Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላል ላይ በድጋሚ...

የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላል ላይ በድጋሚ ለመምከር ሱዳን ገቡ

ቀን:

የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቅዳሜ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ሱዳን መግባታቸው የታወቀ ሲሆን፣ ለሁለት ቀናት በሚያደርጉት ቆይታም የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ ምክክር በማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚጥሩ ይጠበቃል፡፡

 ሚኒስትሮቹ የሚያደርጉት ምክክር በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በግብፅ የጀመሩት ስብሰባ ቀጣይ ሲሆን፣ በካይሮ በነበራቸው ስብሰባ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ በተናጥል ያቀረበችው ፕሮፖዛል ለውይይት ቀርቦ በኢትዮጵያ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

አሁን በሱዳን በሚቀጥለው በዚህ ስብሰባ ላይ ግን የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ባለሙያዎች በዛው በሱዳን ላለፉት አራት ቀናት ባደረጉት ውይይት የደረሱበትን ውጤት ለሚኒስትሮቹ አቅርበው ምክክር እንደሚካሄድበት ሪፖርተር ከኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ባለሙያዎች ሰሞኑን በሱዳን ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ግድቡ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ በውኃ ሊሞላ እንደሚችል በተናጥል በቀረቡ ፕሮፖዛሎች ላይ ምክክር ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ የደረሱበትን ውጤት በተመለከተ እስካሁን ለሚዲያ ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡

- Advertisement -

በሱዳን ሲካሄድ በነበረው የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን የህዳሴ ግድቡ በውኃ በሚሞላበት ወቅት ከግምት ውስጥ የሚያስገቡዋቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በመንተራስ፣ ውኃ የመሙላት ሒደቱ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚገልጽ የጥናት ሐሳባቸውን እንዳቀረቡ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በውኃ ለመሙላት ሦስት ዓመት በቂ እንደሆነ በጥናት ብታረጋግጥም፣ የተለያዩ ቴክኒካዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ግድቡን ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደምትሞላ በጥናት ላይ የተመሠረተ አቋም እንደያዘች ሪፖርተር ከሳምንት በፊት ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ቡድን አባልና የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) አማካሪ ከሆኑት ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በካይሮ ተካሂዶ በነበረው የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ግብፅ የግድቡ ውኃ ሙሌትን በተመለከተ ሌሎቹን አገሮች ሳታማክር ያዘጋጀችውን ሰነድ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጓን መዘገባችን ይታወቃል፡፡

በሱዳን በተካሄደው የባለሙያዎቹ ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን በኩልም የውኃ ሙሌቱን አግባብና የጊዜ ሁኔታ የተመለከተ ሰነድ የቀረበ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሱዳን በግብፅ ተካሂዶ በነበረው ስብሰባ ላይም ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ ጌድዮን (ኢንጂነር) ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በካይሮ ተካሂዶ በነበረው የሚኒስትሮቹ ስብስባ ላይ ግብፅ በተናጥል ባቀረበችው ሰነድ ይዘቶች ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት በእጅጉ ከተተቹት ነጥቦች ዋነኛው፣ “የግድቡ የውኃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ እንድትለቅና ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ ዝቅተኛ የውኃ ይዞታ 165 ሜትር መሆኑን ማረጋገጥና የአስዋን የውኃ መጠን በዚህ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውኃ ላይ መልቀቅ ይኖርባታል፤” የሚል ነው፡፡

ከውኃ ሙሌቱ በተጨማሪም የህዳሴ ግድቡ ሥራ ሲጀምር ኃይል የሚያመነጭበት ሒደት ከግብፅ ባለሙያዎች ጋር በጋራ እንዲመራም ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅ ያቀረበችውን ሐሳብ ሉዓላዊነትን የሚዳፈር፣ በትብብር ላይ ተመሥርቶ ከተጀመረውና ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት መንገድ ያፈነገጠ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ አድርገዋለች፡፡

 ይህንኑ የግብፅ ያልተገባ መንገድና የኢትዮጵያን አቋም በተመለከተም፣ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሒሩት ዘመነ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ የሚገኙ አምባሳደሮችን ሰሞኑን በመጥራት ግልጽ አድርገዋል፡፡ ሚኒስትሮቹ በሱዳን በጀመሩት በዚህ ስብሰባ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ፣ ጉዳዩ ቡድን ዘጠኝ በመባል ለሚታወቀውና የሦስቱ አገሮች መሪዎች፣ የመከላከያ ሚኒስትሮችና ዋና የደኅንነት ኃላፊዎች አባል ለሆኑበት ቡድን እንደሚመራ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...