Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከባድ መኪኖችና ሰሞንኛው መመርያ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 2 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ መዲናዋ እንዳይንቀሳቀሱ፣ ጭነት መጫንም ሆነ ማራገፍ የሚከለክል መመርያ በማውጣት ሲያስተገብር ቆይቷል፡፡

መመርያው ተሽከርካሪዎችና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች በተጠቀሰው የጊዜ ክልል ወደ ከተማው መግባትና መንቀሳቀስ እንደማይችሉ በዚሁ መመርያ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መሠረት ከሁለት ወር ተኩል በላይ የቆየው ይህ መመርያ ከሰሞኑ ተሻሽሎ እገዳ የተጣለባቸው ተሽከርካሪም ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ከ10 ሰዓት እንዲንቀሳቀሱ ፈቅዷል፡፡ መመርያው በወጣበት ወቅት አግባብነት እንደሚጎድለው የሚገልጽ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ መጀመርያውኑ ይህ መመርያ ለምን ተገበረ? ትራንስፖርቱን የሚመራው የከተማው አስተዳደር ክፍል መመርያውን ለምን ቀለበሰው? የሚለው ብዙ ያነጋግራል፡፡ ቀድሞውንም አግባብ አልነበረም ከሚለው አስተያየት ጀምሮ፣ የመመርያው ትግበራ ያስከተለው ችግር በዝርዝር ሲቀርብ ሰምተናል፡፡ አበባ ላኪዎች ምርታቸውን በአግባቡ መላክ እንዳልቻሉ፣ ሥጋ ላኪዎችም ይህንኑ አቤቱታ በማጠናከር የመመርያው መውጣት አላላውስ እንዳላቸው በማስታወቅ ለአቤቱታ የመንግሥት ቢሮ እስከማንኳኳት መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ክስተት ነበር፡፡ የጭነት ተሽከርካሪ ባለቤቶችም ሥራ አጣን፤ ተቸገርን በማለት መመርያውን ሲቃወሙ ሰምተናል፡፡ አሽከርካሪዎችም መመርያው ከተተገበረ በኋላ ለችግር መዳረጋቸውን በየሚዲያው ገልጸዋል፡፡

የዚህ መመርያ መውጣትና ለጥቂት ጊዜም መተግበር ያስከተለው ችግር በተለያየ መንገድ እንደሚገለጽ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በየጎዳናው የምንመለከታቸው ትላልቅ የጭነት ተሽከርካሪዎችና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አብዛኛዎቹ በባንክ ብድር የተገዙና ዕዳቸውን ከፍለው ያልጨረሱ ናቸው፡፡ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች መመርያው በፀናባቸው ወራት ውስጥ የባንክ ዕዳ ባለመክፈላቸው ባንኮችንም አስደንግጦ ነበር፡፡

አንዳንድ ተሽከርካሪዎችም ከአዲስ አበባ ርቀው ሥራ ላይ ስለነበሩ፣ ባንኮቹ ዕዳ ያለባቸውን ተሽከርካሪዎች ለማግኘት እንደቸገራቸው ሲናገሩ ደግሞ የመመሪያው ዳፋ የት ድረስ እንደሄደ ያሳየ ነበር፡፡ ስለዚህ ተግባር ላይ የምናውላቸው ውሳኔዎች ከመፈጸማቸው በፊት ግራና ቀኝ መመልከት፣ ደግሞ ደጋግሞ መመልከቱ፣ ጥቅምና ጉዳቱን ማጥናቱ ግድ ነው፡፡ አስተዳደሩ ያወጣው መመርያ አግባብ አልነበረም ወደሚል መደምደሚያ ዳር ዳር እንደማይለኝ ልብ ይሏል፡፡ ሆኖም የመመርያው መተግበር ጉዳት ላይ ጣለን ያሉ ወገኖች በየፈርጃቸው ድምፃቸውን ባሰሙበት ወቅት፣ አስተዳደሩ ግን ‹‹ወይ ፍንክች ሐሳቤን አልለውጥም፤ መመርያውም አይቀለበስም፤›› በማለት በአቋሙ መጽናቱን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቶ ነበር፡፡ ድንገት ከሰሞኑ ሳይታሰብ መመርያው ተሻሽሏል አለ፡፡ አስተዳደሩ እንዲህ በአጭር ጊዜ ሐሳቡን ለውጦ መመርያውን ያሻሽላል ብሎ የጠበቀ መኖሩን እንጃ፡፡ ግን ሆነ፡፡

በመሆኑም በከተማው መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሰዓት ላይ ማሻሻያ ተደረገ፡፡ ይህ ሲሆን ግን የሚያጭርብን ጥያቄ አለ፡፡ መመርያውን ለማውጣት ያስገደደው ምክንያት የቱን ያህል አሳሳቢ ነበር? የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተሻሻለበትስ ምክንያት ይሆናል፡፡ በእርግጥ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቅረፍ ተብሎ የወጣ መመርያ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ችግር ተቀርፎ ነው መመርያው የተስተካከለው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ የተፈጥሮ ነው፡፡ ለዚህ በቂ መልስ ብናገኝ ምንኛ በወደደን ነበር፡፡ ለማንኛውም እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በይደርና ይቆዩንና ከሰሞኑ በወጣው የመመርያው  ማስተካከያ መሠረት ከጠዋቱ 4 እስከ 10 ሰዓት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እንዳሻቸው እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው ትላልቅ ተሽከርካሪዎችና ሌሎችም ክልከላ ተደርጎባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች ዳግመኛ የትራፊክ ፍሰቱን ሊያጨናንቁት እንደሚችሉ እንረዳለን፡፡

ከሰሞኑ የታዘብነው ይህኑ ነው፡፡ ተሽከርካሪዎቹ እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደበት የሰሞኑ ማሻሻያ አግባብ ከሆነና በከተማዋ ጎዳናዎችም መጠቀማቸው ካስፈለገ አስተዳደሩ  ሊፈጽም የሚገባው ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ ይህም የትራፊክ ፍሰቱ የበለጠ እንዳይጨናነቅ ሕግና ሥርዓት በደንብ እንዲከበር ማድረግ ነው፡፡ ለነገሩ ያወጣውን ሕግ ባሻው ጊዜ የሚቀያይረው ከሆነ እንዲከበር መጠበቁ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡

በሰበብ በአስባቡ ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ አሁን ያሻሻለውን ሕግ ማስተግበር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ባልሆነ መንገድ አሁንም ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለከተማው የትራፊክ መጨናነቅ መንስዔ በመሆናቸው የሕግ ማስከበሩ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከዚህም ሌላ ለከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ አንዱ ምክንያት ትላልቅ ተሽከርካሪዎች እንዳሻቸው በየመንገዱ መቆማቸው ነው፡፡ ቁጥር በማይሞሉ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች ምክንያት ከተማው ሲጨናነቅ የሚወሰድ ዕርምጃ የለም፡፡ የሰዓት ገደብ ሲወጣም በገደቡ መሠረት ሕጉ እንዲከበር ማድረጉ ነው፡፡ በከተማችን በተለያዩ ቦታዎች በዋና ዋና ጎዳናዎች የሚቆሙ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች የሚስናገዱበት መናኸሪያ ወይም ማደሪያ ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚያመላክት በመሆኑ፣ የከባድ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚፈቅደው መመሪያ፣ ጎዳናዎች ላይ ያለሥራ ከሚቆሙ ተሽከርካሪዎች ነፃ በማድረግ መጨናነቁን መቀነስ አለበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት