Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እንደ ሆቴል ባለሙያ አገር በብራንድ ሆቴሎች ዕጦት ስትቸገር ማየት ያስጨንቃል›› አቶ ነዋይ ብርሃኑ፣ የካሊብራ ሆቴል አማካሪ ድርጅት መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር 

የካሊብራ ሆቴል አማካሪ ድርጅት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ በሒልተን ሆቴል የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ክፍል የሽያጭና ገበያ ዳይሬክተር፣ የሥራ አጋራቸው አቶ ዮናስ ሞገስ በምግብና መጠጥ ክፍል ኦፊሰርነትና ዳይሬክተርነት የሥራ ድርሻቸው ለአሥር ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በኢንዱስትሪው የሚታዩ ክፍተቶችን ለማቃለል ያስችላል ያሉትን የማማከር ሥራ ከጀመሩም አሥረኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል፡፡ በሆቴል ኢንቨስትመንት መስክ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች እንዲመጡ የሚያስችል ሥራ በመሥራት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 27 የሚደርሱ የሆቴል ፕሮጀክቶችን አፈራርመዋል፡፡ የእንግሊዙ ቤንች ኤቨንትስ ኩባንያም በአዲስ አበባ ለሦስት ጊዜያት ያህል የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም የተሰኘውን ስብሰባ እንዲያዘጋጅ በመወትወት፣ በማገዝና አብሮ በመሥራት ሲሳተፉ የቆዩት አቶ ነዋይ፣ በቅርቡም በእንግሊዝ የሚገኘው ግሎባል ብራንድ በተሰኘው መጽትሔት እሳቸውና ድርጅታቸው ለሽልማት መብቃታቸው ይታወሳል፡፡ ቤንች ኤቨንትስ ኩባንያም በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች እንዲስፋፉ ላደረጉት ጥረት የኩባንያው አምባሳደር ተብለው ተሸልመዋል፡፡  በሆቴል ኢንቨስትመንት መስክ ካሊብራ ኩባንያ እያከናወነ ስላለው እንቅስቃሴ፣ በዘርፉ ስለሚታየው ለውጥና ሌሎች ጉዳዮች ብርሃኑ ፈቃደ አቶ ነዋይ ብርሃኑን አነጋገሮ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡– ካሊብራ ሆቴል አማካሪና ቢዝነስ ድርጅት እንዴት ነበር አመሠራረቱ? እንዴት ነበር ወደ ሥራው የገባችሁት?

አቶ ነዋይ፡- ካሊብራ ከተመሠረተ አሥር ዓመታት ያስቆጠረ ድርጅት ነው፡፡ በሥራ ባልደረባዬ አቶ ዮናስ ሞገስና በእኔ የተከፈተ ድርጅት ሲሆን፣ ሁለታችንም በሒልተን ሆቴል በነበረን የሥራ ኃላፊነት ብዙ ልምድ አካብተናል፡፡ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የሆቴል ኢንቨስትመንት እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ ዓላማ በመያዝ የመሠረትነው ድርጅት ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንደ ልብ አለመኖራቸው በተለይ አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ ከተማና ከ120 በላይ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መገኛ ብትሆንም፣ ይህንን በሚገባ ሊያስተናግድ የሚችል የሆቴል አቅርቦት ብዙም አልነበረም፡፡ በዚህ ሳቢያ በርካታ ስብሰባዎችን ማስተናገድ ሳንችል ቆይተናል፡፡ ማይስ የተሰኘውን የስብሰባ፣ የኮንቬንሽንና የክንውኖች ዘርፍ እያጠናው ነበር፡፡ ሌዠር የተሰኘው የቱሪዝም ዘርፍ ማለትም ጎብኚዎች በራሳቸው አለያም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ለመዝናናት የሚመጡበት የቱሪዝም ዓይነት ነው፡፡ የቢዝነስ ተጓዦች አሉ፡፡ የመንግሥትና የዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ያተኮሩ ጎብኚዎችም አሉ፡፡ ሒልተን እያለን ነው እንዲህ ያሉ የኮርፖሬትና መሰል ከሆቴል ሥራ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በሚገባ ያወቅነውና የተማርነው፡፡ በአገር ደረጃ ያሉን ዕድሎች ምን ያህል ሰፊ እንደሆኑ ብናውቅም፣ መሠረተ ልማቱ ግን ብዙ ይቀረው ነበር፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ብቻም ሳይሆን፣ ደረጃውን የጠበቀ የስብሰባ ማዕከል እንኳ እንጥቀስ ብንል የነበረን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የአፍሪካ ኅብረት እንዳሁኑ አዲስና ሰፋፊ ይዞታዎች ኖረውት አልተገነባም ነበር፡፡ ስብሰባ ማካሔጃውም የለም፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልም እንደ ልብ የለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ክፍተት ላይ መሥራት እንደሚገባን አመንን፡፡ ክህሎቶቻችንንም በዚሁ በሆቴል ኢንዱስትሪ በመሆኑ ለሚታየው ችግር አንድ ነገር ማድረግ እንደምንችል እናስብ ነበር፡፡ በየዓመቱ አፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ይካሄዳል፡፡ በርካታ መሪዎች ይመጣሉ፡፡ እያንዳንዱ መሪ አብሮት እስከ 50 ልዑክ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ አንዳንዱም እስከ 300 አጃቢዎች ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ እነዚህን እንግዶች ሊያስተናግዱ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ብራንድ ሆቴሎች ሒልተንና ሸራተን ብቻ ነበሩ፡፡ ሒልተን 372፣ ሸራተን 292 ክፍሎች አሏቸው፡፡ በጠቅላላው ከ660 በላይ ክፍሎች ቢኖሩም ለእነዚህ እንግዶች እንኳ በቂ አልነበሩም፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያለውን ትተን በከተማው እንኳ በቂ ሆቴል አለመኖሩ ተጓዦች እንደ ልብ እንዳይስተናገዱ አስገድዷል፡፡ እርግጥ እኛ ስለብራንድ ሆቴሎች አወራን እንጂ፣ ራሳቸውን የቻሉ አገር በቀል ሆቴሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የውጭ እንግዶች የሚያውቋቸውና ዓለም ላይ የታወቁ ብራንድ ሆቴሎች ግን እንደ ልብ አልነበሩንም፡፡ ከሒልተን በኋላ ሸራተን እስኪመጣ 30 ዓመታት መጠበቅ ነበረብን፡፡ ይህ ለኢንዱስትሪው አይመችም፡፡ ስለዚህ እኛ ስንነሳ፣ በዓመት ቢያንስ አንድ ደረጃውን የጠበቀ ብራንድ ሆቴል እንዲከፈት ለማስቻል ነው፡፡ የሆቴል ዕድገት የጅምሩን ያህል ማደግ ሳይችል ቆይቷል፡፡ ሒልተን ሆቴል በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት ነበር የተከፈተው፡፡ በመንግሥት አቅም የተሠራ ነበር፡፡ ሌላ ብራንድ ሆቴል ግን አልመጣም፡፡ በደርግ ጊዜ ሌላ ሆቴል ጭራሽ አልታየም፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜም ቢሆን አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረውም፣ የግል ባለበሀብቶች በነፃ ገበያ እንደ ልብ እንዲሠሩ ተፈቅዶም አብዛኛው ትኩረት ግን በሌሎች ዘርፎች ላይ እንጂ ሆቴል ላይ አልነበረም፡፡ ባለሀብቶች የለመዱትና ምቾት የሰጣቸው የሥራ ዘርፍ ላይ ማተኮርን በመምረጣቸው ብራንድ ሆቴልን እንደ አዋጭ ቢዝነስ ገና አላዩትም ነበር፡፡ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑም ጭምር ብዙዎች ትኩረት አልሰጡትም፡፡ ይሁንና የታክስ እፎይታና የቀረጥ ነፃ ዕድሎች ሲሰጡ ግን ለውጦች መታየት ጀመሩ፡፡ ባለሀብቶች ሆቴል መገንባት ሲፈልጉ ደግሞ ማስተዳደሩ አሳሳቢ ሆነ፡፡ አገር ውስጥ ብራንድ ሆቴሎችን ሊያስተዳድር የሚችል አካል አለመኖሩ ችግር ነበር፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ እዚህ ላይ ነው የእናንተ ሚና መታየት የጀመረው?

አቶ ነዋይ፡- የእኛ ሚና መምጣት የጀመረው ከዚህ መነሻ ነው፡፡ እኔ በሒልተን ሳለሁ በሥራዬ አጋጣሚ የተማርኩት ጥሩ የንግድ ሥራ ከጥሩና መልካም ግንኙነት በመገንባት እንደሚጀምር ማወቄ ነው፡፡ በማይስ፣ በኮርፖሬት ገበያውና በሌላው መስክ ያለውን የገበያ ሁኔታ በማጥናት፣ ምን ያህል ክፍል እንደሚያስፈልግ ለእነዚህ አካላት በድርድር የዋጋ አማራጭ በመስጠት ከዓመት ዓመት የሥራ ዕድገት ያስገኘልን ውጤት አስመዘግብ ነበር፡፡ ከበርካታ ውሳኔ ሰጪዎች ጋር የምንገናኝበትን፣ ፍላጎቶቻቸውን የምናውቅበትን ዕድል የፈጠረልን የሥራ መስክ ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡– እስካሁን ከ20 በላይ የሆቴል ስምምነቶችን አደራድራችሁ አስፈርማችኋል፡፡ ለዚህ ውጤት ያበቃችሁ ምንድን ነው?

አቶ ነዋይ፡- የካሊብራ ስኬታማነት ትብብርና አብሮ መሥራት ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ ብራንድ ሆቴሎችን ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በማስማማት ማስከፈት ብቻውን ውጤታማ ያደርጋል የሚል እምነት የለንም፡፡ መነሻው ግን በመተማመንና በአቻ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ሥራና ውጤት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ሒልተን እያለን በመማራችንና ወሳኝ ከሚባሉ ዘርፉ ውሳኔ ሰጪዎች ጋር በመተዋወቃችን ጭምር ነው በሥራው ውስጥ ውጤታማ ያደረገን፡፡ ከዓመት ዓመት እናገኛቸውና ሥራችንን ያውቁ ስለነበር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መተማመን አዳብረን ነበር፡፡ ዕውቀቱና ልምዱ ያውቃሉ፡፡ ቀድሞም ግር በሚላቸው ጉዳይ ላይ መፍትሔ እያቀረብን እናግዛቸው እንደነበር በማየታቸው፣ ካሊብራን ከመሠረትን በኋላ በቀላሉ በእኛ ላይ እምነት እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡ ለዚህም ነው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለይ ለምንሰጣቸው ምክርና የሙያ ድጋፍ ዋጋ ይሰጡት ነበር፡፡ እንዲህ ባለው አካሔድ የጀረመው ሥራችን የመጀመርያውን ደንበኛ ያመጣልን ከዚሁ በአገር ውስጥ በሚተዳደር ብራንድ መንቀሳቀስ የፈለገውን ካፒታል ሆቴልን ነበር፡፡ የሆቴሉ ባለቤት ገና የሆቴል ግንባታውን የጀመሩ ሰሞን ነበር ወደ እኛ የመጡት፡፡ እንድናግዛቸው በጠየቁን መሠረት፣ ካፒታል ሆቴል ተከፍቶ ሥራ እስኪጀምርና ለውጤት እስኪበቃ ድረስ ያለውን ሒደት በሙሉ በማማከር አግዘናል፡፡ ባለሀብቶች ሥጋት አላቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎችን የሚመርጡበት አንዱ ምክንያት ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተውበት የገነቡትን ሆቴል በሚገባ የሚያስተዳድርላቸው የአገር ውስጥ ባለሙያ ከማጣት አንፃር ጭምር ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ብራንዶች የሚጠይቋቸው መሥፈርቶች ምን እንደሆኑ በሰፊው ስለማይታወቅም ጭምር ባለሀብቶች ደረጃቸውን የጠበቀ ሆቴል ለመክፈት ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ይኼንን ችግር ለመፍታት የእኛ ሚና ያስፈልግ ነበር፡፡ ሌላው ትልቅ ችግር ግን የሆቴል ባለሙያ የሚጋበዘው የሆቴል ቤቱ ግንባታ ካለቀ ወይም ብዙ ከሄደ በኋላ መሆኑ ነበር፡፡ እንደ ካሊብራ አንድ ሆቴል ሲገነባ ከተገነባበት አካባቢ ሁኔታና ሊኖረው ከሚገባው ደረጃና ተመራጭነት ብሎም ከዋጋ አኳያ ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ በሚገባ እያየን ከመጀመርያውኑ ባለሙያ መሳተፍ እንዳለበት እንመክራለን፡፡ በዓለም ተሞክሮ የአንድ ሆቴል ቤት ፊትና ጀርባው ወሳኝ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ የቤቱ ፊት ለፊት እንግዶች በብዛት የሚጠቀሙበት፣ የተፈቀደላቸው የሆቴሉ ሠራተኞች ብቻ እንግዶቹን ለማገልገል የሚታዩበት አካባቢ ነው፡፡ የሆቴል ጀርባ አካባቢ ሠራኞች አብዛኛውን ጊዜ ለሥራ የሚያውሉበት፣ እንግዶች የማይገቡበት ቦታ ነው፡፡ የሆቴል ዲዛይን ከእነዚህ ቦታዎች ይጀመራል፡፡ 

ሪፖርተር፡– በከተማው አንዳንድ መሐንዲሶች የግንባታ ወጪዎችን ዋጋ ያንራሉ ይሏችኋል፡፡ የሆቴሉ ገጽታና ይዘት በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆን በሚል ምክንያት የተገነባ ታስፈርሳላችሁ፣ ይቀየር እያላችሁ ዋጋ ታንራላችሁ ይሏችኋል?

አቶ ነዋይ፡- ከፈረሱ ጋሪው እንደሚባለው ያለ በቂ ምክክር ከተገነባ በኋላ ከሆነ ደንበኛውን ያገኘሁት፣ የኮከብ ደረጃውን የማይመጥን ቦታ ላይ ተሠርቶ ከሆነ፣ አለያም ሆቴሉ የተገነባበት ቦታና ለሆቴሉ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች በአግባቡ ካልተደራጁ ይህንን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ እመክራለሁ፡፡ ለምሳሌ ማዕድ ቤቱና ምግብ ቤቱ የተራራቁ ከሆነ ለተመጋቢው የሚደርሰው ምግብ መቆየት ካለበት ጊዜ በላይ ይቆይና የሃይጂን ችግሮችም ሊጋለጥ ይችላል፡፡ እኛ ዝርዝር ጉዳዮችን አሳይተን ምርጫውን ለሆቴል ባለቤቶቹ እንተውላቸዋል፡፡ የተገነባውማ ጥሩም መጥፎም ሆኖ ሊገነባ ይችላል፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ እኛ የምንመክረው ግን ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የሆቴል ፕሮጀክቱ ከወረቅት ንድፍ መጀመር አለበት እያልን ነው፡፡ አንዴ የተሠራውን በከፍተኛ የማኔጅመንት ዕገዛና የደንበኛ አገልግሎት አምሮና ተሟልቶ እንዲቀርብ ለማድረግ የምናግዝበት አካሄድም አለ፡፡ ብዙውን ጊዜ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የደንበኛ ዕርካታ መፍጠር ያልቻለ ሆቴል ለችግሩ የሚያሳብበው ማኔጅመንቱ ላይ ሲሆን ይታያል፡፡ ችግሩ ግን በሚገባ ዲዛይን ካለመደረጉና ካለመገንባቱ የተነሳ ሊሆንም ይችላል፡፡ ካሊብራ ገንዘብ ያልወጣባቸው ላይ እናተኩራለን፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ መሥራቱን የምንመርጠውም የባለሀብቱንም የአገርንም ሀብት ለማዳን ከማሰብ በመነሳት ጭምር ነው፡፡ እኛ የምንይዛቸው ፕሮጀክቶች የግድ በዓለም አቀፍ ብራንድ ሥር መተዳደር አለባቸው አንልም፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፍ ብራንድ ቢመጣ ያለምንም ማፈራረስና ተጨማሪ ግንባታ በነበረው ደረጃ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አድርገን ነው የምናዘጋጃቸው፡፡ ለዚህ ከሒልተን ያገኘነው ሰፊ የቴክኒክ ክህሎትና ልምድ ጠቅሞናል፡፡ የተሻለ ዕውቀትና በሥራው ላይ የሚቀሰም ልምድ የምታገኘው በዓለም አቀፍ ሆቴሎች ውስጥ በመሥራት ነው፡፡ ለእዚህ እኔና ባልደረባዬ እማኞች ነን፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴልና መስተንግዶ ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም በሌለበት ሁኔታ እንዲህ ያለውን ዓለም አቀፍ ደረጃ ማሟላት የምንችለው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ሲኖሩ ነው፡፡ ሉዛን፣ ካርኔል እንዲሁም ስዊስ ውስጥ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የሆቴልና መስተንግዶ ትምህርት ቤቶች በሌሉበት ወቅት ትልቅ የክህሎትና ዕውቀት ማግኘት የቻልነው እነ ሒልተን በመኖራቸው ነው፡፡ የእኛ አገር የሥልጠና ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች እንደ አቅማቸው የሚያስመርቋቸው የሆቴል ሙያ ተማሪዎች የተግባር ሥልጠና የሚያገኙት በእነዚህ ጥቂት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ውስጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቂ አይደለም፡፡ ራሱን የቻለ የሥልጠናና በተግባር መማሪያ ሆቴል መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ደረጃቸውን የጠበቀና ዓለም አቀፍ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል መሆን መቻል አለበት፡፡ 

ሪፖርተር፡– ዘንድሮ በአዲስ አበባ ለሦስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሂዷል፡፡ ስኬታማ ነበር? ከነበረስ መለኪያዎቹ ምንድን ናቸው?

አቶ ነዋይ፡- ስለዘንድሮው ከመነጋገራችን በፊት ጥቂት ስለፎረሙ አጀማመር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውን የፈጠሩትና አሁንም ገበያውን እያሽከረከሩት የሚገኙት እነማን ናቸው በማለት ስናጠና፣ ቤንች ኤቨትንስ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ ዓለም ላይ ያለውን የሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም በማዘጋጀት የታወቀ እንደሆነ አረጋግጠናል፡፡ ዓለም አቀፍ ፎረሙን በርሊን ላይ ያካሂዳል፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ፎረሙን ዱባይ ላይ፣ የአውሮፓውን በለንደንና በርሊን ሲያካሄድ፣ በሩስያ፣ በአሜሪካ፣ በቱርክና በሌሎች አገሮችም የሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረሙን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ይኼንን ስናውቅ ፎረሙ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ በማሰብ አነጋግረናቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2010 በኢትዮጵያ እንዲያዘጋጁ ስጠይቃቸው፣ በሞሮኮ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ፎረም ይካሄዳልና እዚያ እንነጋገርበት ብለውን ነበር፡፡ እንኳንና በኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮችም ስብሰባውን የማካሄድ ሐሳቡ አልነበራቸውም፡፡ ይህም ለአፍሪካ ከነበረው ምልከታ ነበር፡፡ ለሆቴል ኢንቨስትመንት የሚመች ነገር የለም ብለው ያስቡ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይፈቅድ ሆቴሎች በራሳቸው የውጭ ደንበኞችን ማግኘት ይቸግራቸው ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ ነበር ይህን ያህል እንግዳ ለዚህ ሆቴል በማለት የሚደለድለው፡፡ ይህም ከዓለም አቀፍ ሆቴሎች አለመኖር ጋር በተያያዘ በየትልልቁ ስብሰባ ወቅት የሚፈጠረውን ችግር ለማቃለል የሚደረግ ነበር፡፡ እንደ ሆቴል ባለሙያ አገር በዚህ ደረጃ ስትቸገር ማየት ያስጨንቅ ነበር፡፡ እነ ሊቢያም ይህን ዓይተው ነው አዲስ አበባ ለአፍሪካ ኅብረት አትመጥንም ሲሉ የነበሩት፡፡ የውጭ እንግዶች በሚሄዱባቸው አገሮች ሁሉ የለመዷቸውን ሆቴሎችና አገልግሎቶችን ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ለስብሰባ በምንሄድበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ቢሮ ሔደን ስለሁኔታው ለቺፍ ፕሮቶኮሉ አቶ መስፍን ሚደቅሳ ሐሳባችንን ነግረናቸው፣ ፎረሙ ላይ የእኛን መሳተፍ ደግፈውና ደብዳቤ አሲይዘው ሸኝተውናል፡፡ ይህንኑ ለቤንች ኤቨንትስ ኃላፊዎች ስናሳውቅ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓይነቱ ስብሰባ ብቁ አይደለችም ብለው ያስቡ ስለነበር፣ በኢትዮጵያ ሸራተንን የመሰለ ትልቅ ሆቴል እንዳለና የቱሪዝም ፍሰቱም ለሆቴል ኢንቨስትመንት የሚስማማ እንደሆነ አቀረብንላቸው፡፡ በወቅቱ መንግሥትም የቱሪዝም ብሔራዊ ምክር ቤት በማቋቋም ላይ ስለነበር ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች አብራራንላቸው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ነው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም የተመሠረተው እንጂ መጀመርያ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ነበር ሲካሄድ የነበረው፡፡ እኛ የመጀመርያው ዕድል እንዲሰጠን እየጠየቅን በነበረበት ወቅት ኬንያውያን ከእኛ የተሻለ ዝግጅት በማድረግ ቀድመውናል፡፡ በተከታታይም ፎረሙን አስተናግደዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት ጥረት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2014 ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትም ተመሥርቶ ስለነበር የተሳካ ፎረም ማካሄድ ቻልን፡፡ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴል ለአገር ገጽታና ኢኮኖሚ የሚኖረውን ጠቀሜታ ማሳወቅ የተቻለበት መድረክ ሆኖ በማለፉና ፎረሙ ድጋሚ እንዲካሄድ በማስፈለጉ በዓመቱ ድጋሚ ሲካሄድ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገኝተው ነበር፡፡ ተከታዮቹን ስብሰባዎች ሩዋንዳ አዘጋጅታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን መልካም አካሄዶች የምትከተለው ሩዋንዳ ባቀረበችው ጥያቄ ለሁለት ተከታታይ ጊዜ አሰናድታ ነበር፡፡ ይህ ዘርፉን የሚያነቃቃና በአፍሪካ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ አጉልቶ ለማሳየትም ዕድሉን የፈጠረ መድረክ ነበር፡፡ በሩዋንዳ የተሰናዳውና እ.ኤ.አ. በ2018 የተካሄደው ስብሰባ ላይ ዋናው ተናጋሪ የዘርፉ ባለሙያ ስለኢትዮጵያ ሲናገር ያቀረበው በወቅቱ ገና ሥልጣን ላይ የወጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ይወስዷቸው የነበሩ ዕርምጃዎችና እየታዩ የነበሩት ፈጣን ለውጦች ኢትዮጵያ ዳግም ትኩረት እንዲሰጣት አስችሏል፡፡ የሆቴል ኢንዱስትሪ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡ ትልልቅ ብራንዶችን ይዘን በሚገባ ከሠራንበት ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍል ሒሳብ የሚወጣለት በዶላር ተሰልቶ ነው፡፡ እንበልና 150 ክፍሎች ያሉት ሆቴል ሠርተህ፣ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶውን እንደምታከራየው በማሰብ እያንዳንዱን በቀን 200 ዶላር ሒሳብ ብታከራየው ስንትና ስንት ገቢ እንደሚያስገኝ ማስላት ትችላለህ፡፡ አሁን ደግሞ ታላቁን ቤተ መንግሥት ወደ ሙዚየምነት የመቀየርና የገቢ ምንጭ እንዲሆን የሚፈልግ መሪ በመጣበት ወቅት ፎረሙን ማካሄድ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገን የታወቀ ነው፡፡ ፎረሙን ስኬታማ ያሰኙት ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ ስለንግድ መነጋገሪያ ብቻም ሳይሆን፣ ኤሆፕ ኢትዮጵያ ለተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት 15 ሺሕ ዶላር የተለገሰበት፣ ተሳታፊዎች ለዚህ ተግባር ከውጭ በልዩ ዲዛይን ተሠርቶ የመጣውን ካኔቴራ ለብሰው የሮጡበት፣ ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በለንደን ማራቶን ያሸነፈበትን ማልያ ለጨረታ አቅርቦ በአንድ ጥሪ በ5,000 ዶላር ዋጋ የተሸጠበትና ለዚሁ ዓላማ የዋለበት መድረክ ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ የታላቁን ቤተ መንግሥት ሙዚየም የጎበኙበት አጋጣሚም የፎረሙ አንዱ መገለጫ ነበር፡፡ በርካታ የሆቴል ኢንቨስትመንት ውይይቶች፣ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር ትልቅ አገልግሎት እያቀረበ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሞክሮ የተወሳበትና ሌሎችም የቀረቡበት ነበር፡፡ በፎረሙ ከ15 በላይ አዳዲስ ውሎች ተፈርመዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህም ሆኖ ግን ሦስተኛው ፎረም ከመጣ በኋላ የሚጠበቀውና እንደ ከዚህ ቀደሙ ብዛት ያለው የሆቴል ስምምነት ሲፈረም አልተመለከትንም፡፡

አቶ ነዋይ፡- በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ አራት ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ጠብቀን ነበር፡፡ አንዱ ብቻ ተፈርሟል፡፡ ሦስቱ በባለሀብቶቹና በሆቴሎቹ የራሳቸው ፕሮግራም አለመመቻቸት ሳይፈረሙ ቀሩ እንጂ፣ የኢንቨስትመንት ስምምነቶቹ ዳር ደርሰዋል፡፡ ፊርማ ማኖር ብቻ ሲጠበቅ ለፎረሙ ሳይገጣጠም ቀረ እንጂ የፕሮጀክቶቹ ስምምነቶች በካሊብራ አመቻቺነትና አደራዳሪነት ያለቁ ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከካሊብራ ውጭ ስምምነት የተደረገባቸው የሉም ማለት ነው?

አቶ ነዋይ፡- ከእኛ ውጭ አንድ ፕሮጀክት ስምምነት ተደርጎበታል፡፡ ባለሀብቶቹ በራሳቸው ቀጥታ ከዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሉ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ያደረጉት ስምምነት አለ፡፡ ከእኛ ውጭ አምስት ያህል ሆቴሎች መፈረም የሚችሉበት አጋጣሚ ታይቷል፡፡ ብራንድ ሆቴሎች የሚፈርሙት የሆቴል ኢንቨስትመንቱና ግንባታው ተጀምሮም ጭምር ነው፡፡ ካሊብራ ሆቴሎቹ እስኪመጡ አይጠብቅም፡፡ ምክንያቱም ቴክኒካዊ መስፈርቶቻቸውን ስለምናውቅ፣ የገበያ ጥናትና ሌሎችም የዲዛይን ይዘቶችን አስተካክለን ካዘጋጀን በኋላ፣ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴል እንዲመጣና እንዲስማማ ማድረጉ ሦስተኛ ደረጃ ሥራ ነው፡፡ የገበያ ጥናቱም ዲዛይኑም አሟልተን ከጨረስን በኋላ ነው ፕሮጀክቱንና አዋጭነቱን ዓይተው አብረው ለመሥራት የሚመጡት፡፡ ተመሳሳይ ቋንቋ መነጋገር በምንችልበት ደረጃ ላይ ስንደርስ ይመጣሉ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 27 የሚደርሱ ሆቴሎችን ለማፈራረም የቻልነው ለብራንድ ሆቴሎች ፍላጎት የሚመች መፍትሔ በመስጠታችን ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጥያቄን ምላሽ በመስጠትና መተማመኑ እስኪፈጠር ድረስ በትንሹ እስከ አራት ዓመታት አብረናቸው ፕሮጀክቱን እናስኬዳለን፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደ ቤተሰብ አብረናቸው እንሠራለን፡፡ ጥያቄዎቻቸውን እንመለስለን፡፡ ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ አገር ተጠቃሚ ስለምትሆን፣ ሥራው ወሳኝ ነው፡፡ የዘንድሮው ፎረም ስኬታማ የሆነባቸው በርካታ ውጤቶች ታይተውበታል፡፡ ከ450 ያላነሱ የውጭ የሆቴል ባለሙያዎችና ባለሀብቶች የተሳተፉበት፣ የአገሪቱን ሁኔታና አመቺነት የተመለከቱበት፣ ለወደፊቱም አማራጭ ዕድሎችን ያስተዋሉበት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴሎች ተስፋፉ፡፡ እናንተም ከ25 በላይ ሆቴሎችን ወደ ኢትዮጵያ አመጣችሁ፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እንደ ልብ ጎብኝዎችን ለተራዘመ ጊዜ ሊያቆያቸው የሚችል አሠራር አልዳበረም፡፡ የሆቴል ዘርፉን ማስፋፋቱ ብቻ ፈተና አይሆንም ወይ? በጎብኝዎች ቆይታ ላይስ መሥራት አይገባም?

አቶ ነዋይ፡- ይህ ልክ ነው፡፡ የትኛውም ጎብኚ ለስብሰባ አለያም በግሉ ለመዝዝናት ወይም ለሌላ ዓላማ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሆኖም ጎብኚዎች ከመጡበት ዓላማ በሻገር ተጨማሪ ቀናትንና ምሽቶችን በኢትዮጵያ እንዲያሳልፉ በማድረግ እንዴት ገንዘብ እናገኛለን የሚለው በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙም አልሠራንበትም፡፡ ይህ የተቀናጀ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የዘርፉ የሙያ ማኅበራት፣ አስጎብኚዎችና የቱሪዝም ወኪሎች በተቀናጀ መንገድ ካልሠሩ በዘርፉ ተጠቃሚነታችን ላይ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ መዳረሻዎቻችንን ማስተዋወቅ አለብን፡፡ ቱሪስቶች ከመነሻው ስለኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶችና ስለሚጠብቋቸው መልካም ነገሮች ቀድመው ማወቅ መቻል አለባቸው፡፡ በአንድ ወቅት ግብፅን የመጎብኘት ዕድል ነበረኝ፡፡ አገሪቱን የሚሸጠው አስጎብኝ ድርጅት ብቻ አልነበረም፡፡ የሆቴል ጠባቂዎችና ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ስለአገራቸው የቱሪዝም ሀብት በሚገባ ይገልጹልሃል፡፡ ቀን ከፍለህ ያየሃቸውን ፒራሚዶች ማታ ደግሞ ታሪካቸው በፊልም እየተተረከልህ በጨለማ ትመለከታለህ፡፡ ለዚህም ትከፍላለህ፡፡ ቀን ብትከፍልም ማታም ድጋሚ ያንኑ መጠን ትከፍላለህ፡፡ ስለፒራሚድ አሠራር ጥርት ባለ የድምፅና የመብራት አጠቃቀም በማራኪ ሁኔታ ያሳዩሃል፡፡ እኛ ከእነሱ ያላነሱ ሰፊ ቅርሶች አሉን፡፡ ግን በአግባቡ ማሳየቱና ማስጎብኘቱ ነው ችግራችን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት ሥራ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሞዴል ነው፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችም ይህንኑ ተመልክተው ዘርፉን ለመወለጥ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ሆቴል ውስጥ ብዙ ዕውቀት ያላቸው፣ ቱሪዝሙን የሚመሩ የካበተ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች አሉን፡፡ የማየው ችግር ግን አለመተባበርና አለመተጋገዝ ነው፡፡ የካሊብራ ስኬት በትብብር ከመሥራት የሚመነጭ ነው፡፡ አሁን ወዳለንበት ሥራ ሳንገባ ከምናውቃቸው የዘርፉ ተዋንያን ጋር በጋራ መሥራትና መተባበር በመቻላችን ነው፣ ይህን ሁሉ ዓለም አቀፍ ሆቴል ማምጣት ያስቻለን፡፡ እኔም የሥራ አጋሬም ከሙያም ከዝንባሌም ጭምር በአንድነት ለመሥራት ያበቃን ትልቅ መናበብና መተባበር አለን፡፡ እንዲህ ያለው ትብብርና ተመሳሳይ ፍላጎት፣ ዕውቀት፣ ሙያና ክህሎት ታክሎበት ውጤታማ ሲያደርገን ዓይተናል፡፡ የቤተሰባችንም አስተዋጽኦም ለዚህ ይጠቀሳል፡፡ እኔም ዮናስም ከእናቶቻችን ጋር ጥሩ ቀረቤታ አለን፡፡ የእኔ እናት የታወቀች የሆቴል ባለሙያ ነበረች፡፡ ከአንድም ሦስት ጊዜ በመንግሥት ሽልማት አግኝታለች፡፡ ከልጅነቴ የሙያው ፍላጎት እንዲያድርብኝ አስችላኛለች፡፡ ፍላጎቷ ትልቅ ሆቴል የመገንባት ህልም ነበር፡፡ የሕይወት ጉዳይ ሆነና ዛሬ አብራኝ የለችም፡፡

ሪፖርተር፡– የሆቴል ጉዳይ ሲነሳ የሆቴል ብራንድና የኮከብ ደረጃ ሲያከራክር ይታያል፡፡ የኮከብ ደረጃ አሰጣጥን የሚተቹ የሆቴል ባለሙያዎች ይህ አሠራር ያፈጀ ነው ተጠቃሚ ኮከቡን ሳይሆን የሆቴሉን ብራንድ ወይም ማንነት አይቶ ነው የሚመጣው ይላሉ፡፡ በኮከብና በብራንድ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ነዋይ፡- የኮከብ ደረጃ ሥርዓት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ብራንድ የኮከብ ደረጃን ለመግለጽ የምንጠቀምበት አይደለም፡፡ የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ሥርዓት ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው አሠራር ሲሆን፣ ደረጃውን የሚያወጣው መንግሥታዊ ተቋምም የአገሪቱን ገጽታ በአግባቡ ሊገልጽ የሚችል ደረጃ የማውጣትና የማስተግበር ኃላፊነት በመውሰድ የውጭ ጎብኝዎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይኖቸው ለማስቻል ጭምር የሚውል አሠራር ነው፡፡ የኮከብ ደረጃ አሠራር መኖሩ ልቅ የሆነና የዘፈቀደ አሠራርን መሥመር ያስይዛል፡፡ ማንም እንደፈለገ የራሱን ኮከብ ደረጃ እያወጣና ለራሱ እየሰጠ በነበረበት ወቅት ጎብኝዎች ቅሬታ ሲፈጠርባቸው ቆይተዋል፡፡ በሌላ አገር ያለው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ደረጃ በኢትዮጵያ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ መገኘት መቻል አለበት፡፡ የኮከብ ደረጃውን የሚገልጽና የሚመጥን አገልግሎት መኖር መቻል አለበት፡፡ የሚከፍሉን ሰዎች ለሚከፍሉበት ዋጋ ተመጣጣኝ ነገር እስካልሰጠናቸው ድረስ ቅሬታ ውስጥ ገብተው ገጽታችንን ሊጎዳ የሚችል ነገር ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎትና የኮከብ ደረጃን የጠበቀ መስተንግዶና አቅርቦት መስጠት መቻል አለበት፡፡ አሁን ላይ የቃሉ አጠቃቀም እየተቀያየረ ቢሆንም፣ በሁሉም አገሮች ውስጥ የኮከብ ደረጃ አሁንም  እየተተገበረ ነው፡፡ በሆቴል ኢንዱስትሪው ብራንድ የምንላቸው ገንነው የወጡ ተቋማት አሉ፡፡ እንደ ሒልተን፣ ማሪዮት፣ ኢንተር ኮንቲኔንታል ግሩፕ የመሳሰሉት ለዓመታት እየተሻሻለና እያደገ የመጣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አላቸው፡፡ አንዱ ከሌላው ያላቸው ልዩነት የሚገለጸው በሚሰጡት አገልግሎት ደረጃ ነው፡፡ አንዱ የሆቴል ብራንድ በሥሩ በተለያየ የኮከብ ደረጃ የሚመደቡ ብራንዶች ይኖሩታል፡፡ ብራንድ መለያቸው ነው፡፡ ብራንዱ ምንም ይሁን የኮከብ ደረጃ መያዙ ግን መሠረታዊና የማይቀር ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...