2.2 ሚሊዮን የወለድ አልባ አስቀማጮች ተመዝግበዋል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወለድ የማይታሰብበት ወይም የሸሪዓ ሥርዓትን ባሟላ መንገድ ገንዘብ የሚያስቀምጡ ደንበኞቹን ቁጥር እየጨመረ፣ በዚሁ ዘርፍም በገበያው ሰፊ ድርሻ መያዝ የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2.2 ሚሊዮን አስቀማጮች 25 ቢሊዮን ብር ማሰባሰቡን አስታውቋል፡፡ ባንኩ በዚህ ዓመት 54 ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቅርንጫፎች ለመክፈት አቅዷል፡፡
ከስምንት ዓመታት በፊት በመደበኛ ባንኮች በመስኮት ተወስኖ ይቀርብ የነበረው አገልግሎት አሁን በቅርንጫፍ ባንኮች ደረጃ ራሱን ችሎ መሰጠት በመጀመሩ ከባንኮች የራቀውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ እንደጀመረ ንግድ ባንክ አስታውቆ፣ ረቡዕ መስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ባንኩ ወለድ አልባ አገልግሎት ብቻ የሚሰጠውንና ‹‹መካ›› ተብሎ የተሰየመውን ሁለተኛውን ወለድ አልባ ቅርንጫፍ ከፍቷል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የወለድ አልባ አገልግሎት ተጠቃሚዎች አፍርቷል፡፡ ከእነዚህ ደንበኞቹ የተሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብም ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ሰባት ባንኮች ከዚህ ዘርፍ ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከ20 ቢሊዮን ብር አይበልጥም ነበር፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገልጋዮቹ ቁጥር መበራከቱን ያሳያል፡፡
ከዚህ ቀደም የወጡ የንግድ ባንክ መረጃዎች በሁለት ዓመታት ውስጥ በወለድ አልባ ቁጠባ የሚቀመጠው የገንዘብ መጠን ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡ ወለድ አልባ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎች ሲታከሉበት፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር ይበልጡን እየጨመረ እንደሚመጣ ይታመናል፡፡ ወለድ አልባ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን በዓመት ውስጥ 54 ለማድረስ ማቀዱም በዘርፉ ያለውን ሰፊ እንቅስቃሴ አመላክቷል፡፡
እንደ አቶ ባጫ ገለጻ፣ ንግድ ባንክ በ1,443 ቅርንጫፎቹም ወለድ አልባ አገልግሎት ለብቻው በተዘጋጀ መስኮት እያቀረበ ነው፡፡ ይሁን አንጂ ራሱን በቻለ ቅርንጫፍ አገልግሎቱ ለብቻው ተለይቶ መቅረቡ የጠቃሚዎችን ቁጥር እንደሚያበራክተው ከአንድ ወር በፊት በተከፈተውና ቢላል ቅርንጫፍ የተገኘው ውጤት እንዳሳየ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡
በቢባል ወለድ አልባ ቅርንጫፍ ንግድ ባንክ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ ማቅረቡንም ባንኩ አስታውቋል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ የተከፈተው መካ ቅርንጫፍ ለደንበኞች የተሟላ አገልግሎት በሚሰጥበት ደረጃ መዘጋጀቱን አቶ ባጫ ገልጸው፣ ቅርንጫፎቹ የሸሪዓ መርህን የተከተሉ የተቀማጭ ገንዘብ፣ የፋይናንስ፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎችም የባንክ አገልግሎቶችን አሟልተው ያቀርባሉ ብለዋል፡፡
‹‹እንደ ቢላልና መካ ልዩ ቅርንጫፎች ሁሉ በሸሪዓ ሕግ መሠረት የተሟላ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ከ14 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍተን አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ባጫ አስታውቀዋል፡፡ የተከፈቱት እነዚህ ቅርንጫፎች ወደፊት በተያዘላቸው ጊዜ በይፋ እንደሚመረቁም አክለዋል፡፡ ቅርንጫፉ ሥራ በጀመረ በሰዓታት ውስጥ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ገቢ መደረጉ ታውቋል፡፡
በመካ ቅርንጫፍ ምረቃ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሙፍቲ ሐጅ ኡመር ኢድሪስ፣ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እያሰፋ ሕግ ወጥቶለት እንዲተገበር መደረጉ ሙስሊምና ክርስቲያኑን፣ ሙስሊሙንና መንግሥትን የሚያቀርብ አገራዊ ሥራ እንደሆነ ገልጸውታል፡፡
‹‹ሙስሊሙ እስካሁን ድረስ አልተስተናገደም ነበር፡፡ ወለድ ከልክሎት ነበር፡፡ አሁን እንጥቀመው ተብሎ የተጀመረው ነገር ሊመሠገን ይገባዋል፤›› ያሉት ሙፍቲህ ሐጅ ኡመር፣ እንደ ዘምዘምና ሒጀራ ያሉ ወለድ አልባ የግል ባንኮች ለመከፈት መዘጋጀታቸውም ለዘርፉ ማደግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
የመካ ቅርንጫፍ ሥራ መጀመርን በማስመልከት በተሰናደው የምርቃት ፕሮግራም ላይ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎትና ጠቀሜታውም ተወስቶ ነበር፡፡ በተለይ በንግድ ባንክ የወለድ አልባ አገልግሎት የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሼክ መሐመድ ሐመዲን እንደገለጹት፣ ይህ ዘርፍ አዋጭና ጠቀሜታውም የጎላ ነው፡፡ ወለድ የማይፈልጉ ነገር ግን ከባንክ የራቁ ሰዎች ወደ ባንክ መጥተው ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ፣ እንዲያንቀሳቅሱ፣ የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩና በመደበኛው ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሳተፉ ዕድል የሚከፍት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ቅርንጫፍ መከፈቱ ለአገራችን ትልቅ ብሥራት ነው ያሉት ሼክ መሐመድ፣ ሁሉም ተገልጋይ ‹‹ያለምንም ልዩነት፣ ያለ ገደብ፣ ያለ ምንም መሳቀቅ በአገሪቱ ዕድገት ላይ የጋራ ርብርብ የሚያደርግበትን ዕድል የሚሰጥ ነገር ነው፤›› በማለት ስለአገልግሎቱ ተናግረዋል፡፡
‹‹እኛ የሥራ ቦርድ አማካሪዎቹም ወደዚህ ከተቀላቀልን ጀምሮ አገልግሎቱ የሸሪዓውን መስመር ስለመከተሉ በደንብ እያጣራንና እየሠራን ነው፡፡ በርካታ ነገሮችን እየተመለከትን ነው፡፡ በጤናማ ጉዞ እየተከናወነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዕለቱ እንደተከፈተው ዓይነት ራሱን የቻለ ቅርንጫፍ ወደ ሥራ ማስገባቱ እንዴት እንደተጀመረም ወደ ኋላ በመመለስ አስቃኝተዋል፡፡
ከወራት በፊት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጀይላን ከድር (ዶ/ር) ይህ አገልግሎት በመስኮት እንዲቀርብ ከተፈቀደ ራሱን የቻለ ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚከለክለው እንደሌለ መረጋገጡንና ተገልጋዮችም እንዲከፈት መጠየቃቸውን ገልጸው ነበር፡፡ አገልግሎቱ በዚህ መልኩ ቢጀመር ተጠቃሚው ማኅበረሰብ እንደሚፈልገው ያቀረቡትን ሐሳብ አማካሪ ቦርዱ ለባንኩ አመራሮች ማቀረቡንና አመራሩም ተቀብሎት መተግበሩን ተናግረዋል፡፡ ወለድ አልባ አገልግሎቱ በመስኮት እንዲቀርብ ከተፈቀደ፣ በቅርንጫፍ ደረጃ እንዳይቀርብ የሚከለክል ሕግ ስለሌለ በዚሁ አግባብ እንደተጀመረም ተብራርቷል፡፡ እየተከፈቱ ለሚገኙት የወለድ አልባ ቅርንጫፎች መነሻ ሐሳብ እንዳቀረቡ የሚጠቀሱት የባንኩ ሸርዓ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ይህ አገልግሎት እንዲስፋፋ የበለጠ መሠራት አለበት ይላሉ፡፡
ባንኩ ከፍተኛ የወለድ አልባ የተቀማጭ ገንዘብ ቢያሰባስብም፣ እስካሁን በወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት ወይም በብድር የተሰጠው ገንዘብ አነስተኛ ነው፡፡ ባንኩ ከወለድ አልባ አገልግሎቱ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የቁጠባ ገንዘብ ቢያሰባስብም፣ በዚሁ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞች የሸሪዓ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የሰጠው ብድር 1.1 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎቱ ከተሰባሰበው ገንዘብ አንፃር አነስተኛ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ተብሏል፡፡
የባንኩ የሸሪዓ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሼክ መሐመድም በዚሁ ላይ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የተቀማጭ ገንዘቡ ማደጉ ትልቅ ዕመርታ እንደሆነ ገልጸው፣ የተሰጠው ብድር 1.1 ቢሊዮን ብር ብቻ የሆነበት ምክንያት ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ወለድን የሚከለክለው እስልምና ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም ሃይማኖት ይከለክላል፡፡ ጎጂነቱ በተጨባጭ የሚታይ ነው፡፡ የሚታወቅም ነው፤›› ያሉት ሼክ መሐመድ፣ ዕድሉ ለተጠቃሚው ቢቀርብም፣ ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን አውቆ እየተገለገለበት እንዳልሆነ ስለሚያሳይ፣ በአገልግሎቱ እንዲጠቀም ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የተሰበሰበው ገንዘብ ሥራ ውስጥ ቢገባ ብዙ ለውጥ እንደሚያመጣ አስታውሰው፣ የወለድ አልባ ፋይናንስ ተጠቃሚዎችን በፋይናንሱ እንዲጠቀሙበት ጋብዘዋል፡፡