Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

12 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ሊዛወሩ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በ2012 በጀት ዓመት 12 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ዕቅድ መያዙንና በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ያለውን የ70 በመቶ የባለቤትነት ድርሻም ለመሸጥ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸሙና የ2012 በጀት ዓመት ዕቅዱን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣ በበጀት ዓመቱ ወደ ግል ከሚዛወሩት 12 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ስድስቱ የስኳር ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ካሉት 13 የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ ወደ ግል የሚዛወሩት ስድስቱ በጥናት ተለይተው ይፋ ከተደረጉ በኋላ ወደ ግል የማዛወሩ ሥራ ይሠራል ተብሏል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ የትኞቹ የስኳር ፕሮጀክቶች ወደ ግል ይዛወራሉ ለሚለው እየተደረገ ያለው ጥናት ሲያልቅ እንደሚታወቅና ከአንድ ወር በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ከስኳር ፕሮጀክቶቹ ሌላ በፍልውኃ አስተዳደር ሥር የሚገኘው የላንጋኖ ቅርንጫፍ ሆቴል ወደ ግል ይዛወራል ተብለው ከተመረጡት ውስጥ ይገኛል፡፡ ሦስት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎችም በዚህ ዓመት ወደ ግል እንደሚዛወሩ የዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ያስረዳል፡፡

በመንግሥትና በሒልተን ኢንተርናሽናል የባለቤትነት ይዞታ የሚተዳደረው የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ላይ መንግሥት ያለውን የ70 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በሽያጭ እንደሚያስተላልፈው ታውቋል፡፡

እንደ አቶ በየነ ማብራሪያ የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል 70 በመቶው የኢትዮጵያ የመንግሥት ድርሻ በመሆኑ፣ ይህንን የባለቤትነት ድርሻውን በሽያጭ ለማስተላለፍ የሚያስችለው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የሆቴሉ አጠቃላይ የሀብት ግምት ከተሰላ በኋላ ወደ ጨረታ ሒደት ይገባል ተብሏል፡፡

ኤጀንሲው በ2012 የበጀት ዓመት ወደ ግል ከሚያዛውራቸው (ስድስቱን የስኳር ፕሮጀክት ሳይጨመሩ) እና ከዚህ ቀደም ወደ ግል ካስተላለፋቸው ድርጅቶች ወደ 4.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንዳቀደም ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሌላው ክዋኔ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው በኤጀንሲው ሥር ከሚገኙት 23ቱ የልማት ድርጅቶች ሁለቱን የሚያዋህድ መሆኑን የኤጀንሲው ዳይሬክተር ከሰጡት መግለጫ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ውህደት ይፈጽማሉ የተባሉት የልማት ድርጅቶች አዶላ ወርቅ ልማት ድርጅትና የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት ኩባንያዎች ማዋሃድ የተፈለገው በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ በመሰማራታቸው ነው ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም ጨረታ ወጥቶ ከአሸናፊው ጋር ውል ሊገባ ሲል በፍርድ ቤት ዕገዳ የተቋረጠው የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጉዳይ ምን ደረሰ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ፣ ጉዳዩ በቅርቡ ይቋጫል  ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊውን ለመለየት እየተሠራ በነበረበት ወቅት፣ በፋብሪካው ላይ መብት አለኝ ያሉና ፋብሪካው በደርግ ዘመን ያለአግባብ የተወረሰ ነው በሚል ከፍርድ ቤት ባመጡት ዕግድ የሽያጩ ውጤትና ማስተላለፉ ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ አቶ በየነ እንደገለጹት ዕግድ ያመጡት ግለሰብ ጥያቄያቸው ቀደም ብሎ በነበረው አዋጅ መሠረት ከዚህ ቀደም አስተናግዷቸዋል፡፡

ይህ በወቅቱ ሥልጣን የነበረው አካል ‹‹ሊመለስላቸው አይገባም›› ብሎ መወሰኑን አስታውሰው፣ በየደረጃው ይግባኝ ብለው ቢያቀርቡም በጊዜው የዚያ ኤጀንሲ ቦርድ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ‹‹መመለስ አንደማይችል›› በመግለጽ ከአንድም ሁለት ጊዜ ውሳኔ ያስተላለፈበት ጉዳይ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ድጋሚ ፋብሪካው መሸጥ የለበትም ብለው ከፍርድ ቤት ዕግድ አውጥተው ፋብሪካውን ለመሸጥ የወጣውን ጨረታ ውጤቱን ጠብቆ እንዳይፈጸም በማድረግ፣ ጉዳዩ አሁንም ያላለቀ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በቅርቡ እልባት ያገኛል የሚል እምነት ያላቸው ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ተስፋ የምናደርገው በዚህ ዓመት በመጀመርያው ቀጠሮ ውሳኔ ያገኛል፤›› ብለዋል፡፡

የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ፋብሪካውን ለመግዛት ከቀረቡት ውስጥ ሎሚናት ቤቨሬጅስ 3.6 ቢሊዮን ብር፣ ፒዩር አልኮልና ቤቨሬጅ ማኑፋክቸሪንግ 1.6 ቢሊዮን ብርና መታደም ማኑፋክቸሪንግ 1.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ይህ ፋብሪካ አትራፊ ከሚባሉት የልማት ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ በ2011 በጀት ዓመት እንኳን ከዕቅዱ በላይ የ16 በመቶ ብልጫ ያለው 233.4 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ላይም ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች