ማመንጫዎቹ በሁለት ዓመት ተገንብተው ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ
በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት እንዲገነቡ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች መካከል የመጀመርያዎቹ ሁለት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ፈረመ።
አክዋ ፓወር የተሰኘው ይህ የሳዑዲ ኩባንያ፣ ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ብቸኛው በመሆን የተወዳደረ ሲሆን፣ የተቀመጡትን መሥፈርቶች ከማሟላት ባሻገር ዝቅተኛውን የመሸጫ ትርፍ በማቅረቡ እንደተመረጠ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ከሚተዳደረው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄነራል የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ፕሮጀክቶችን ገንብቶ የመነጨውን ኃይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የተስማማው ይህ ኩባንያ፣ ኃይል የሚሸጥበት ዋጋም በኪሎ ዋት ሰዓት 2.5 የአሜሪካ ሳንቲም ሲሆን፣ ይህ ታሪፍ በአፍሪካ ዝቅተኛው ዋጋ እንደሆነም ገንዘብ ሚኒስቴር ይገልጻል።
እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከፀሐይ የሚያመነጩትን እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በራሱ ወጪ እንደሚገነባቸው ታውቋል። በአፋር ክልል የሚገነባው የኃይል ማመንጫ ዲቼቶ በተሰኘ አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ ስያሜውንም ከአካባቢው በመውሰድ የፕሮጀክቱ መጠሪያ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ጋድ በተሰኘ አካባቢም 125 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ዋናው ኃይል ማመንጫ ኃይል እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል፡፡
የአክዋ ፓወር ኩባንያ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚኒስተር ፓዲ ፓድማናታን ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት ኩባንያው ፍላጎቱን እንዳሳወቀና ይህንንም በስምምነት እንዳረጋገጠ ገልጸው፣ እ.ኤ.አ. በ2021 ገንብቶ በማጠናቀቅ ያመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት እንደሚያስገባ አስታውቀዋል።
ስምምነቱን ከኩባንያው ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ ኩባንያው በውኃና በኃይል ልማት መስክ ካለው ልምድና አቅም አኳያ መመረጡን፣ ስምምነት የፈጸመባቸውን ፕሮጀክቶችም በወቅቱ ገንብቶ ለውጤት እንደሚያበቃ እምነታቸውን ገልጸውላቸዋል።
ከ20 ዓመታት በላይ በሚዘልቀው በዚህ ስምምነት የመንግሥት ሚና የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ከመቆጣጠር ባሻገር የመነጨውን የኃይል መጠን በተስማማበት ዋጋ ከኩባንያው በመግዛት ለፍጆታ ማዋል ነው።
ይህ ቢባልም በጨረታው አምስት ኩባንያዎች እንደሚወዳደሩ ተጠብቆ የሳዑዲው ኩባንያ ብቻውን እስከመጨረሻው ሒደት በብቸኝት መሳተፉ ታውቋል፡፡ ጨረታው ሊከፈት አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ ተጫራቾቹ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መሥፈርት ባለማሟላታቸው ውድቅ መደረጋቸውን የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ጥላሁን ታደሰ ከሪፖርተር ስለጉዳዩ ተጠይቀው አብራርተዋል፡፡
በጨረታው ሒደት ላይ ቅሬታ ያቀረቡት ኩባንያዎች፣ የጨረታ ጊዜው ሊራዘምላቸው እንደሚገባ መጠየቃቸውን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በጨረታ ሰነዱ ላይ በግልጽ የተመለከቱትን መሥፈርቶች እንዳላሟሉና ያቀረቡት የጨረታ ይራዘምልን ጥያቄም በጨረታ ሰነዱ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ መሠረት ባለመቅረቡና ጨረታው ሊከፈት ሰዓታት ሲቀሩት የቀረበ በመሆኑ ውድቅ እንደተደረገ አብራርተዋል፡፡ የጨረታው ሦስት ዋና ዋና መሥፈርቶች የተባሉት የፋይናንስ፣ የቴክኒክ እንዲሁም ለፕሮጀክቶቹ የሚውሉ ብድሮች ከነወለዶቻቸው ገደብ አልባ እንዲሁም አስገዳጅ ሁኔታዎች የሌሉባቸውን ብድሮች ማቅረብ (Unconditional Term Sheet of Commercial Requirement) ናቸው፡፡ እነዚህን መሥፈርቶች ሌሎቹ ተሳታፊዎች ሙሉ በሙሉ ባለማሟላታቸው እንዲሁም ለጨረታው የተሰጠው ዝቅተኛ ዋጋ የሳዑዲ ኩባንያ ያቀረበው ሆኖ በመገኘቱ ሊያስመርጠው እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡ በጨረታው ኢዲኤፍ ኢነርጂ፣ ኤነል ግሪን ፓወር፣ ግሎብ ኤሌክትሪክ እንዲሁም አል ኖዌስ ግሩፕ የተሰኙ የእንግሊዝ፣ የጣልያን፣ የካናዳና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ ቢያስገቡም፣ የሳዑዲው አክዋ ፓወር የጨረታው አሸናፊ በመሆን ስምምነት ፈርሟል፡፡
ለጨረታው 12 ኩባንያዎች ታጭተው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ኩባንያዎች የኃይል ማመንጫዎቹ በሚገነቡባቸው ቦታዎች ጉብኝት በማድረግና ለተጫራቾች በተዘጋጀው ስብሰባ መሳተፋቸው ሲገለጽ፣ አምስት ኩባንያዎችም የጨረታ ሰነድ በማስገባት መሳተፋቸውን ሚኒስቴሩ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የሳዑዲው ኩባንያ የቴክኒክና የፋይናንስ መሥፈርቶችን በማሟላቱ ሊመረጥ መብቃቱን የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክተር ጄነራል ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
አክዋ ፓወር በመካከለኛው ምሥራቅ በበርካታ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፍ ሲሆን፣ በሳዑዲ መንግሥት (ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ የተሰኘ መንግሥታዊ ተቋም) የ25 በመቶ የአክሲዮን ድርሻና የ15 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለባቸው የመንግሥትና የግል ኩባንያዎች የጋራ ኩባንያ ነው፡፡ አቡናያን ትሬዲንግ አብዱልቃድር አል ሙሐይዲብና ልጆቹ፣ እንዲሁም ማዳ ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኮሜርሺያል ዲቨሎፕመንት ግሩፕ በተሰኙ ኩባንያዎች አጋርነት የተመሠረተ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮም አክዋ ፓወር ፕሮጀክት በሚል ስያሜ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ የሚገነቡትን ዓይነት ሦስት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን በግብፅ ለመገንባት የሚያስችለውን የፋይናንስ አቅርቦት በማግኘት ለግንባታ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ በሳዑዲ 300 ሜጋ ዋትና በኦማን 445 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከመዋዋሉም በተጨማሪ፣ በሞሮኮ 120 ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ይሳተፋል ተብሏል፡፡
በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት አማካይነት ሁለቱን ፕሮጀክቶች ጨምሮ 750 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል የሚያመነጩና 1.2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቁ ስምንት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲካሄድ መንግሥት ስለመወሰኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከፀሐይ ኃይል ባሻገር፣ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ከውኃ ኃይል የሚያመነጩ ስምንት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ሦስት የፍጥነት መንገዶች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት እንዲገነቡ ተወስኗል፡፡