የባንኩ ኃላፊዎች ተሿሚዎቹ ለቦታቸው ይመጥናሉ ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሦስት ምክትል ገዥዎችን መሾማቸውን ተከትሎ የባንክና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥያቄ አነሱ፡፡ ሹመቱ የተሰጣቸው ኃላፊዎች አገሪቱ ላለችበት ችግር ተገቢውን መፍትሔ መስጠት ስለመቻላቸው ተጠራጥረዋል፡፡
ለባንኩ ምክትል ገዥነት የተሾሙት በባንኩ የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ እያገለገሉ የሚገኙ ሦስት ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሪፖርተር ከብሔራዊ ባንክ ባረጋገጠው መሠረት፣ ባንኩን በምክትል ገዥነትና በዋና የኢኮኖሚ ባለሙያነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ የተባሉ ኃላፊ ናቸው፡፡ አቶ ፈቃዱ ለተሾሙበት ቦታ ከመመረጣቸው ቀድሞ በባንኩ የውጭ ኢኮኖሚያዊ ትንተናና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
አቶ ሰሎሞን ደስታ የተባሉ ሌላኛው ምክትል ገዥም፣ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡ በአዲሱ ኃላፊነታቸውም የፋይናንስ ተቋማትን ለመቆጣጠር በምክትል ገዥነት ተመድበዋል፡፡ አቶ ኢዮብ ገብረ ኢየሱስ በብሔራዊ ባንክ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓቱን እንዲሁም የክፍያ አፈጻጸሞችን የሚመራውን ዳይሬክቶሬት በመምራት ላይ ነበሩ፡፡ በአዲሱ ሹመታቸው መሠረት ግን በምክትል ገዥነት የባንኩን የኮርፖሬት ዘርፍ ይመራሉ ተብሏል፡፡
ይሁንና የባንኩ ምክትል ገዥዎች ሹመት ከኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ዘንድ ቅሬታና ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈጉ የባንክና የኢኮኖሚ ባለሙያ ለሪፖርተር የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምደባው የኮታ እስኪመስል ድረስ የተሻሉና በዚህ ደረጃ የተሻለ ውሳኔና አመራር ሊሰጡ የሚችሉ ባለሙያዎች ሳይታጡ ከታች የነበሩትን መሾም ለሥራው አይመጥንም፡፡›› አያይዘውም መንግሥት ‹‹አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማለት ትልቅ አገራዊ አጀንዳ በዘረጋበት፣ በመሠረታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶች ኢትዮጵያ እየተናጠች በምትገኝበት ወቅት፣ የተሻለ ልምድና አቅም ያላቸው ወደ ኃላፊነቱ ሊመጡ ሲገባ፣ ሥራ ለማስለመድ በሚመስል መንገድ ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቀውን ሹመት ለበታች ኃላፊዎች መስጠቱ አያስኬድም፤›› በማለት ኮንነዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የገለጹ የብሔራዊ ባንክ የበታች ኃላፊ በበኩላቸው፣ ‹‹አዲሶቹ ተሿሚዎች ለቦታው ያላቸውን ብቃት ሲያስመሰክሩ የቆዩ ናቸው፤›› በማለት ለቦታቸው እንደሚመጥኑና ለሚፈለገው የሪፎርም ፕሮግራምም ተገቢነት እንዳላቸው ተከራርከዋል፡፡ ለብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥነትና ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያነት የተሾሙት አቶ ፍቃዱ፣ ለዓመታት የፖሊሲ ጥናቶችና ምርምሮችን በማካሄድ ሲሳተፉ የቆዩ፣ በተቋሙ የሕትመት ውጤቶችም የጥናት ውጤቶቻቸውን በማሳተም የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፎች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በእኚሁ ኃላፊ ተነግሮላቸዋል፡፡ የተቀሩትም ለተመደቡበት ቦታ ብቃት እንዳላቸው በመግለጽ ሞግተዋል፡፡ ስለተሿሚዎቹ ምደባ ተጨማሪ ማብራሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፡፡
አቶ ፍቃዱ የተሾሙበት የምክትል ገዥነትና የዋና ኢኮኖሚ ባለሙያነት ቦታ፣ ከዚህ ቀደም በዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ሲመራ ነበር፡፡ ይሁንና ዮሐንስ (ዶ/ር) ከዚህ ኃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት የተዛወሩ ሲሆን፣ በምክታቸው የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ተሾመው ነበር፡፡ አቶ በቃሉ ሹመቱን ባለመቀበላቸው ሳቢያ ይህ ቦታ ሌላ ኃላፊ ሳይመደብበት ቆይቷል፡፡
የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና እሳቸውን በመተካት በቦታው ሲሠሩ የቆዩት አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ በአዲሱ ተሿሚ አቶ ሰሎሞን ደስታ ሲተኩ፣ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፉን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት አቶ የማነ ዮሴፍም በአቶ ኢዮብ ገብረ ኢየሱስ ተተክተዋል፡፡