የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ በማተኮር ለመንቀሳቀስ ከተቋቋሙ ማኅበራት መካከል፣ በቡና ዘርፍ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ሴቶች የዘርፍ ማኅበር ወይም ‹‹ኢትዮጵያን ውመን ኢን ኮፊ›› የተሰኘው ተቋም ይጠቀሳል፡፡ ማኅበሩ በቡና ንግድ ዘርፍ በሕግ አግባብ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት አስቆሯል፡፡
የማኅበሩ ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መሠረት ደስታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከማኅበሩ ዋና ዋና ዓላማዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው፣ ሴቶች በቡና ዘርፍ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ በሕግ ተመዝግቦ መንቀሳቀስ የጀመረው በ2009 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት በተለያዩ መስኮች ቡናን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕዮች ላይ በመሳተፍ ማኅበሩ ራሱንም አባላቱንም ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡
ቡና አምራችና ነጋዴ ሴቶች እርስ በርሳቸው የሚረዳዱበትን መድረክ መፍጠር፣ በወንዶች ጫና ውስጥ በሚገኘው የቡና የምርት ሰንሰለት ውስጥ ሴቶች እንዴት ተጠቃሚ ይሁኑ በሚሉት መስኮች ላይ እንደሚሠራ ያመለከቱት ወ/ሮ መሠረት፣ የማኅበሩ መመሥረት በርካታ ለውጦችን እያስገኘ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ውስጥ የቡና ላኪዎች ማኅበርን የመሳሰሉ ተቋማት ቢኖሩም፣ ሴቶች በአምራችነት፣ በላኪነት በአቀነባባሪነትና በመሳሰሉት መስኮች የሚሳተፉበት ተቋም ግን እምብዛም አልነበረም፡፡ አዲሱ ማኅበር በቡና ወጪ ንግድ መስክ ሴቶችን በማስተሳሰር የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚንቀሳቀስ ማኅበር መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ሊቀመንበሯ ያስረዳሉ፡፡
ቡና የአገሪቱን ሰፊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝና በዓለም መድረክም ሰፊ የግብይት ድርሻ የያዘ እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያም በመስኩ ካላት አቅም አኳያ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት የቦርድ ሊቀመንበሯ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሴቶች ብቻ በተናጠል የተሰባሰቡበት ማኅበር እንዲቋቋም የተፈለገበት ሌላው ዋና ምክንያት በቡና የምርት እሴት ሰንሰለት ውስጥ ሴቶች የላቀ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ በማመላከት ነው፡፡ እንደ ወ/ሮ መሠረት ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ከ60 በመቶ በላይ የቡና ምርት ሥራ በሴቶች የሚከናወን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተጠቃሚነቱ ላይ እነዚህ ሴቶች ብዙም የሉበትም፡፡ ይህንን መለወጥ የማኅበሩ ሚና ወሳኝ ነው ያሉት ወ/ሮ መሠረት፣ በቡና ለቀማና በቡና ጥራት አጠባበቅ ሥራዎች ላይ የሚሳተፉ በርካታ ሴቶች፣ ሥራቸው ትኩረት ተሰጥቶት፣ ሥልጠና አግኝተው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ይህንን ክፍተት የማስተካከል ሥራ ማኅበሩ እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡
‹‹የቡና ላኪዎች ማኅበር ላኪዎችን ብቻ የያዘ ነው፡፡ የአምራቾች ማኅበርም የቡና አብቃዮችን ብቻ ያካተተ ነው፡፡ የእኛ ግን ከሥር ጀምሮ በቡና ዘርፍ የተሠማሩ ሴቶችን ይዞ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ከአብቃይ እስከ ቆይ፣ ከቆይ እስከ ላኪ፣ ከላኪ እስከ ቀማሸ ያሉትን ሁሉ ይዞ መንቀሳቀሱ የተለየ ያደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡ ማኅበሩ በምሥረታው በ22 አባላት ጀምሮ በአሁኑ ወቅት 40 የቡና ላኪዎች፣ አምራቾች፣ ቡና ቆይዎችና የራሳቸው የቡና መደብር ወይም ካፌ ያላቸው አባላትን እንዳካተተ ተጠቅሷል፡፡ አባላቱ የየራሳቸውን ኩባንያዎች የሚያንቀሳቅሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉበት መድረክ መፍጠር ችለዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የቡና ገበያ በትንሹ አሥር ዓውደ ርዕዮች በየዓመቱ ስለሚካሄዱ በእነዚህ መስኮች እየተሳተፉ አባላቱ የተሻለ ገበያ እንዲያገኙና፣ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማገዝ በኩል ማኅበሩ ሚናውን እንደሚጫወት ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስካይ ላይት ሆቴል በተደረገው ምክክር ወቅት ተወስቷል፡፡
የማኅበሩ መመሥረት ለአባላቱ ምን አስገኘላቸው ተብለው የተጠየቁት ወ/ሮ መሠረት፣ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ምላሻቸውን እንዲህ አካፍለዋል፡፡ ‹‹ቡና ሳይንስ እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡ ድርጅቴ ወደ ቡናው ዘርፍ ሲገባና ኤክስፖርት ማድረግ ሲፈልግ ማለፍ ያሉብኝ ሒደቶች ቀላል እንዳልሆኑ የተገነዘብኩት በማኅበሩ በኩል ባገኘሁት ሥልጠና ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ሁሉ ሌሎች አባላትም በቡና ዘርፍ ለደረሱበት ደረጃ ከማኅበሩ ያገኙት የዕውቀትና የሥልጠና ድጋፍ ጥሩ ድጋፍ እንደሆናቸው አስረድተዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የሚጠቀስ፣ በግብርናው መስክ የጥራት አጠባበቅ ሥልጠና ማግኘታቸው ትልቅ ዋጋ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥልጠና ለሴቶች ብቻም ሳይሆን፣ ለአገርም አስተዋጽኦ እንዲያበርክት ታስቦ መዘጋጀቱ ተብራርቷል፡፡
በሥልጠና ረገድ የልዩ ጣዕም ቡናዎች ላይ ያተኮረው ማኅበር ወይም ‹‹ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሴሽን›› ከዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል ጋር በመተባበር ለአባላቱ የቡና ቅምሻ፣ የቡና ንግድ ሥልጠና የልዩ ጣዕም ቡናዎች አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ሲገልጹም፣ ‹‹አባላት ሥልጠና የሚወስዱት በነፃ አይደለም፤›› ያሉት ወ/ሮ መሠረት፣ ሥልጠናውን የወሰዱ አባላት ሌሎችን የማሠልጠን ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ መሠረት የዚህ ጥቅሙ፣ ለአብነት ጥሬ ቡና በመላክ ላይ ብቻ ተመሥርቶ የነበረው ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት ጥሬው ቡና ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብን፣ በዓለም ገበያ ቡና ገዥዎች የሚፈልጉትን ጥራት ያሟላ ቡና ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡ ይህ ከሥልጠናው የተገኘና ለሌሎችም ሴቶች የሚሠራ ትሩፋት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ‹‹አጠቃላይ የቡና የገበያ ሰንሰለትን ማወቅ በመቻሌና በሥልጠና በመታገዜ ዛሬ የተሟላ ላብራቶሪ ያለው የቡና ሱቅ ለመክፈት አስችሎኛል፤›› የሚሉት ወ/ሮ መሠረት፣ ማኅበሩ አባላቱን በመደገፉ ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ማሳያዎችን ያቀርባሉ፡፡
ይህ ዓይነቱ ድጋፍ በመዘርጋቱም ውጤታማና ጥራት ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት የሚችሉ አባላት ማፍራት እንዳስቻለ፣ ከአምራችነትና በጥሬው ከመላክ ባሻገር ቡና ላይ እሴት ጨምሮ አቀነባብሮና አሸጎ መላክ የሚያስችል አቅም እንዲፈጠር ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሒደት ቡና ሳይንስ መሆኑን ጭምር ያሳያል ያሉ የቦርድ ሊቀመንበሯ ወደዚህ ለመድረስ ግን በዕውቀት ላይ የተመሠረቱት የማኅበሩ ሥልጠናዎች ትልቅ ዕገዛ አድርገዋል፡፡
በቡና ለቀማ፣ አጠባ፣ አስተሻሸግና በመሳሰሉት የምርት ሒደቶች ውስጥ የተሰማሩ ሴቶች፣ ሥራቸው ጥራትና ብቃትን መሠረት እንዲያደርግ በሥልጠና መታገዝ እንዳለባቸው፣ ይህ ዓይነቱ አሠራርም ጥራቱ የተጠበቀ ቡና በአባላቱ ዘንድ ግብይት እንዲፈጸምበት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ የቡና ጥራት ብቻም ሳይሆን የቡና የንግድ መለያ ወይም ብራንድን መሠረት ያደረገ አሠራር ላይ እንዲሁም በቡና ቱሪዝም መስክ ሊገኙ ስለሚችሉ ጠቀሜታዎች በምክክር መድረኩ ወቅት ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውን በዋቢነት አውስተዋል፡፡
የቡና ቱሪዝምን ማጎልበት ተጨማሪ ጥቅም እንደሚያስገኝ፣ ማኅበሩም በዚሁ ላይ ለመሥራት ስለማቀዱ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ እንግዳ አቀባበል የሚደረግለት ቡና በማፍላት እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ መሠረት፣ ይህ በንግድ ደረጃ እንዲጎለብት የተደረገ ጥረት ባለመኖሩ ማኅበራቸው ትኩረት እንደሰጠው አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ ባለው ሥራ ላይም ዋነኛ ተዋናዮች ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ይህንን መስክ አሳድገን፣ የቱሪዝም መስህብ አድርገን ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የምንጠጣው ቡና ምን ያህል ጥራት እንዳለው እናሳውቃለን፤›› በማለት የቡና ቱሪዝም ላይ መሥራት የኢትዮጵያ ቡናን ለማስተዋወቅ ብቻም ሳይሆን የሚያስገኘው ጠቀሜታም እንደታሰበበት ገልጸዋል፡፡
የማኅበሩ አባላት እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡትን ቡና ከ100 ገበሬዎች በመግዛት የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲችሉ ማድረጉም ተወስቷል፡፡ ሴት ቡና ቆዪዎች ምርቱን በቀጥታ ከሴት ገበሬዎች የሚገዙበትን የግብይት ሥርዓት ለማስፋፋት ማኅበሩ ስለማቀዱም ተጠቅሷል፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሴቶች ቡና ቆይዎችን የሚወክሉ አካላትን በመፍጠር፣ ሴቶች ገበሬዎችን በማፈላለግ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና እንዲያመርቱ በማገዝ ቡናውን መግዛት የማኅበሩ ዕቅድ እንደሆነ ወ/ሮ መሠረት አስታውቀዋል፡፡ ሴት ቡና አምራቾች ከሌሎች የቡና ዘርፍ ተዋንያን ሴቶች ጋር በትስስር የሚገበያዩበትን መድረክ መፍጠርም የዚሁ ተግባር አካል እንደሚሆን ከወ/ሮ መሠረት ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በቡና ሥራ መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ቁጥር ከቡና የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ብሎም የሴቶችን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት ማጉላት ማኅበሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት ሲሆኑ፣ ከዚህ አኳያ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁበት ያስረዱት ወ/ሮ መሠረት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቡና እንዳለው አቅም አልተሸጠም፡፡ አገሪቷ የአቅሟን ያህል አላገኘችም፡፡ ላኪውም አላገኘም፤›› ይላሉ፡፡ ይህን ለማሻሻል በርካታ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ያብራራሉ፡፡ የአገሪቱም የቡና ተዋንያኑም ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆን የሚከነክናቸው አካላት በተለያዩ መድረኮች ሐሳቦቻቸውን ሲሰነዝሩ እንደቆዩ አንስተዋል፡፡
ወጪ ንግዱ የገቢ ንግዱ ደጋፊ ከመሆን አልፎ በራሱ መቆም እንደተሳነው፣ ላኪውም ለትርፍ መሥራት እንዳቆመ ወይም አትራፊ መሆን እንዳልቻለ ለዚህ ደግሞ ወጪ ንግዱን እንዲደጉም የሚያስገደዱ የንግድ ችግሮች በመሆናቸው እንደሆነ፣ በገበያው ሰንሰለት ውስጥ በርካታ ደላሎች መኖራቸውና የእሴት ሰንሰለቱን ማራመዘማቸው ለቡናው ዘርፍ ደካማ መሆን ተደጋግመው ሲሰነዘሩ የሚደመጡ ሐሳቦች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች በመሰንዘር ‹‹ነገሩን በሌሎች ላይ ማላከኩን ትተን ወደ ውስጣችን ማየት አለብን፤›› ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና በአግባቡ ባለመታወቁና ብራንድ ወይም የራሳቸው የንግድ መለያ ያላቸውን ምርቶችን አጉልቶ ማውጣት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብራንድ ተብለው በዓለም ገበያ የሚታወቁት የይርጋ ጨፌ፣ የሐረርና የሲዳማ ቡናዎች ሲሆኑ፣ በዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ተቋም አማካይነት በኢትዮጵያ ባለመብትነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ግን በጣዕምና በጥራታቸው እየወጡ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቡናዎችን ማስተዋወቅ እንደሚገባ ወ/ሮ መሠረት አስታውቀዋል፡፡
እንዲህ ያለውን ሥራ በውጤታማነት ለመወጣት ግን የአገር ውስጥ የገበያ ሥርዓትን በሚገባ መፈተሽ እንደሚገባ፣ ሥራውም በቡና ማሳያዎች ማለቅ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና የሚፈለገውን የጥራት ደረጃና በብዛት የማምረት አቅም ከዓለም ገበያ አኳያ ውስን እንደሆነ ሲጠቅሱም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ቡና፣ እንዲሁም በዓለም ገበያ ያላት ድርሻ ከሦስት በመቶ በልጦ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ይህንን ለመለወጥ አዳዲስ ቡናዎችም ማስለመድ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጰያ ዘመናዊ የቡና ግብርና ሥራ ውስጥ ሴቶችን በመስኩ ለማብቃት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ማኅበሩ ስላከናወናቸው ሥራዎች ከሌሎች የዘርፉ አካላት ስለማኅበሩ ተነግሮ ነበር፡፡
ማኅበሩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ያጎላሉ ካላቸው ሥራዎች አንዱ የቡና መቀነባበሪያ ማዕከል መገንባት ነው፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋው እንደገለጹት፣ ማኅበሩ ለማስገንባት ባቀደው የቡና ማቀነባበሪያ ተቋም ግንባታ ላይ መሥሪያ ቤታቸው ዕገዛ ያደርጋል፡፡ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሴቶቹ የጀመሩትን ሥራ በማገዝ ዓላማቸው እንዲሳካ ባለሥልጣኑ አብሯቸው እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹አገራችን ከቡና የምታገኘው ጥቅም ከፍ እንዲል በጋራ እንሠራለን፡፡ ቢሮ ሰጥተናቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሠሩ ስለሆነ ልንደግፋቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡