ወለድ አልባው ዘምዘም ባንክ የ600 ሚሊዮን ብር ካፒታል አሰባሰበ
በቅርቡ የአክሲዮን ሽያጭ የጀመረውና በምሥረታ ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች መሸጡ ተገለጸ፡፡
ከባንኩ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ የአክሲዮን ሽያጩ በየሳምንቱ እየጨመረ በመምጣቱ የተሸጡት አክሲዮኖች ባንኩን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታል በአጭር ጊዜ በማሟላት በዚህ ዓመት ወደ ሥራ ለመግባት ያስችሉታል ተብሏል፡፡
ባንኩ አክሲዮን ሽያጭ በይፋ የጀመረው ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 400 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጩን በማከናወን በኢንዱስትሪው ውስጥ ይህንን ያህል የአክሲዮኖች ሽያጭ በማሰባሰብ ፈጣን ጅምር ያሳየና በምሥረታ ላይ የሚገኝ ባንክ ያደርገዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ሕግ በሚፈቀደው መሠረት ባንኮችን ለመመሥረት ይጠየቅ የነበረው ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል መጠን 100 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህንን ገንዘብ ለማሟላት በምሥረታ ላይ የነበሩ ባንኮች ከአንድ ዓመት በላይ ይወሰድባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ባንክ ለማቋቋም ይጠየቅ የነበረው የተከፈለ ካፒታል መጠን ወደ 500 ሚሊዮን ብር በማደጉ ለምሥረታ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ ባንኮች መመናመን፣ መንገድ የጀመሩትም ከስመው እንደቀሩ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከዓመታት በፊት የንግድ ባንኮችን ለማቋቋም ይጠይቅ የነበረው የተከፈለ ካፒታል መጠን 75 ሚሊዮን ከዚያም 100 ሚሊዮን ብር በነበረበት ወቅት የተቋቋሙ ባንኮች፣ ይህንን ካፒታል ለማሟላት ይወስደባቸው የነበረው ጊዜ ከአንድ ዓመት ተኩል ያላነሰ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህንን የገንዘብ መጠን የሚጠይቀው መመሪያ ከመውጣቱ በፊት የተቋቋሙ ባንኮችም ቢሆኑ በወቅቱ ይጠየቅ የነበረውን ከ25 ሚሊዮን ብር ያነሰ ካፒታል ለመሙላት ከዓመት በላይ ይፈጅባቸው ነበር፡፡
ይሁንና አማራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጩን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደገለጸው፣ ባንኩን በ2012 ዓ.ም. አጋማሽ ሥራ ለማስጀመር አቅዷል፡፡ አሁን የደረሰበት የአክሲዮን ሽያጭ መጠን በያዘው ዕቅድ መሠረት ባንኩን ሥራ ለማስጀመር እንደሚያስችለው የባንኩ መረጃ ይጠቁማል፡፡
በአገሪቱ ሕግ መሠረት ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ አማራ ባንክ ይህንን ለመሙላት የቀረው 100 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህንን ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሟልቶ ሥራ ሊጀምር እንደሚችል ተጠቀሟል፡፡ አማራ ባንክ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚጀምር ይግለጽ እንጂ በሁለት ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል እንደሚመሠረት አስታውቋል፡፡
ከአክስዮን ሽያጩ ጎን ለጎን ቢሮ የማደራጀት ሥራ ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ፣ በመላ አገሪቱ ቅርንጫፎችን በመክፈት ሥራ እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል፡፡ የአማራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የአማራ ክልል የአንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በተገኙበት በይፋ የተጀመረ መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ የባንኩ አደራጅ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ለማቋቋም በፈር ቀዳጅነት የሚጠሰው ዘምዘም ባንክ ለምሥረታ የሚበቃውን የተከፈለ ካፒታል ማሟላት እንደቻለ አስታወቀ፡፡ ባንኩ ይፋ እንዳደረገው፣ እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ያሰባሰበው የካፒታል መጠን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡
ከባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ለማወቅ እንደተቻለው፣ ባንኩን ለመመሥረት በቅርቡ ከተጀመረው እንቅስቃሴ የተሰበሰበውን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ባሻገር፣ የ1.2 ቢሊዮን ብር አክሲዮን ለመግዛት የተመዘገቡ ባለአክሲዮኖችን ማስፈረም ችሏል፡፡ ዘምዘም ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወን ከጀመረ አራተኛ ወር ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡ ባንኩ ለመመሥረት የሚያበቃውን የካፒታል መጠን በማሟላቱ፣ በአገሪቱ ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥ የመጀመርያው ባንክ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡