Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የመጀመሪያ የሆነ በሞት የሚያስቀጣ ድንጋጌን የያዘ ረቂቅ አዋጅ...

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የመጀመሪያ የሆነ በሞት የሚያስቀጣ ድንጋጌን የያዘ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

ረቂቁ በሰዎች የመነገድ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን የሚደንግግ ነው

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የመጀመሪያ የሆነ በሞት የሚያስቀጣ ድንጋጌን የያዘ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይሁንታ አግኝቶ ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምክር ቤቱቀረበው ረቂቅ አዋጅ ስያሜበሰዎች የመነገድ፣ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገርና ሕገወጥ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅየሚል ሲሆን፣ በሥራ ላይ የሚገኙትን ተመሳሳይ አዋጆችና የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎችን የሚተካ መሆኑ ታውቋል፡፡

- Advertisement -

በሰዎች የመነገድ፣ በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሕገወጥ መንገድ ለሥራ ሥምሪት ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎች የሰዎችን አካል፣ ሕይወትና ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጡ ወንጀሎች በመሆናቸውና እነዚህን ወንጀሎች መከላከል አስፈላጊ መሆኑ እንዲሁም በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ቁጥር 909/2007 ግልጽነት የጎደለው፣ ከሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣጣምና ለችግሩ በቂ ምላሽ የማይሰጥ ሆኖ በመገኘቱ በአዲስና በተሟላ የሕግ ማዕቀፍ መተካት አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ሕጉን ማዘጋጀት አስፈላጊ እንዳደረገው የረቂቁ መግቢያ ያስረዳል፡፡

በረቂቁ ድንጋጌ መሠረት በሰዎች የመነገድ ወንጀል ማለት፣ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያ ግዛትም ሆነ ከኢትዮጵያ ግዛት ውጭ ለብዝበዛ ዓላማ በዛቻ፣ በኃይል፣ በማገት፣ በመጥለፍ፣ ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም፣ በማታለል፣ የተስፋ ቃል በመስጠት፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ የሰዎችን ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት ወይም በመቀበል ሰዎችን የመለመለ፣ ያጓጓዘ፣ ወደ ሌላ ሰው ያስተላለፈ፣ ያስጠለለ ወይም የተቀበለ፤” መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የወንጀል ድርጊቱን ከሚገልጸው ጥቅል ድንጋጌ ውስጥ የተዘረዘሩ ቃላቶች ተጨማሪ ትርጓሜ በረቂቁ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ብዝበዛ የሚለው ቃል ሰፋ ያለ ፍችን ይዟል፡፡

በዚህም መሠረት ብዝበዛ ማለትሌላውን ሰው ከፈቃዱ ውጭ ወይም ሙሉ ፈቃዱን መስጠት የማይችል ወይም ፈቃዱን መስጠት በማይችልበት ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አካሉን፣ነ ልቦናውን ወይም ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር ለራስ መጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀም ማድረግ ሲሆን፣ በተለይም በወሲብና ወሲብ ነክ ተግባር ማሰማራት ወይም መፈጸም፣ የሕፃናት ጉልበት ሥራ፣ ሰውን በባርነት መያዝ፣ አገልጋይ ማድረግ፣ የዕዳ መያዣ ማድረግ፣ የግዳጅ ሥራ እንዲሠራ ማድረግ፣ በልመና ወይም በወንጀል ተግባር ማሰማራት፣ ጋብቻ መፈጸም፣ ማህፀን ኪራይ፣ አካል መውሰድ ወይም ማውጣት ተግባር መፈጸምን ያካትታል፤የሚል ትርጓሜን ይዟል፡፡

ብዝበዛ የሚለው ትርጓሜ ውስጥ ደግሞ ሰውን በባርነት መያዝ፣ አገልጋይ ማድረግና ወሲብና ወሲብ ነክ ተግባራት የሚሉት ቃላቶች ተጨማሪ ትርጓሜ በረቂቁ ተስጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ባርነት ማለት የሌላ ሰው የባለቤትነት መብት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እየተፈጸመበት ያለ ሰው የሚገኝበት ሁኔታ ወይም አቋም እንደሆነ፣ “አገልጋይ ማድረግማለት ደግሞ አንድ ሰው ሊያስቀረው፣ ሊከላከለው ወይም ሊቀይረው በማይችልበት ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ወይም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

ወሲብና ወሲብ ነክ ተግባር ማለት ደግሞአንድን ሰው ለግብረ ሥጋ ግንኙነት አገልግሎት ማቅረብ፣ መጠቀም፣ ወይም በዝሙት ተግባር ማሰማራት፣ ጸያፍ ወይም ለመልካም ጸባይ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት በተለይም ገላን ወይም ህፍረት ሥጋ ለሌሎች እንዲያሳይ ማድረግ ሲሆን፣ እነዚህን ተግባራት በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ መቅረጽና ማሠራጨት ወይም ለማሠራጨት ዓላማ መቅረጽን ያካትታል፤የሚል ትረጓሜንዟል፡፡

ማንኛውም ሰው፣ በሰው የመነገድ ወንጀልን የፈጸመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአሥር ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ የተደነገገ ሲሆን፣ በተፈጸመው ወንጀል ሒደት ውስጥ ባለፈ ሰው ላይ ብዝበዛ የተፈጸመ ወይም መፈጸሙ ተጀምሮ እንደሆነ በሒደቱ የተሳተፈ እንዲሁም ብዝበዛውን የፈጸመው ሰው ከሰባት ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺሕ ብር እስከ 70 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቃጣ በረቂቁ ተደንጓል፡፡

በሰው የመነገድ የወንጀል ድርጊት ውስጥ የመመልመል፣ የማጓጓዝ፣ ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ፣ የማስጠለል ወይም የመቀበል ተግባር የተፈጸመ ባይሆንም በሌላ ሰው ላይ ብዝበዛ የፈጸመ ማንኛውም ሰው፣ ከሰባት ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺሕ ብር እስከ 70 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣም ያመለክታል፡፡

በከባድ ሁኔታ ድንጋጌው የተመለከተው ማለትም የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው በሕፃናት፣ በአዕምሮ ሕመምተኛ ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፣ ወይም አደንዛዥ ዕፅ፣ መድኃኒት ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንዲሁም፣ በመንግሥት ሠራተኛ ወይም በባለሥልጣን ከሆነና ወንጀሉን የፈጸመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ከሆነ፣ ወይም የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ፈቃድ ባለው አካል ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ ከሆነ፣ ቅጣቱ ከአሥር ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ30 ሺሕ እስከ አንድ መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚሆን ረቂቁ ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል የተመለከተው የወንጀል ድርጊት በከፋ መልኩ ማለትም የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን ወይም ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር የተፈጸመ እንደሆነ ወይም በተጎጂው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ወይም የማይድን በሽታ ያስከተለ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከሃምሳ ሺሕ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ ብር እንደሚሆን በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

የተፈጸመው ወንጀል በተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ እንደነገሩ ሁኔታ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞትና ከመቶ ሺሕ እስከ ሦስት መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ በሌሎች የዝሙት አዳሪነት መጠቀምን በተመለከተ በተቀመጠው ተጨማሪ ድንጋጌ፣ ማንኛውም ሰው በሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ሒደት ለመጠቀም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ለማርካት በማሰብ ሌላውን ሰው ለዝሙት ተግባር ያሰማራ፣ ያገናኘ፣ ያቀረበ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ለመጠቀም ዝሙት አዳሪን ቤቱ ያስቀመጠ፣ የሥራ ወይም የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለዚህ ተግባር ያዋለ ወይም ያከራየ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት መጠቀሚያ አድርጎ የያዘ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአሥር ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ከላይ የተመለከተው ድርጊት የተፈጸመው ሕፃናት ላይ እንደሆነ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺሕ ብር እስከ 70 ሺሕ መቀጮ እንደሚያስቀጣ የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል፡፡

ረቂቁ ኢትዮጵያውያንን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ ሒደት ውስጥ ወይም ይህንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎችም አካቷል፡፡

በዚህም መሠረት ማንኛውም ሰው ፈቃድ ሳይኖረው፣ ፈቃዱ ታግዶ ወይም ተሰርዞ እያለ ወይም እንዲልክ ፈቃድ ወዳልተሰጠው አገር ኢትዮጵያዊ ዜጋን ለሥራ ወደ ውጭ አገር የላከ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ ከላይ የተመለከተው ወንጀል የተፈጸመው የጉብኝት፣ የሕክምና፣ የትምህርት ወይም የመሰል ጉዳዮች ቪዛን ሽፋን በማድረግ እንደሆነ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ30 ሺሕ ብር እስከ 70 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ በተመለከተው የወንጀል ድርጊት ምክንያት የተላከው ሰው በሰብዓዊ መብቱ፣ በሕይወቱ፣ በአካሉ ወይም በሥነ ልቦናው ላይ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከ 20 አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ150 ሺሕ ብር እስከ 250 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

ከላይ የተገለጹትንና ሌሎች በረቂቁ የወንጀል ድርጊት መሆናቸውተገለጹት ተግባራት የተፈጸሙት የሕግ ሰውነት በተሰጠው አካል ወይም ተቋም ከሆነ ለወንጀሉ የተቀመጠው ቅጣት ተወስዶ ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶች ተሰልተው በቀላል እስራት ወይም እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ እስከ 500 ሺሕ ብር፤ ከአምስት ዓመት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት ከሆነ ከአምስት መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር፣ ከ20 ዓመት በላይ በሆነ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሆነ ከሁለት ሚሊዮን ብር እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር መቀጮ እንደሚጣልበት ረቂቁ ያመለክታል፡፡

በረቂቁ የተመለከቱትን በሰው መነገድ ወንጀል መፈጸሙን ወይም እየተፈጸመ መሆኑን ወይም የወንጀሉን ፈጻሚ ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ለፖሊስ ወይም አግባብነት ላለው የሕግ አስከባሪ አካል ወዲያውኑ ያላሳወቀ ወይም ሐሰተኛ ማስረጃ የሰጠ እንደሆነ፣ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣም በረቂቁ ተቀምጧል፡፡

በሰው የመነገድ ወንጀሎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በመደበኛው የምርመራ ዘዴ ማስረጃ ማሰባሰብ ሳይቻል ሲቀር ወይም የማይቻል ሆኖ ሲገኝ መርማሪዎች ተጠርጣሪው በፖስታ፣ በደብዳቤ፣ በቴሌፎን፣ በፋክስ፣ በራዲዮ፣ በኢንተርኔትና በሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸውን ልውውጦች ወይም ግንኙነቶች መጥለፍ እንደሚችሉ በረቂቅ ሕጉ ተደንግጓል፡፡

በተጨማሪም መርማሪዎች በወንጀል ቡድን ውስጥ ሠርጎ በመግባትና አብሮ በመሆን የተጠርጣሪዎችን እንቅስቃሴና ድርጊት በመከታተል፣ የይምሰል ግንኙነቶችን በመፍጠር፣ መከታተል እንደሚችሉ በልዩ ሁኔታ ይፈቅዳል፡፡

ልዩ የማስረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ፍርድ ቤት የምርመራውን አስፈላጊነት አምኖ ሲፈቅድ ብቻ እንደሚሆን በቋሚነት ቢደነገግም፣ ፖሊስ አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው የወንጀል ጉዳዩ ላይ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ባለው የዓቃቤ ሕግ ተቋም ኃላፊ ፈቃድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በልዩ የምርመራ ዘዴ ማስረጃ ሊሰበስብ እንደሚቻል ነገር ግን በ48 ሰዓት ውስጥ ምክንያቶችንና በዓቃቤ ሕግ የተሰጠውን ጊዚያዊ ፈቃድ ጨምሮ ለፍርድ ቤት በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚኖርበት ያመለክታል፡፡

ሰርጎ የገባ መርማሪ ማንነቱ እንዳይለይ ወይም ወንጀል ፈጻሚዎቹ ጥርጣሬ እንዳይኖራቸው ለማድረግ፣ እንዲሁም ራሱንና ሌሎችን ከአደጋ ለማዳን ብቻ በወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችል ረቂቁ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ዕርምጃዎቹን መውሰድ የሚችለው ሌላ አማራጭ በማጣት ወይም አስገዳጅ ሁኔታ በመኖሩ እንደሆነ ብቻ በወንጀል ተጠያቂ እንደማይሆን ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ከመጠን በማለፍ ወይም ከአስገዳጅ ሁኔታ ውጭ በሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት አግባብነት ባለው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ተጠያቂ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡

በሰዎች የመነገድ፣ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገርና ሕገወጥ የውጭ አገር ሥራምሪት ወንጀል መከላከልና መቆጣጠርን ዓላማው ያደረገ ብሔራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት እንደሚቋቋምና የብሔራዊ ምክር ቤቱ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ ረቂቁ ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ መደበኛ ስብሰባውን ሲጀምር በቅድሚያ ከሚመለከታቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ፓርላማው ረቂቅ አዋጁ ላይ የመጀመሪያ ውይይት ካደረገ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት መርቶታል፡፡

ረቂቁ በዚሁ መልኩ የሚፀድቅ ከሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሥልጣን ዘመን የመጀመሪያ የሚሆን፣ እንዲሁም ለመጀመሪያዋ የአገሪቱ ሴት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለፊርማ የሚቀርብ የሞት ቅጣትን የያዘ አዋጅ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ