Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ሁለተኛውን ወለድ አልባ ቅርንጫፍ ከፈተ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዳያስፖራው ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ ሥራ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወለድ አልባ የባንክ አልግሎት ብቻ ለይተው የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን ለማስፋፋት በያዘው ዕቅድ መሠረት ሁለተኛውን ወለድ አልባ ቅርንጫፍ ሥራ እንደሚያስጀምር አስታወቀ፡፡ የመጀመሪያውና ዳያስፖራዎች ብቻ የሚጠቀሙበት ቅርንጫፍም አገልግሎት ጀምሯል፡፡

የሸሪዓ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ወለድ አልባ ባንክ ለመክፈት፣ አደራጆች አክሲዮን እየሸጡ በሚገኙበት ወቅት፣ ንግድ ባንክ በበኩሉ ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁለተኛ ቅርንጫፉን በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ፣ ከረቡዕ መስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ያደርጋል ተብሏል፡፡ ባንኩ የመጀመርያውን የወለድ አልባ አገልግሎት ቅርንጫፍ፣ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ‹‹ቢላል ቅርንጫፍ›› በሚል መጠሪያ መክፈቱ ይታወሳል፡፡

ንግድ ባንክ ወለድ አልባ አገልግሎቱን ለማስፋፋት በያዘው ዕቅድ መሠረት፣ በዚህ ዓመት ብቻ 54 ወለድ አልባ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችን በመላው ኢትዮጵያ ለመክፈት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ንግድ ባንክ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎትን ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት ትይዩ እየቀረበ ቢሆንም፣ ራሳቸውን የቻሉና የተሻለ ወለድ አልባ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ቅርንጫፎችን በመክፈት ገበያውን ለማስፋፋት እየሠራ ነው፡፡

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ 11 ባንኮች መካከል በመስኩ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበው ንግድ ባንክ፣ ከወለድ አልባ የባንክ አገለግሎት በርካታ ቁጠባ በማሰባሰብ ሰፊውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ በቅቷል፡፡ በዚህ ረገድ የሚታየው የባንኩ እንቅስቃሴ፣ በምሥረታ ላይ የሚገኙ ወለድ አልባ ባንኮችን ሊገዳደራቸው እንደሚችል የሚጠቁሙ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ ራሱን የቻለ ወለድ አልባ ባንክ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በማሟላትና በሸሪዓ ሕግ መሠረት መፈጸም ያለባቸውን መሥፈርቶችም በማሟላት ቅርንጫፎቹን የማስፋፋቱ ሥራም ትልቁን ገበያ የመውሰድ ዕድሉን እንዳሰፋለት የሚገለጹም አሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ወለድ አልባ አገልግሎት ለመስጠት ሰባት ባንኮች የምሥረታ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ የአክሲዮን ሽያጭ እንደጀመሩም ይታወቃል፡፡ የወለድ አልባ አገልግሎት በኢትዮጵያ ሲጀመር፣ በመደበኛ ባንኮች መስኮት፣ በቅርንጫፍ ባንኮች ደረጃ ከዚያም በአሁኑ ወቅት ራሱን የቻለ ባንክ እንዲመሠረት ምክንያት እንደሆነ የሚጠቀሰው፣ ዘምዘም ባንክ (በምሥረታ ላይ ይገኛል) ቀዳሚው ወለድ አልባ ባንክ ለመሆን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ንግድ ባንክ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚገለገሉበትን ቅርንጫፍ ባንክ በመክፈት ሥራ ማስጀመሩ ታውቋል፡፡ ባንኩ ለገሐር አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሕንፃ ሥር ‹‹ዳያስፖራ ቅርንጫፍ›› በማለት የሰየመውን ቅርንጫፍ ዓርብ፣ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፣ የቅርንጫፉ ዋነኛ አገልግሎትም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቹን ማስተናገድ ላይ ብቻ እንደሚያተኩር ታውቋል፡፡ ሌሎች የባንኩ ደንበኞች አይስተናገዱበትም፡፡  

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹት፣ ባንኩ ለዳያስፖራ ማኅበረሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያቀረበ ሲሆን፣ ለዳያስፖራው ተደራሽ ለመሆን በማሰብ አዲሱን ቅርንጫፍ ከፍቷል፡፡  

ባንኩ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ የሚሳትፍባቸው የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቀርጾ ሥራ ላይ ማዋል የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ በቅርቡ ትግበራ እንደሚጀምር የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህ ማሳያው ሥራ የጀመረው የዳያስፖራ ቅርንጫፍ የጥረቱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዳያስፖራ ባንኩ፣ ለደንበኞቹ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ለወጪና ገቢ ንግድ ማንቀሳቀሻ፣ ለታላላቅ የልማት ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማሰባሰብ እንደሚያግዝም አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም የቁጠባ አገልግሎቶች፣ የቤት መሥሪያና መግዣ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎቶች የሚስተናዱበት ሲሆን፣ በተጨማሪም ለዳያስፖራው የኢንቨስትመንት አማራጮች እንደሚቀርቡበት ተብራርቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ዳያስፖራው የባንኩን አገልግሎቶች ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ የቁጠባ ሒሳብ መክፈት የሚችሉበት፣ በአካል መቅረብ የማይችሉትም በሚኖሩበት አገር በሚገኝ ኤምባሲ ወይም ቆንፅላ ጽሕፈት ቤት ሒሳብ እንዲከፍቱ የሚያስችል ዕድል ማመቻቸቱን አቶ ጊና አስታውሰዋል፡፡

በቅርንጫፉ ሥራ በጀመረበት ምረቃ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፣ ንግድ ባንክ ለዳያስፖራዎች የሚያገለግል ቅርንጫፍ መክፈቱ፣ ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ዕድል ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 432/2011 መሠረት ባለፈው ዓመት ከተቋቋመ ጀምሮ የተፈጠረውን ለውጥና ዳያስፖራው በአገሩ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ እያሳየ ያለውን መነሳሳት ወደ ሥራ ለመለወጥና ለማሳደግ የሚረዱ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች