የማሻሻያው ተግራባዊነት ጥያቄ ቀርቦበታል
‹‹የሪፎርም አጀንዳው የመኖር ጉዳይ፣ ለህልውና የሚደረግ ጉዞ ነው፤››
አቶ መላኩ አለበል፣ የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊ
በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ላይ ለመወያየት በገንዘብ ሚኒስቴር የተገኙ የክልል አመራሮች፣ በማሻሻያው ትኩረት ያሻቸዋል ካሏቸው መካከል የመሬት ጉዳይ፣ የሀብት እኩል ተጠቃሚነትና ክፍፍል እንዲጤኑ አሳሰቡ፡፡ የግብርናው ዘርፍ ከገጠር ፋይናንስና ከሥራ ዕድል አኳያ ታይቶ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል፡፡
መንግሥት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የሚተገበር አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ይፋ ከማድረጉም ባሻገር፣ በፕሮግራሙ ላይ የውይይት መድረኮችን በመዘርጋት የተለያዩ አካላትን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ተዋንያን ለውይይት መጥራቱ ይታወሳል፡፡
ማክሰኞ፣ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር በተካሄደ ውይይት የተገኙ የክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዲሱ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ውስጥ መሻሻል አለባቸው፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችም እንዳይደገሙ በማለት ካነሷቸውና መፍትሔ ይሻሉ በማለት ጥያቄ ካቀረቡባቸው መካከል የመሬት ጉዳይ የአብዛኞቹ ትኩረት ነበር፡፡ የአነስተኛና መካከለኛ መስኖ እርሻም ትኩረት እንዲሰጠው የጠየቁም ነበሩ፡፡
የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከፖለቲካው ችግሮች ጋር እንደሚያያዙ በገለጹበት ጥያቄያቸው፣ የእነዚህ ችግሮች አንዱ መገለጫ የመሬት ችግር እንደሆነ አንስተዋል፡፡ መንግሥት ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ከግብርና ወጪ ንግድ አኳያ ያሉበት ችግሮች ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች በመሆናቸው ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊሰጥባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ መላኩ ሐሳብ የመንግሥት አዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ‹‹ችግሮችን ያለ ርህራሄ ዘርዝሯል››፡፡ ይሁን እንጂ በመሬት ጉዳይ ላይ በካፒታል ፈጠራና ክምችት፣ በሀብት ክፍፍልና በሌሎች ችግሮች ላይ የሚታዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች በመሠረታዊነት የፖለቲካ ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል፡፡
አቶ መላኩ አያይዘው እንደተናገሩት፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገቡና ለውጦች መታየታቸው ማይካድም፣ ዕድገቱ ግን ከዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ይነሳ የነበረ ከመሆኑ አኳያ ትንሹ ለውጥ እንደ ጉልህ እንዲታይ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲታዩ ነበር፡፡ በተለይም የኢኮኖሚው የዕድገት ስሌት መነሻ የተደረገበት ዓመት (ሪቤዝ) በተቀየረ ጊዜ አሁን የሚባለውና ወደፊት ሊታይ የሚችለው ጉዳይ ላይ ክፍተት ሊመጣ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
‹‹ሪፎርሙን ለማስፈጸም ትልቅ የሀብት ምንጭ ይጠይቃል፡፡ የሀብት ምንጩ ምንድን ነው፣ ከየት ነው?›› በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከወዲሁ የውጭ ብድር ማስፈለጉ እንደማይቀር ይህም ለሕዝብ በአግባቡ መገለጽ እንደሚያስፈልገው ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በርካታ የብድር ዕዳ ስላለብን ብድር መውሰድ አቁመናል ካላችሁ በኋላ ተመልሳችሁ ወደ ብድር ገብታችኋል የሚል ጥያቄ እንዳመጣ በማሻሻያ ሰነዱ ውስጥ የገንዘብ ምንጩ ይገለጽ፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
የሪፎርሙ ውጤታማ መሆን ጉዳይ አሳሳቢ የህልውና ጉዳይ እንደሆነም ጠንከር አድርገው በአጽንኦት ማሳሰቢያ ሰጥተውበታል፡፡ ‹‹የሪፎርም አጀንዳው የመኖር ጉዳይ፣ ለህልውና የሚደረግ ጉዞ፤›› በመሆኑ ይታሰብበት ብለዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል የግብርና ሀብት ቢሮም የመሬት ጉዳይ አሳሳቢ ስለመሆኑ አንስቷል፡፡ የክልሉ ኃላፊዎች እንዳወሱት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መሠረት፣ ከ5,000 ሔክታር በላይ መሬት የፌዴራል ኃላፊነት ነው በሚለው አሠራር ሰፋፊ መሬቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እየተሰጡ፣ ‹‹አገር አጥፊ ጥፋቶች›› መከሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት አካላት በማያገባቸው የክልል ጉዳይ እየገቡ ችግሮች ተፈጥረዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የአገር ኢኮኖሚና ሀብት ኪሳራ ላይ ወድቋል ያሉት ኃላፊዎቹ፣ እንዲህ ያሉት አጥፊ አሠራሮችም በሪፎርሙ ይታዩልን፣ ይስተካከሉልን ብለዋል፡፡
ይህም ይባል እንጂ፣ በመሬት ጉዳይ ላይ የቀረቡት የማስተካከያና የማሻሻያ ጥያቄዎች የመሬት ፖሊሲው በምን አግባብ መቀየር እንዳለበት በግልጽ አላመላከቱም፡፡ ባለፈው ሳምንት ከፋይናንስ ዘርፉ ተዋንያን ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት፣ መሬት የመንግሥት መሆኑ ቀርቶ የግል ሀብት ይሁን የሚሉትን ጨምሮ የመሬት አጠቃቀም መብቶችና አፈጻጸሞች እንዲቀየሩ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
ከዚህ ባሻገር ከክልል ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይጥ ግብርናን የሚመለከቱ ጥያቄዎችም ተብላልተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አህመድ ቱሳ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በሚካሄዱ ጥናቶችና ግምገማዎች ችግሮች ተለይተው ቢጡም ተግባር ላይ ሲውሉ እንደማይታዩ አስታውሰዋል፡፡ ተለይተው የወጡ ችግሮች ተፈጻሚነት ላይ ማነቆ አለባቸው ያሉት አቶ አህመድ፣ በሪፎርሙ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው ይልቅ ያልተማከለ አካሄድ እንዲኖረውና አካሄዱም እንዲፈተሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
አቶ አህመድ ባነሱት ሐሳብ መሠረት፣ እስካሁን ባለው አካሄድ በዋና ሸቀጦችና ወሳኝ በሚባሉ ምርቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት በኢትዮጵያ ያለው አደረጃጀት መለወጥ አለበት፡፡ ለውጥ እንዲመጣ ‹‹ብሔራዊ ፕሮግራም›› ያስፈልጋል ያሉት አቶ አህመድ፣ በተለይ ቡና፣ ስንዴ፣ ሰሊጥና መሰል ወሳኝ የወጪ ንግድ ሸቀጦችና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ የግብርና ውጤቶች ላይ ፈጣን የምርታማነት ለውጥ ለማምጣት፣ በፌደራል መንግሥት የሚመሩ የአጭር ጊዜ አገር አቀፍ ፕሮግራሞች በማሻሻያ ፕሮግራሙ መካተት እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡
በመንግሥት ሲሰጡ የቆዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችም በተወያዮቹ ተደጋግመው ተነስተዋል፡፡ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ስለዚሁ ጉዳይ በማንሳት ለውጦች እንደሚደረጉ፣ መንግሥት የሚሰጣቸው ማበረታቻዎች ከዚህ ቀደም እንደነበረው እንዲሁ በዝርዑ የሚቀርቡ ሳይሆኑ፣ ለምን ተግባርና እንዴት እንደዋሉ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ የረባ ሻይ ቤት በሌለት አነስተኛ መንደር ውስጥ ሳይቀር ከ50 በላይ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ለመገንባት እየተባለ ከቀረጥ ነፃ ብረት ያለ ልክ እየገባ፣ መዳረሻው ግን መርካቶ እንደነበር ባለፈው ሳምንት በተደረገ ውይይት ወቅት መነሳቱን ጭምር በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡
እሳቸው ይህን ቢሉም ተወያዮቹም ደጋግመው ለአጽንኦት ሐሳባቸውን ሰጥተውባቸዋል፡፡ አቶ አህመድ በዚህ ሐሳብ ላይ እንደተናገሩት፣ ሙሰኞችና አጭበርባሪዎችን ለመከላከል መንግሥት በሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት ማበረታዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ሆኖ እጥረት ባለበት ወቅት የሚደረገው ቁጥጥርም ለሙስና በር ከፋች በመሆኑ በዚህ መስክም ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በፋይናንስ አቅርቦት ላይ በተለይ የገጠሩን ክፍለ ኢኮኖሚ በሚመለከት በማሻሻያ ፕሮግራሙ የቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች በአብዛኛው የተለመዱና ከዚህ ቀደምም የነበሩ በመሆናቸው፣ ለግብርናው ዘርፍ ብሎም ለገጠር ልማት የሚውለው የፋይናንስ አቅርቦት ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው አቶ አህመድ ጠይዋል፡፡
የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ርስቱ ይርዳውም ግብርናውም በሚመለከት ባቀረቡት ጥያቄ፣ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ክልሎች ያለሟቸዋል ተብለው ለክልሎች እየተተዉ፣ ክልሎችም የማስፈጸሚያ ሀብትና አቅም በማጣት እንዳልተገበሯቸው፣ እሳቸው የሚመሩት ክልልም በዚህ ምክንያት የተጠኑ የመስኖ ጥናቶች እንዲሁ መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዝርዝር ዕቅድ ሲዘጋጅ ትኩረት እንዲሰጥበት አሳስበዋል፡፡
የመሠረተልማት መጓደል ሰፊ በመሆኑ በደቡብ ክልል በርካታ የግብርና ሀብት እያላቸው ነገር ግን በመንገድና በሌሎችም መሠረተልማት አውታሮች ዕጦት ከገበያ ጋር መገናኘት ያልቻሉ አካባቢዎች ምርቶቻቸው ከዕለት ፍጆታ ማለፍ እንዳልቻሉ፣ ፍራፍሬዎችና ሌሎችም ምርቶች እየተጣሉ እንደሚገኙ በመግለጽ አምራቹና ገበያ የሚገናኙባቸው መሠረተልማቶች እንዲስፋፉ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም የፋይናንስና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሮችም እንዲፈተሹ ያሳሰቡት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት፣ ‹‹የኢኮኖሚ ችግር የሰለም እጦት፣ የሰላም እጦትም የኢኮኖሚ ችግር መንስዔዎች ናቸው›› በማለት ክልሎች ኃያላቸውን ኃይል ሁሉ በልማት ላይ እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡
የአፋር፣ የሰማሌ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ተወካዮችም በጠረፍ ንግድ ላይ በተለይም ከዚህ ቀደም ይተገበር የነበረውና አሁን የታገደው የፍራንኮ ቫሎታ ሥርዓትን ጨምሮ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የውኃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ጉዳይ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ትኩረት ያስፈልጋቸዋል በማለት ጠይቀዋል፡፡ አፋር በኦሮሚያ ክልሎች በክረምቱ ወራት ተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ በጥያቄ ቀርቧል፡፡ የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች፣ በበጋው ወራት ውኃ እያጡ፣ ውኃ በማይፈልጉበት በክረምቱ ወራት ግን የጎርፍ አደጋ እያጋጠማቸው አምራቾች ለተረጂነት ሲዳረጉ እንደሚታዩ ተነስቷል፡፡ ይህም የውኃ ሀብትን በአግባቡ ካለመጠቀምና ካለማስተዳደር የሚከሰት በመሆኑ፣ እንዲሁም ግድቦችን በሚገባ ካለመጠቀም የሚመጭም ችግር ስለሆነ በማሻሻያው ይታይ ተብሏል፡፡ በማድን ዘርፍም መንግሥት ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባዋል የተባሉ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ በአፋር ክልል በተለይ ከፖታሽ ማዕድን ጋር በተያያዘ የካሳ ክፍያና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች በትኩረት እንዲታዩ የሚሉ ጥያቄዎች ተደምጠዋል፡፡
እንዲህ ላሉት ሐሳቦችና ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ (ዶ/ር) በተመረጡት ላይ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡ የሀብት ምንጩ ይገለጽ ለሚለው የአቶ መላኩ ጥያቄ፣ አቶ አህመድም ሆኖ ምክትላቸው እንዳሉት፣ መንግሥት አሁንም ቢሆን የውጭ ብድርና ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው አረጋግጠዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ሲገልጹም፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማስፈጸም ከውጭ የሚያስፈልገውን ሀብት በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ቡድን እየሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በሦስት ዓመታት ውስጥ ለሚተገበረው ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ከ10 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ሲገለጽ ቢቆይም፣ ኢዮብ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ መንግሥት በፋይናንስ ረገድ ይህን ያህል ያስፈልገኛል አላለም፡፡ ‹‹የሚፈለገው ሀብት ከዚህ ያነሰም የበለጠም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ገንዘቡን ከአገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ምንጮች ማፈላለጉና ማግኘቱ ችግር አይሆንብንም፤›› ብለዋል፡፡