Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አማራ ባንክ መመሥረቻ ካፒታሉን በማሟላቱ በጥር ወር ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘምዘም ባንክም ለምሥረታ ከሚጠበቅበት በላይ ካፒታል እንዳሟላ ገልጿል

አማራ ባንክ እንዲቋቋም በሕግ ከተፈቀደው ካፒታል በላይ በማሰባሰቡ፣ በመጪው ወር መሥራች ጉባዔውን እንደሚያካሂድና በጥር 2012 ዓ.ም. ሥራ ለመጀመር ማቀዱን አስታወቀ፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኘው የአማራ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ መላኩ ፈንታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአክሲዮን ሽያጭ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ የተሰበሰበው ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህም ባንኩን ለማቋቋም ከሚያስፈልገው ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል በላይ መገኘቱን ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህም ባንኩን ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራ ይጀመራል ብለዋል፡፡ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባንኩን ለማቋቋም የሚያስችል  ካፒታል ማሰባሰብ እንደተቻለ የጠቀሱት አቶ መላኩ፣ የአክሲዮን ሽያጩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሳካል ተብሎ ባይታሰብም፣ በፋይናንስ መስኩ ከነበረው ታሪክ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንክ ለመመሥረት የሚያበቃ ካፒታል ማሰባሰብ የተቻለበት አጋጣሚ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡  

ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የገዙ ባለአክሲዮኖች ቁጥርም ከ15 ሺሕ በላይ መድረሱን ከአቶ መላኩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ምንም እንኳ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን ካፒታል ቢያሰባስብም፣ መሥራች አባል ሆነው ለመካተት የሚፈልጉ ባለድርሻዎች እንዲገቡበት ሲባል የአክሲዮን ሽያጩ እስከ ኅዳር ወር መጨረሻ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡  

በአደራጅ ኮሚቴው ዕቅድ መሠረት ባንኩን ዕውን ለማድረግ የባለአክሲዮኖች መሥራች ጉባዔ በኅዳር 2012 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡ መሥራች ጉባዔው አዳዲስ የቦርድ አመራሮችን በመሰየም፣ የአንድ ወር ዝግጅት ካካሄደ በኋላ፣ በጥር 2012 ዓ.ም. አማራ ባንክ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡

ባንኩ ሥራ ከጀመረ በኋላ እስከ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች 30 ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት ያስታወቁት አቶ መላኩ፣ ለዚህ የሚረዳ ዝግጅት እየተካሄደ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ከአማራ ባንክ ባሻገር በአጭር ጊዜ (አራት ወራት ውስጥ) ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ አክሲዮን በመሸጥ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እየተዘጋጀ የሚገኘው ወለድ አልባው ዘምዘም ባንክም፣ እንደ አማራ ባንክ የሚጠበቅበትን የመመሥረቻ ካፒታል ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማሰባሰብ እንደቻለ ታውቋል፡፡

 አቶ መላኩ በሰጡት ማብራሪያ እስካሁን ከተካሄደው የአክሲዮን ሽያጭ መገንዘብ የተቻለው፣ አብዛኞቹ አክሲዮን ገዥዎች የ15 ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ገዝተዋል፡፡ ይህም ባንኩ አብዛኛውን ማኅበረሰብ አካታች ለማድረግ የያዘውን ውጥን ለማሳካት እንዳስቻለው፣ በተጨማሪም ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሊገዙ የሚችሉ ድርጅቶች፣ የዳያስፖራው ማኅበሰብ አባላት፣ ታዋቂ የንግድ ሰዎችና ሌሎችም አቅሙ ያላቸው ላይ በማተኮር የአክሲዮን ሽያጩን መጠን እስካሁን ከተደሰተበት መጠን በላይ ለማድረስ አማራ ባንክ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች