Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ለዓይን ሕያውነት

ኦርቢስ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የሚንቀሳቀስባቸውም አካባቢዎች በዋናነት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ጥቂት ቦታዎች መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ ለኅብረተሰቡ የሚሰጣቸው አገልግቶች የዓይነ ሥውርነትና የዕይታ መዛባት/መቀነስ መንስዔ በሆኑ የዓይን ሕመሞች ላይ የመከላከል፣ የማከምና አቅም የማጎልበት ተግባራት ናቸው፡፡ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የገጠር ሕክምና ዋና ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ተዘራ ክፍሌ እንቅስቃሴውንና ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር ያካሄዱት ቃለ ምልልስ ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አቀናብሮታል፡፡

ጥያቄ፡- ለዕይታ መቀነስ/መዛባትና ለዓይነ ሥውርነት መንስዔ የሆኑ ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ተዘራ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለዕይታ መቀነስ/መዛባትና ዓይነ ሥውርነት ዋነኛ መንስዔዎች የሆኑት የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ ትራኮማ፣ ግላኮማ፣ በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ መቀነስ ናቸው፡፡ እንዲሁም በትራኮማ ሳቢያ የዓይን ሽፋሽፍት (ትራኮማቲስ ትሪቺያሊ) ወደ ውስጥ የመቀልበስ ችግርም ከመንስዔዎቹም መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ በትራኮማ ተጠቃሽ ናት፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በአብዛኛው በዕድሜ፣ በመጠኑ ደግሞ በአደጋ ምክንያት ሊመጣ ይችላል፡፡ የዓይን ሽፋሽፍት ወደ ውስጥ መቀልበስ ደግሞ መስታወት የሚመስለውን የዓይን ክፍል እየፋቀ ወደ ማይታከም ወይም ወደ ማይመለስ ዓይነ ሥውርነት ሊዳርግ ይችላል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጀ በ1997 ዓ.ም. እና በ1998 ዓ.ም. የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው፣ የትራኮማ ሥርጭት መጠን ቀንሷል፡፡ የዓይን ሽፋሽፍት ወደ ውስጥ የመቀልበስ ችግር ከደረሰባቸው 880,000 ወገኖች መካከልም 287,000 ያህሉ ከችግሩ ተላቀዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በዓይን ሕክምና አገልግሎት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከአገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅተው በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ባካሄዱት እንቅስቃሴ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በዋናነት በሚንቀሳቀስበት በደቡብ ክልል ከትራኮማ ነፃ የሆኑ አካባቢዎች አሉ?

አቶ ተዘራ፡- በእንግሊዝ መንግሥት የሚደገፍ ትራኮማ ማፒንግ ፕሮጀክት በ2005 ዓ.ም. ተቋቁሞ ነበር፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትራኮማ የተመቱ አገሮችን የጥቃት መጠን ዳሰሳ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሥራውንም በዋነኝነት ያከናወነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የትራኮማ ዳሰሳ ተሠርቷል፡፡ በዚህም በእያንዳንዱ ወረዳ ያለው የሚያመረቅዝ አፍለኛ (አክቲቭ) ትራኮማና የዓይን ሽፋሽፍት ወደ ውስጥ የመቀልበስ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ተጠንቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በዋነኝነት በሚንቀሳቀስበት የደቡብ ክልል 136 ወረዳዎች ውስጥ 22 ያህሉ ከትራኮማ ነፃ እየሆኑ ናቸው፡፡ የዓይን ሽፋሽፍት ወደ ውስጥ የመቀልበስ ሁኔታ በጣም እየቀነሰ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ትራኮማን ከኢትዮጵያ ብሎም ከዓለም ለማጥፋት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ባፀደቀው ሴፍ ስትራቴጂ መሠረት ነው፡፡ ይህም ማለት የዓይን ሽፋሽፍት ወደ ውስጥ የመቀልበስ ችግር ላጋጠማቸው ወገኖችን ከችግራቸው ለማላቀቅ የተፋጠነ ሥራ መሥራት ሲሆን፣ ይህም ገንዘብና ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ጥያቄ፡- የዓለም ጤና ድርጅት ያፀደቀውን ስትራቴጂ አተገባበር በዝርዝር ቢያብራሩልን?

አቶ ተዘራ፡- በስትራቴጂው መሠረት በትራኮማ ለተጠቁ ወገኖች የመድኃኒት ሥርጭት እናካሂዳለን፡፡ ይህ ዓይነቱ መድኃኒት በትራኮማ ዓይናቸው ለመረቀዘባቸው ሰዎች እንዲታከሙ ያደርጋል፡፡ ገና በትራኮማ ያልተጠቁ ሕፃናት ደግሞ በበሽታው እንዳይያዙ ይከላከላል፡፡ በዚህ መልኩ በየዓመቱ እስከ አሥር ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወገኖች መድኃኒት ይሠራጫል፡፡ የግልና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅም የስትራቴጂ አካል ነው፡፡ ትራኮማ ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚተላለፍና እንዴት መከላከል እንደሚቻል በየትምህርት ቤቱና በየማኅበረሰቡ ይሰጣል፡፡ በተቻለ መጠን ደግሞ እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ፣ እንዲሁም በመፀዳጃ ቤት መጠቀም ዓይነ ሥውርነትን ከመከላከል አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ኅብረተሰቡ እንዲረዳው ይደረጋል፡፡

ጥያቄ፡- ለዓይን ሞራ ግርዶሽ  ሕክምናው ምንድነው?

አቶ ተዘራ፡- የዓይን ሞራ ግርዶሽ በአብዛኛው የሚመጣው ዕድሜያችን ከፍ እያለ በሚሄድበት ጊዜ ልክ ፀጉራችን ሽበት እንደሚይዘው፣ ቆዳችንም እንደሚጨማደደውና የሰውነታችን ልዩ ልዩ አካላት ሥራቸውን እንደሚያዛቡት ሁሉ ዓይናችን ኳስ ውስጥ የሚገኘው በተፈጥሮ ንፁህና ምንም ነገር የሌለበት ‹‹ሌንስ›› የሚባለው ክፍል እየተዛባ ሲመጣ ብርሃን ማስተላለፍ ይሳነዋል፡፡ በዚህም ጊዜ የሚያስፈልገው ሕክምና ኦፕራሲዮን ብቻ ነው እንጂ ሌላ የሜዲካል ትሪትመንት የለም፡፡

ጥያቄ፡- ይህ ዓይነቱን ቀዶ ሕክምና ለገጠሩ ታካሚዎች በምን መልኩ ነው የምታዳርሱት?

አቶ ተዘራ፡- የገጠሩ ሕዝብ ይህንን የኦፕራሲዮን አገልግሎት የሚያገኘው ወደ ትልልቅ ከተሞች (ሐዋሳ፣ መቐለ፣ አዲስ አበባ፣ ወዘተ) በመምጣት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ደግሞ ታካሚውን ለእንግልትና ለኪሳራ ይዳርገዋል፡፡ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት ወይም ችግሩን በይበልጥ በመረዳት ወደ ኅብረተሰቡ ቢያንስ አንድ ዕርምጃ የቀረበ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት በዋነኛነት ከሚንቀሳቀሱባት ክልል በተጨማሪ በትግራይ ማይጨው፣ በአማራ ደብረ ታቦርና በወላይታ አርባ ምንጭ የሚያስፈልጉትን ማቴሪያሎችና ግብዓቶች በማቅረብ፣ ክትትልና ድጋፍ በመስጠት ኅብረተሰቡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ኦፕራሲዮን በአቅራቢያው እንዲያገኝ አድርጓል፡፡

ጥያቄ፡- የባለሙያዎች አመዳደብ ላይ አልተቸገራችሁም? ከዚህም ሌላ በዓይን መነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ መቀነስ/መዛባት ለመከላከል ምን ጥረት ተደርጓል?

አቶ ተዘራ፡- ኢፕቶሞሊዲፕስቶችን በየገጠሩ መመደብ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡  ከቁጥራቸው ማነስ የተነሳ፣ ስለዚህ እነሱን የሚተኩ በጤና ሚኒስቴር በተደረገው ስምምነት መሠረት ካትራካት ሰርጂኖችን በመመደብ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፡፡ በዓይን መነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ መዛባት ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የገጠር ዓይን ክብካቤ ፕሮግራም በአርባ ምንጭና በጉራጌ ዞኖች በሚገኙ የመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ የመነጽር ማምረቻ ማዕከላትን አቋቁሟል፡፡

ከዚህም ማዕከል እየተመረቱ የሚወጡት መነጽሮች የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ አቅም ባገናዘበ መጠን ተሸጦ የሚገኘውን ገቢ ተጠቃሚዎቹ በሪቮልቪንግ ፈንድ አማካይነት እንዲጠቀሙበት እየተደረገ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ የዕይታ መዛባት ችግር ያለባቸው ሕፃናት ‹‹ደደብ›› እየተባሉ ከመሰደባቸውም በላይ በዚህም ተማረው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱን ችግር ለማስቀረት ሲባል ሕፃናቱ በየዓመቱ የዕይታ ልኬት እየተደረገባቸው መነጽር በነፃ እንዲሰጣቸው እየተደረገ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ይህንን ጉዳይ ዘርዘር ባለ መልኩ ቢያብራሩልን?

አቶ ተዘራ፡- በየትምህርት ቤቶቹ የዕይታ መዛባት ያለባቸው ሕፃናት ቀደም ሲል በሠለጠኑ መምህራን ይለያሉ፡፡ ከዚህም በጤና ተቋም የሚገኘው ባለሙያ ደግሞ ተጨማሪ ምርመራ ይደረግላቸውና ችግራቸው በመነጽር ሊስተካከል የሚችል መሆኑን ሲረጋገጥ መነጽሩ በነፃ ይሰጣቸዋል፡፡ በየትምህርት ቤቱም የዓይን ጤና ቡድን/ክለብ በማቋቋም ሕፃናቱ ፊትንና እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ እንዲያዘወትር የሚያስገነዘብ ትምህርት ይሰጣል፡፡ አካባቢያቸውንም እንዲያፀዱ ያበረታታሉ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ መሠረተ ሐሳቡ ሕፃናቱ በትምህርት ቤት ያገኙትን ወይም የቀሰሙትን ዕውቀት ይዘው ወደ የመኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ወላጆቻቸውን መልሰው ያስተምራሉ የሚል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ሥራ በጤና አክስቴንሽንና በጤና ልማት ውስጥም ይከናወናል፡፡ ከዚህ አንፃር የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን ሴፍ ስትራቴጂ ሙሉ ፓኬጅ በዚህ መልኩ እየተገበረ ለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ጥያቄ፡- የዓይን ሞራ ግርዶሽን ለመግፈፍ ስንት ሰዓት ይፈጃል? ለዚህስ አገልግሎት የሚፈለገው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው?

አቶ ተዘራ፡- ይህ ዓይነቱን ቀዶ ሕክምና ለማከናወን 15 እና 20 ደቂቃ ነው የሚፈጀው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ይህ መሰሉን የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ገንዘብ መክፈል ግድ ይላል፡፡ እኛ ግን በየገጠሩ ባሉት የመንግሥት ሕክምና ተቋማት ውስጥ ባቋቋምናቸው ሁለተኛ ደረጃ የዓይን ክሊኒክ ውስጥ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጠይቀው ክፍያ ከፍተኛ 600 ብር ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ሰዎች በክፍያ መታከም ወይም መዳን እችላለሁ የሚል ስሜት እንዲያድርባቸውና ከጥገኝነት አመለካከት እንዲላቀቁ ለማድረግ እንጂ ክፍያው የአንድ ሰርጀሪን ዋጋ ይመልሳል ማለት አይደለም፡፡ ኦፕራሲዮን ተደርገው በማግሥቱ የታሸገው ዓይናቸው ተከፍቶ ማየት የቻሉ ሰዎች ምን ያህል ደስታ እንደሚፈጥርባቸው መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከሰውነታችን ክፍሎች አንዱና ዋነኛው ዓይናችን ነው፡፡ የሰው ልጅ 85 በመቶ የሚሆነውን ዕውቀት የሚያገኘው በዓይኑ ከሚያየው መረጃ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2020 ትራኮማን የማጥፋት ዓላማ ነበረው፡፡ ዓመቱ ከመቃረቡ አኳያ ሌላ የተያዘ ዕቅድ ይኖር ይሆን?

አቶ ተዘራ፡- የዓለም ጤና ድርጅት ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግሥት ሥር ያሉ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲህ ዓይነት ተነሳሽነት አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት የሚደርሱበትን ግብ አስቀምጠው ያቅዳሉ፡፡ ዕቅድ ደግሞ ሁልጊዜም ሊለወጥ ሊስተካከል፣ ሊሻሻል የሚችል ነገር ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው ግብ መሠረት ኢትዮጵያን ጨምሮ አባላት አገሮች ፈርመው ሲያንቀሳቅሷቸው የነበሩት ሥራዎች በአብዛኛው በተሳካ መልኩ ተከናውነዋል፡፡ በዚህም የአቅም ግንባታ፣ ኅብረተሰቡ የራሱን ጤና እንዲያበለፅግና ንቃተ ህሊናውም ከፍ እንዲል፣ የመንግሥት ጤና ተቋማት የዓይን ጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አኳያ ብዙ ርቀት ተካሂዷል፡፡ ይህ ግብ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ግሩም የሆኑ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን ከቀሩ ሥራዎች አንፃር ሲታይ ምናልባት የ2020 ዒላማ ይከለሳል ብለን እናስባለን፡፡ ግን ከተሄደበት ወይም ከተሠራው ሥራ አኳያ ሲታይ አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል ማለት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፡- ለድርጅቱ ሥራ መቃናት በመንግሥት በኩል የሚታየው ዕገዛና ድጋፍ ምን ይመስላል? ከትራኮማ ነፃ ለወጡ ወረዳዎች ዕውቅና ይቸራቸዋል ወይ?

አቶ ተዘራ፡- ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዚህም የተነሳ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለዓይነ ሥውርነትና የዕይታ መዛባት መንስዔዎችን በማከምና በመከላከል ሲሠራ የቆየው ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ያለ መንግሥት ተሳትፎ ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ይህም ማለት ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከዞንና ከወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤቶች ጋር እንዲሁም በዋነኝነት ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ሥራውን የማቀላጠፍ፣ የፋይናንስና የቴክኒካል ድጋፍ በመስጠት፣ የአካባቢው አቅም በመገንባት እየሠራ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አኳያ ያለ መንግሥት መዋቅር ተሳትፎ ፍፁም መሥራት አይቻለውም፡፡ ከመንግሥት ጋር በጋራ ፕሮጀክቶችን እንቀርፃለን፡፡ በጋራ እንተገብራለን፡፡ በጋራ ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በተረፈ የዓለም ጤና ድርጅት ዕውቅና የሚቸረው ለየወረዳው ሳይሆን አገር አቀፍ ደረጃ ያለው የትራኮማ በሽታ ከዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ከአምስት በመቶ በታች መሆኑን፣ ነፃ በሆነ አካል ተጠንቶ ከተረጋገጠና ኢትዮጵያ ይህ ውጤት ይረጋገጥልኝ ብላ ስትጠይቅ ነው፡፡ ይህም ረዥም ሒደት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ በርካታ የአገሪቱ ክልሎችም ተፈለገው ነጥብ ላይ ገና አልደረሱም፡፡

ጥያቄ፡- ትራኮማ የድህነት በሽታ ነው ለማለት ይቻላል?

አቶ ተዘራ፡- ትራኮማ የደሃ ደሃ በሽታ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነቷ ተላቅቃ በማግሥቱ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ዘንድ ወይም ከዚያም በላይ ብትደርስም ትራኮማ አይጠፋም፡፡ ትራኮማ በቀጥታ ከድህነትና ካለማወቅ፣ ከግንዛቤ ማነስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቆሻሻን ለማንሳት መፀዳጃ ቤት ለመሥራት ገንዘብና ዕውቀት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ድህነት ይህንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ይህም ለትራኮማ መፈጠርና መሠራጨት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ የአገራችን የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካው ሁኔታ ወደፊት እየተሻሻለ በሚሄድበት ጊዜ ትራኮማ ታሪክ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ዛሬ ትልልቅ የሆኑ አገሮችም በዚሁ መንገድ ነው ያለፉት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...