ ማድረግ ስለመሆኑ ሲገልጹ ቢቆዩ፣ አይደለም የዘንድውን ምርጫ ከአምስት ዓመት በኋላ የሚመጣውን ምርጫም ያለ ችግርና ፈተና ማካሄድ ይቻላል ብለው እንደማያምኑ ለመጀመርያ ጊዜ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ዘንድሮ ፈተና አልባ ምርጫ ማድረግ ባይቻልም፣ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻልና ለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያደረገ ያለው የተሻለ ዝግጅት፣ የሲቪክ ማኅበራትና የመገናኛ ብዙኃን በአንፃራዊነት የተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ “ምክንያት እየፈለጉ አሁን እንችልም ብለን የዘንድሮ ምርጫን ብናራዝም ብዙ ችግር አለው። የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ በሙሉ ልብ መሥራት ይሻላል፤” ብለዋል፡፡

በዚህ አስተያየታቸው በሕዝብ ተመርጦ ወደ ሥልጣን የሚመጣ ቅቡል መንግሥት አገሪቱን ቢያስተዳድር በተሻለ ልበ ሙሉነት መምራት እንደሚቻል ቅድሚያ ትኩረት መስጠታቸውን ያስገነዝባል፡፡

 ነገር ግን የዘንድሮ ምርጫ መራዘም የለበትም ብለው አስረግጠው አልተናገሩም፡፡ ከንግግራቸው መረዳት የሚቻው ምርጫው መራዘም የለበትም የሚለው የግልና የሚመሩት ፓርቲ ኢሕአዴግ እምነት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምርጫን የማራዘም ሥልጣን የሌሎች ባለድርሻዎች ጭምር መሆኑን፣ የመጨረሻውን ውሳኔ መስጠት የሚችለውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 “አሁን ያለው ምክር ቤት ከክልል ምክር ቤቶች ጋር በመሆን የሥልጣን ዘመኑን ማራዘም ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሞራል ሊቀጥል አይችልም፡፡ ከዚህ ይልቅ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ እንደ አዲስ መወከል ይሻላል፤” ብለዋል።

ምርጫውን አስቸጋሪ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብለው ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል፣ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በቅርቡ የፀደቀውን የምርጫ አዋጅ ድንጋጌዎች በተመለከተ ጠንካራ ቅሬታ እያቀረቡ መሆናቸውን፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ከውህደት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው አለመግባባትን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከምንጊዜውም በተሻለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገራቸው ገብተውና በአገር ውስጥ ያሉትም ተጠናክረው በነፃነት የመወዳደር ዕድል እንዳገኙ ገልጸው፣ የተሰጠውን ዕድል መጠቀም እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል።

 የምርጫ ሕጉ ለመንግሥት ካቢኔ ሳይቀርብ ምርጫ ቦርድ ባለድርሻ አካላትን አወያይቶ በቀጥታ ለፓርላማ ልኮ ማፅደቁን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ፓርቲዎች የምርጫ ሕጉ ያስቀመጣቸውን መሥፈርቶች በተመለከተ የሚያነሱት ቅሬታ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

“እነዚህ ፓርቲዎች 30 እና 40 ሆነው ምርጫን እንዴት ማሸነፍ ይችላሉ? ምርጫን የማሸነፍ ዕድል ቢያገኙስ እንዴት አገርን መምራት ይችላሉ?” ሲሉ አገር ለመምራት ወደ አንድ መሰባሰብ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭት ያዘሉ መካረሮችን በተለይም በትግራይ ክልልና በአማራ ክልል፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ከቅማንት ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ፣ ከሰሞኑ ደግሞ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከቅማንት ማኅበረሰብ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልልን የሚመራው መንግሥት የቅማንት ብሔረሰብ ላነሳው የማንነትና ራስን የማስተዳር ጥያቄ በአብዛኛው ዕልባት መስጠቱን፣ ነገር ግን በሦስት ቀሌዎች ላይ ያለ ጥያቄ መፍትሔ አለማግኘቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የተነሳ አንድም ሰው መሞት እንደሌለበትና ሁለቱም ወገኖች ተቀራርበው ሊፈቱት እንደሚገባ ገልጸዋል። በዚህ አካባቢ ሌሎች ኃይሎች ጣልቃ እየገቡ ሊሆን ቢችል እንኳን፣ አሁን በአካባቢው ያለውን ግጭት በሦስተኛ ወገን ወይም በውጭ አካል ማሳበብ ችግሩን ለመፍታት እንደማያስችል ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በአማራና በቅማንት ብቻ ሳይሆን በአፋርና በሶማሌ ኢሳ ጎሳ መካከል ለተነሳው ግጭት መፍትሔ ለማምጣት እየሠራ ነው ብለዋል።

‹‹ኃላፊነት ላለመውሰድ ከውጭ የሚመጣ አካል ነው የሚያጠቃን የሚሉ ቅራኔዎች ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ምክንያት በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ሰሞኑን በተከሰተ ግጭት ላይም አጋጥሟል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ የተነሳም መንግሥት በሥፍራው የነበረውን የመከላከያ ኃይል አስወጥቶ ልዩ ኃይል እንዳስገባ ተመሳሳይ ዕርምጃም በአማራና በቅማንት መካከል የሚስተዋለውን ግጭት ለመፍታተት ተግባራዊ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በየአካባቢው የሚስተዋለውን መንገድ የመዝጋትና መስል ተግባሮች በተመለከተ በሰጡት አስተያየትም፣ ‹‹መንገድ መዝጋት ኋላ ቀርና የብሽሽቅ ፖለቲካ ነው፤›› በማለት መቆም አለበት ብለዋል፡፡

በክልሎች መካከል ጦርነት የሚመስል ዝግጅትና ሥጋትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ በክልሎች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጦርነትን እንደ መፍትሔ የሚያምኑ አካላት መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ‹‹እነዚህ አካላት አሁንም የፓርቲ አመራር ሆነው ነው ያሉት፡፡ የሚሞተው ግን የደሃው ልጅ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡም በክላሽ ዘላቂ ድል አይመጣም ብሎ በቃ ሊል ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

 ይህንን ጉዳይ ለማብራራት የትግራይ ክልልን ለአብነት ያነሱ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ያሉ አመራሮች የሕዝቡን ችግሮች መፍታት ላይ እንጂ ስለጦርነት አስበው እንደማያውቁና ሕዝቡም ልምድ ስላለው ጦርነት እንደማይፈልግ ገልጸዋል፡፡ በሌሎች ክልሎች ያለው ሁኔታም እንደዚሁ ተመሳሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በክልሎች የሚስተዋል የጦርነት ዝማሬም ሆነ መካረር ሥጋት ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ የተናሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ክልሎች የያዙት ትጥቅ በሌሎች አገሮች ዓይን ሲታይ ግለሰብ ከሚታጠቀው ያነሰ ነው፡፡ ያን ያህል ሥጋት የሚያመጣ ትጥቅ የታጠቀ አካል የለም፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በአንፃራዊነት መሻሻል ቢያሳዩም አሁንም ችግር ያለባቸው መኖራቸውን፣ እነዚህም ሚዲያዎች የዘር ነጋዴዎች መጠቀሚያ ወይም የገንዘብ ነጋዴዎች መሆናቸውን በመግለጽ ሚዲያዎቹን በተመለከተ የብሮድካስት ባለሥልጣን የሚዲያ ነፃነቱን በማይጎዳ መንገድ የማስተካከያ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

 ‹‹የውጭ አገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች ስትፈልጉና ሰላም ሲሆን እዚህ ተጫውታችሁ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት አገር ያላችሁ ሰዎች፣ እኛ ትዕግሥት እያደረግን ያለነው ዓውዱን ለማስፋት ነው፤›› ሲሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።  

‹‹በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላምና ህልውና ላይ ከመጣችሁ አማርኛ ብትናገሩም ኦሮሚኛ ብትናገሩም፣ ዕርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መሆኑን በጥንቃቄ መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...