Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሶቹ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥዎች በአማካሪዎች እንደሚታገዙ ተገለጸ  

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አደረጃጀቱን ማሻሻል፣ አቅሙንም ማጎልበት እንደሚጠበቅበት በተደጋጋሚ ሲገለጽ ከርሟል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎችን በአግባቡ ተንትኖ የወደፊት አካሄዳቸውን ለማሳለጥ በብሔራዊ ባንክ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ ወሳኝ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡

ባንኩ በአዲስ ገዥ እንዲመራ ሲወሰንም፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን በማሻሻል የተሻለ ለውጥ እንዲያመጣ ታምኖበት እንደሆነ፣ የባንኩን አደረጃጀትና አወቃቀር ማስተካከልም የሪፎርሙ አካል ስለመሆኑ ሲነገር ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚህ አኳያ እስካሁን የተሠራውም የተፈጸመውም የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ የሚገልጹ ቢኖሩም፣ ባንኩ በአንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ሥራዎችን እንደተወጣ ይገለጻል፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ማነቆ የነበሩ አዋጆችና መመርዎችን አሻሽሏል፡፡ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማትን የሚመለከቱ አዋጆችን አሻሽሎ፣ አንዱን አዋጅ ቀይሮና 20 መመርያዎችን አሻሽሎ የመጣባቸውን መንገዶች ብሔራዊ ባንክ በአብነት ያነሳቸዋል፡፡

ይህም ሆኖ ብሔራዊ ባንክ የሚጠበቅበትን ያህል መሥራት እንዲችልና አቅሙን ለማጎልበት በብቁ ባለሙያዎች መደራጀት አለበት የሚለው አስተያየት ጎልቶ ይደመጣል፡፡ ባለሙያዎች የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት፣ ባንኩ ወቅቱና የመጪውን ጊዜ ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ በመተንተን መፍትሔ ሰጪ ፖሊሲዎችን የሚቀርፁ ባለሙያዎች ያስፈልጉታል፡፡ አጠቃላይ መዋቅራዊ ማሻሻያ ማድረግ አለበት በሚባልበት ወቅት እንኳ በምክትል ገዥነት ባንኩን የሚመሩ ኃላፊዎች ሳይሾሙለት መቆየቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ለዚህ የኃላፊነት ቦታ ዓለም አቀፋዊ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ይመደባሉ ተብሎም ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክን በምክትል ገዥነት የሚመሩ ኃላፊዎችን ለመሾም ከአገር ውጭ የሚኖሩ ወይም የውጭ ባለሙያዎችን የማፈላለግ ሥራዎች ሲሠሩ ቢቆዩም፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የታየው ግን ይህ ሐሳብ እንደተቀየረ ነው፡፡ በባንኩ መካከለኛ የአመራርነት ዕርከን ሲያገለግሉ የቆዩ ባለሙያዎች ሦስት ቁልፍ የተባሉ የምክትል ገዥነት ቦታዎችን እንዲረከቡ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ቀደም በምክትል ገዥነትና በዋና የኢኮኖሚ ባለሙያነት ቦታውን ይዘው ይመሩ የነበሩት ኃላፊዎች መነሳታቸውን ተከትሎ ቦታው ክፍቱን ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ ግን አዳዲስ ምክትል ገዥዎች ተሰይመዋል፡፡ የባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዳዲሶቹን ምክትል ገዥዎች በባንኩ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው ሲሠሩ የነበሩና የተጀመረውን ሪፎርም ዳር ለማድረስ እንደሚችሉ ስለታመነባቸው ነው፡፡  

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት አዳዲሶቹ ምክትል ገዥዎች አቶ ሰለሞን ደስታ፣ አቶ እዮብ ገብረ ኢየሱስና አቶ ፍቃዱ ደግፌ ናቸው፡፡ አዲሶቹን ምክትል ገዥዎች ለኃላፊነት በማጨት ረገድ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሚና እንደነበራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ገዥው ለሪፖርተር ከሰጡት ገለጻ መረዳት እንደተቻለውም፣ በውስጥ አቅም የባንኩን ሪፎርም ዕውን ለማድረግ በባንኩ የካበተ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ለሹመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ አቅርበዋቸዋል፡፡ አዲሶቹ ተሿሚዎች በባንኩ በተለያዩ የኃላፊነት ከ15 ዓመታት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው ውጤታማ ሥራ እንደሚሠሩ እምነታቸው መሆኑን ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ የባንኩን ቁልፍ ኃላፊነት እንደሆነ የሚነገርለትን የምክትል ገዥነትና የዋና የኢኮኖሚ ባለሙያነት ቦታ የሚሾምበት ኃላፊ በመጥፋቱ ለአንድ ዓመት ክፍቱን መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የዚህን ያህል ጊዜ ክፍቱን ለመቆየቱ ሲጠቀስ የነበረውም ባለሙያዎች እየተፈለጉ የሚለው ምክንያት ነበር፡፡

በተለይም የዋና ኢኮኖሚ ባለሙያና ምክትል ገዥነት ቦታውን ደርቦ የሚይዝ ተሿሚ በወቅቱ አለመሰየሙ ለምን? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ በአንድ ወቅት ይናገር (ዶ/ር) ሲያብራሩ፣ በምክትል ገዥነት ቦታው ላይ በወቅቱ ኃላፊ ያልተሾመው፣ ባንኩ ከሚያካሂደው የሪፎርም እንቅስቃሴ፣ ሊተገበርባቸው ካሰባቸው አዳዲስ አሠራሮች አኳያ በተለይ እንደ ካፒታል ገበያ ያሉትን ሥራዎች ታሳቢ በማድረግ፣ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ልምድ ያለው ባለሙያ እንዲመደብ ታስቦ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አሁን ግን በምክትል ገዥነት ቦታዎች ላይ ባንኩ የራሱን ባለሙያዎች ከታች ማሳደጉ የቀድሞውን ሐሳቡን እንደቀየረ ያሳያል፡፡ ይናገር (ዶ/ር) ግን ለዚህ ምላሽ አላቸው፡፡ የታሰበውን ለመሥራትና ከዓለም አቀፍ ልምድ አንፃር አስፈላጊውን ሙያዊ ዕገዛ የሚያደርጉ የውጭ ባለሙያዎች የተካተቱበት አማካሪ ቡድን በመዋቀሩ፣ ለባንኩ የዕለት ተዕለት ሥራ የውጭ ባለሙያ የመቅጠር ሐሳቡን በመቀየር ክፍተቱ እንደተሸፈነ አብራርተዋል፡፡

የተዋቀረው የቴክኒክ አማካሪ ቡድን የባንኩን አመራርና ባንኩ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማገዝ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ልምዶችንና አሠራሮችን በመጠቀም የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ተብሏል፡፡ የውጭ ባለሙያዎችን ያካተተው ይህ አማካሪ ቡድኑ፣ ባንኩ የሚፈልጋቸውን ለውጦችና ማሻሻያዎች ብሎም አዳዲስ ሥራዎች ተግባር ላይ ለማዋል አቅሙና ችሎታው ያላቸው ባለሙያዎችን እንዳካተተ ተጠቅሷል፡፡ በአማካሪ ቡድኑ ውስጥ የተካተቱንና ዋና ባለሙያ የሚባሉትን አማካሪዎች ወጪ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የአፍሪካ ልማት ባንክ ይሸፍናሉ ተብሏል፡፡ በቅርቡ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምት መሠረት፣ ውጤታማ የሪፎርም ሥራ ለመሥራት ባንኩን እንደሚያግዙት ተገልጿል፡፡ በመሆኑም የምክትል ገዥዎቹ ሹመት ሪፎርሙን ለመተግበር ከአማካሪው ቡድን ጋር ሆነው እንደሚሠሩ ገዥ ይናገር (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉን ማሻሻያዎች ትግበራ ለማሳካት ብሔራዊ ባንክን የሚያግዙ አማካሪዎችን መጠቀሙ በተለያየ መልኩ ጠቃሚ እንደሆነ የውስጥ አቅሙን መሠረት በማድረግም ሦስቱ ምክትል ገዥዎችም በዚሁ ሥሌት የባንኩን ቋሚ የኃላፊነት ቦታዎች እንዲረከቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡  

ከገዥው ገለጻ መረዳት እንደተቻለው አዲሶቹ ተሿሚዎችና አማካሪ ቡድኑ ባንኩን በሚገባ አደራጅተውና አጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጡን ለማስፈጸም የሚረዱ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ታምኖባቸዋል፡፡ በመሆኑም የምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት በመሆን የተሰየሙት አቶ ፍቃዱ ደግፌ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴውን ይመራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ የገንዘብና የፋይናንስ ትንታኔዎችን የሚሠራውን ዳይሬክቶሬት፣ የኢኮኖሚ ሞዴልና የፖሊሲ ትንተና ዳይሬክቶሬትን የውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬትንና የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር፣ የመጠባበቂያ ክምችትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬትን ይመራሉ፡፡

የፋይናንስ ሥርዓቱን በተረጋጋ መንገድ እንዲመራ በማስተባበርና አመራር በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የተመደቡት ምክትል ገዥ አቶ ሰሎሞን ደስታ፣ በሥራቸው የሚመሯቸው ኃላፊነቶች፣ የባንክ ሱፐር ቪዥን፣ የኢንሹራንስ ሱፐር ቪዥን፣ የማክሮ ፋይናንስ ሱፐር ቪዥንና የመገበያያ ገንዘብ ማኔጅመንት፣ የክፍያ ሥርዓትን የሚመራው ዳይሬክቶሬትም በእኚሁ ምክትል ገዥ ሥር ይካተታል፡፡  

የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ገዥ በመሆን የተሾሙት አቶ ኢዮብ ገብረ ኢየሱስ የሚያስተዳድሯቸው ዳይሬክቶሬቶች ስድስት ሲሆኑ፣ የኮርፖሬት ፕላንና ፋይናንስ፣ እንዲሁም የሰው ኃይል ልማት ዳይሬክቶሬቶች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ የኢንፎርሜሽንና የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬቶችም በእሳቸው ኃላፊነት ሥር ይካተታሉ፡፡  

የቀድሞ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ በምትካቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በቦታው ተሰይመው ነበር፡፡ ለጥቂት ወራት ከሠሩ በኋላ መልቀቂያ በማስገባት የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ፣ በኋላም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናናን በመተካት ከጡረታ ተመልሰው በቦታው ተሾመው የነበሩት አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ ይመሩት የነበረውን ቦታ ለአቶ ሰለሞን ደስታ ለቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች