Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ260 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ የተሸከሙ የልማት ድርጅቶች ትርፍና ኪሳራ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አትራፊ ሲሆን ሜቴክ በከፍተኛ ኪሳራ ይመራል 

ግዙፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ 23 የልማት ድርጅቶች በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር እንዲተዳደሩ ከተደረገ አንድ ዓመት ገደማ ሆኗል፡፡ እንደ አዲስ በተመሠረተው በዚህ ኤጀንሲ ሥር የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ይተዳደራሉ፡፡

ከእነዚህ ባሻገር የተለያዩ ፕሮጀክቶችንና ኩባንያዎችን በሥራቸው በማካተት ከሚንቀሳቀሱት ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ያሉ ተቋማትም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር ተካተዋል፡፡

በሆቴል ዘርፍም አንጋፋው አዲስ አበባ ሒልተና ግዮን ሆቴሎች ከ23ቱ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የልማት ድርጅቶቹ በጠቅላላው ከትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት አላቸው፡፡ የልማት ድርጅቶቹን የ2011 ዓ.ም. አፈጻጸም በተመለከተ ሐሙስ፣ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከ23 የልማት ድርጅቶች ውስጥ 18ቱ አትራፊ በመሆን ዓመቱን ተሻግረዋል፡፡ የተቀሩት አምስት ኩባንያዎች በኪሳራ ደምድመዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል እንደገለጹት፣ 18ቱ ድርጅቶች ከታክስ በፊት በጠቅላላው 52.3 ቢሊዮን ብር አትርፈዋል፡፡ አምስቱ ድርጅቶችም የ3.9 ቢሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግበዋል፡፡ ድርጅቶቹ ከታክስ በፊት እንደሚያስገኙ ይጠበቅ የነበረው ትርፍ 69.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አፈጻጸማቸው 77 በመቶ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ እንዲያስገኙ የታቀደው የገቢ መጠንም 311.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር፣ በተጨባጭ ያገኙት ግን 258.5 ቢሊዮን ብር በመሆኑ የዕቅዳቸውን 83 በመቶ እንዳሳኩ ተብራርቷል፡፡ ከሽያጭና ከአገልግሎት እንደሚያኙ የታሰበው ገቢ ከአፈጻጸሙ አንፃር ሲታይ በ53.5 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን ያመለክታል፡፡ ከዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ የልማት ድርጅቶቹ ካስመዘገቡት ትርፍ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተገኘ ነው፡፡

ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ በቀዳሚነት የሚቀመጠው ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በ2011 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 24.5 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ በተሸኘው ዓመት በኤጀንሲው ሥር እንዲካተት የተደረገው ንግድ ባንክም ከታክስ በፊት 17.9 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከታክስ በፊት 8.9 ቢሊዮን ብር፣ የባህር ትራንስፖትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 1.7 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸው ታውቋል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ የልማት ድርጅቶችም ከትርፉ ተቋዳሽ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ ግዮን ሆቴሎች ድርጅትና የፍል ውኃ አገልግሎት ድርጅት በጠቅላላው የ134.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግበዋል፡፡ ሦስቱ የልማት ድርጅቶች የሽያጭና የአገልግሎት ገቢያቸው 683.5 እንደነበርም ታውቋል፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት 198.5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች 324 ሚሊዮን ብር በማትረፍ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከልማት ድርጀቶቹ ሁሉ ከዕቅድ በላይ በማትረፍ የሚጠቀሰው አልኮል አምራቹ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ነው፡፡ ፋብሪካው ከታቀደለት በላይ ማትረፉ ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም ከዕጥፍ በላይ በማደጉ የተለየ አድርጎታል፡፡ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በ2011 ዓ.ም. ከታክስ በፊት እንዲያተርፍ የታቀደው 200.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ሆኖም በዓመቱ መጨረሻ  ያገኘው ትርፍ ከዕቅዱ በላይ የ16 በመቶ ብልጫ በማሳየት 233.4 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የድርጅቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትም፣ በ2011 ዓ.ም. ለውጭ ገበያ ከቀረበው ምርት አኳያ የታቀደው 202 ሺሕ ዶላር ገቢ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ግን 464,993 ዶላር በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ከዕቅዱ በላይ በ230 በመቶ ከፍ አድርጎታል፡፡

በገቢ ረገድ በትርፍም ጭምር ትልቅ ውጤት ያስገኙት እንዳሉ ሆነው 2011 ዓ.ም.ን በኪሳራ ካጠናቀቁ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ልማት ባንክንና ሜቴክን የሚስተካከላቸው የለም፡፡ አቶ በየነ እንዳስታወቁት፣ እነዚህን ጨምሮ አምስት የልማት ድርጅቶች የ3.9 ቢሊዮን ኪሳራ አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡ ኃላፊው ይህን ቢገልጹም እያንዳንዱ ድርጅት ስላስመገዘበው ኪሳራ መጠን በዝርዝር አልጠቀሱም፡፡

ሆኖም ኤጀንሲው ሰሞኑን በተከታታይ ካካሄዳቸው ግምገማዎች፣ ከከሰሩት የልማት ድርጅቶች መካከል ልማት ባንክና ሜቴክ ዋነኞቹ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በኪሳራ የተመዘገቡት ሌሎች ሦስት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ማዕድን፣  ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማኅበር እንዲሁም ሸበሌ ትራንስፖርት ድርጅት ናቸው፡፡ ልማት ባንክ ያስመዘገበው ኪሳራ 768.79 ሚሊዮን ብር እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ የልማት ባንክ የ2011 ዓ.ም. አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት፣ በ2011 ዓ.ም. እንዲያተርፍ የታቀደው 887.8 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ 768.8 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቧል፡፡ በዚህም በኤጀንሲው ሥር ከሚገኙት ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ ኪሳራ በማስመዝገብ ከዋና ዋናዎቹ ተርታ ተሰልፏል፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪውም ብቸኛው የከሰረ ተቋም በመሆን ይጠቀሳል፡፡

የሜቴክ ኪሳራ ከልማት ባንክም የላቀ ነው፡፡ ሜቴክ በገባበት ቀውስ የተነሳ ኪሳራ ማስመዝገቡ አይቀሬ እንደነበር ቀድሞውንም ተገምቷል፡፡ የሜቴክን የ2011 ዓ.ም. አፈጻጸም የሚያመለክቱ መረጃዎች፣ ድርጅቱም በራሱ ይፋ ካደረገው መረጃ እንደተረጋገጠው የ1.7 ቢሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቧል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ጅምሮው 2.3 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ ቢነሳም፣ ዕቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች እንደ ሥራ ባህሪያቸው የተለያየ አፈጻጸም ቢያስመዘግቡም፣ ከፍተኛ የብድር መጠን ከአገር ውስጥና ከውጭ አበዳሪዎች አከማችተዋል፡፡ ከፍተኛ የብድር ዕዳ ካለባቸው ተቋማት መካከል በርካቶቹ በኤጀንሲው ሥር ይገኛሉ፡፡ አቶ በየነ እንደገለጹትም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሳይጨምር 22ቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በጠቅላላው የ110 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር ዕዳና የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ አለባቸው (የውጭ ዕዳቸው በወቅቱ የምንዛሪ ዋጋ ሲተመን ከ155 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል)፡፡

የልማት ድርጅቶቹ በአግባቡ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ በርካታ ጥረቶች አድርገውና የተሻሉ አሠራሮች ተዘርግተው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አቶ በየነ ይናገራሉ፡፡ በፋይናንስ አስተዳደርና በብድር አመላለስ ክፍተት የታየባቸው ታይተው፣ በ2011 ዓ.ም. የዕዳ አከፋፈል ሒደቱ በዕቅድ እንዲካሄድ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት በ2011 ዓ.ም. ከአገር ውስጥ ከተበደሩት ውስጥ 14.2 ቢሊዮን ብር ለብድር ዕዳ መክፈላቸው ሲገለጽ፣ ለውጭ አበዳሪዎችም 338 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንደተከፈለ አቶ በየነ አስታውቀዋል፡፡ የብድር አከፋፈሉ በበጀት ዓመቱ እንዲከፈል ከተያዘው ዕቅድ አንፃር  ሙሉ ለሙሉ በተቀመጠው መሠረት አልተከናወነም ያሉት አቶ በየነ፣ ከውጭ ዕዳ ውስጥ መክፈል የተቻለው በዕቅድ ከተያዘው 64 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ በዚህ ዓመት የሚተገብሯቸው ዕቅዶች ማከናወን መጀመራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ዘመናዊ አሠራር እንዲከተሉ ለማድረግ የሚያግዙ መመርያዎች ተሰናድተው ለትግበራ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

ከፋይናንስ አጠቃቀም አኳያ ድርጅቶቹ ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ዓለም አቀፉን የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ እንዲሁም የኦዲት ሥርዓትን እንዲተገብሩ እየተደረገ ነው፡፡ እስካሁን የነበራቸውን ሒሳብ በአግባቡ ኦዲት የማድረጉ ሥራን በተመለከተም የበርካቶቹ ድርጅቶች 2010 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት መጠናቁ ታውቋል፡፡ ሌሎችም ድርጅቶቹን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚስችል ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን፣ ለዚህ የሚሆን ስትራቴጂ እንደተነደፈ አቶ በየነ አስታውሰዋል፡፡ የልማት ድርጅቶ በ2012 ዓ.ም. የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግቡ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ በዚህ መሠረት 23ቱም ድርጅቶች ፕሮጀክቶቻቸውን ለማስፈጸም፣ የማምረቻ መሣሪዎቻቸውን ለማሻሻልና ለመሳሰሉት ተግባራት በጠቅላላው 54.7 ቢሊዮን ብር የካፒታል ኢንቨስትመንት ያካሂዳሉ ተብሏል፡፡ ይህ የኢንቨስትመንት ወጪ ከድርጅቶቹ ገቢ እንዲሁም ከባንክ በሚገኝ ብድር እንደሚሸፈን አቶ በየነ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የልማት ድርጅቶቹ ዕዳቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ የሚያስችል አሠራር እንደተረዘጋ፣ ዕዳው ከዓመት ዓመት እየተንከባለለ እንዳይቀጥል ፕሮግራም ወጥቶ ድርጅቶቹ ዕዳቸውን የሚከፍሉበት ዕቅድ መዘጋጀቱን አቶ በየነ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በ2012 ዓ.ም. በኤጀንሲው ሥር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ማስገኘት የሚጠበቅባቸው የገቢ መጠንና ዕቅድና አጠቃላይ ትርፋቸው ይፋ ተደርጓል፡፡  

በመሆኑም በ2011 ዓ.ም. ከተቀመጠላቸው ግብ አኳያ ከ30 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው አፈጻጸም ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ 23ቱ የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ከአገልግሎትና ከሽያጭ እንዲያስገኙ የታሰበው ገቢ 338.1 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 70.9 ቢሊዮን ብር ያህል እንደሚያተርፉም ዕቅድ ተይዞላቸዋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከ2011 ዓ.ም. አኳያ በ34 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ በኤጀንሲው ሥር የሚተዳደሩት የልማት ድርጅቶች ከ171 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ ሲሆን፣ 82 በመቶዎቹ ቋሚ ሠራተኞች እንደሆኑ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች