ለዘመናት ተዋዶ፣ ተዋልዶና ተከባብሮ፣ በቋንቋና በባህል ተሳስሮ በኖረው የአማራና የቅማንት ሕዝብ መካከል በመግባት እያጋጩና ሁከት እየፈጠሩ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በመፍጨርጨር ላይ ያሉት ወይም የሚጣጣሩ የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ናቸው ሲል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረውን የሰላምና የመግባባት ሒደት ለማደናቀፍ፣ ለአንዱ ወገን የተቆርቋሪነት ጭምብል በማጥለቅ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከሚሠሩት ሴራ ጀርባ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ያለሙትን አዝመራ በወቅቱ እንዳይሰበስቡ በማድረግ፣ ክልሉን በኢኮኖሚ ማዳከም መሆኑን ገልጿል፡፡
የአማራን ሕዝብ ማዳከም የስትራቴጂያቸው አካል በማድረግና የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር በመሆን እያካሄዱት ያለው የሽብር ተግባር የትም እንደማይደርሳቸውም አክሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት በመግለጫው እንዳብራራው፣ ሰሞኑን የተፈጠረው ሽብር ሲገለጥ የሚገኘው ሀቅ፣ በአማራና በቅማንት ሕዝቦች መካከል የተለየ ግጭት ኖሮ ሳይሆን የሁከት ነጋዴ የሆኑ የጥፋት ኃይሎች፣ በተቀናጀ መልክ ያደረጉት ሴራ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ለማፍረስና አማራውን በልዩ ልዩ መንገድ ማዳከም መሆኑን የክልሉ ሕዝብና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው ጠቁሟል፡፡ የተፈጠረው የሽብር ተግባር የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ፣ በፋይናንስና ሆን ተብሎ ለጥፋት በተከፈቱ የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በተቀናጀ ሁኔታ ታስቦበት የሚሠራና የአማራ ሕዝብ አንድ እንዳይሆን ለማድረግ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ተጀምሮ በሁሉም ዘንድ የሚቀጣጠል እሳት በመለኮስ፣ የክልሉን ሕዝብና መንግሥት ስም በማጠልሸት አንድነታቸውን እንዲፈርስና እርስ በርስ ለማበላላት፣ በተለይ በአማራ ስም በተከፈቱ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም መግለጫው ያብራራል፡፡
ሴረኞች እንዳለሙትና እንደፈለጉት ሳይሆን ትልማቸውና ዕቅዳቸው ሁሉ እየከሸፈ መሆኑን የሚናገረው የክልሉ መንግሥት መግለጫ፣ አማራን በሁለንተናዊ መልኩ በማዳከም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጣጣሩ የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞችን የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከሕዝቡ ጋር ሆኖ በጠንካራ ክንዱ የሚመክታቸው መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ሕገወጥ ተግባር እየፈጸሙ የሚገኙ ወንጀለኞች ካለፈው ስህተታቸው የማይማሩና ታሪክ ይቅር በማይለው የጥፋትና የሽብር ተግባር የተጠመዱ በመሆናቸው፣ እንዲሁም የእነሱም ሕገወጥ የሽብር ተግባር በማራገብ ላይ በሚገኙ ጽንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድም የክልሉ መንግሥት ጠይቋል፡፡ የአማራ ሕዝብና መንግሥት የጥፋት ኃይሎች ሴራን እያወቁ ዝም ያሉት ለዘላቂ አብሮነት መሆኑን የጠቆመው የክልሉ መንግሥት፣ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ትዕግሥትንና ሆደ ሰፊነትን በንቀት ዓይን መመልከታቸውን ትተው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መክሯል፡፡ ካልሆነ ግን የክልሉ ሕዝብና መንግሥት በአንድነት በመቆም ራሳቸውን ለመከላከል እንደሚገደዱም አሳስቧል፡፡