Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከማስተዋል በስተጀርባ!

ሰላም! ሰላም! አሁን በዚህ ዘመን ፍቅር ያዘኝ ብላ መርዝ የምትጋት ሴት አለች ቢባል ማን ያምናል እናንተ? እውነት ማን ያምናል? ዳሩ የዘንድሮ መርዝ ጠጪ ማማ ወተት ከጎኑ አስቀምጦ ነው። ማን ሞኝ አለ አትሉም? ከኑሮ ውድነት በቀር ማርከሻ የሌለው መርዝ ለነገሩ የታለና?! ወይ ፍቅር አልኩ ገርሞኝ! ‘ላቭ ኢዝ ብላይንድ’ እንዳትሉ አጮላቂውን እንኳን ‘ሲንግሎቹ’ ባለትዳሮቹም አልቻሉትም። ወይ የዘንድሮ ጉድ! ገንዘብ ባይኖርማ በቃ እኮ ፍቅር የሚለው ቃል ራሱ ዘራቸው እየጠፋ ካሉ እንስሳት ጋር አብሮ በተደመረ ነበር። እውነቴን ነው! አንዳንዴ የዘመኑን ሰው ለገንዘብ ያለውን ፍቅር ሳስተውል ሮሚዬና ዡሊዬት ሳይቀሩ በፍቅር ማመናቸውን ባቆሙ ነበር ያሰኘኛል። በተለይ እንደ ዘመኑ ሰው ሆነው አሁን ተፈጥረው ቢሆን ኖሮ አንድ ያሉን የፍቅር ተምሳሌቶች ድራሻቸው አይጠፋም ልትሉኝ ነው። ‹‹በእነሱ ጊዜ እኮ ‘ቫት’ የለ፣ የአከራይ ተከራይ የለ፣ የልማት መዋጮ የለ። አሁን አይደለም እነሱ ገፀ ባህሪያቱን የፈጠራቸው ሼክስፔር አንዴ ከጥልቅ እንቅልፉ ነቅቶ ያለንበትን ዘመን ቢያየው ፍቅርን በዚያ መንገድ በመግለጹ በተፀፀተ ነበር፤›› ያለኝ አንድ የቅርብ ወዳጄ ነው። ወዳጀ ብዙ ወጉ ረጅም ነው እንዳትሉኝ ብቻ፡፡

ለማንኛውም ጨዋታውን ለምን አነሳኸው ብትሉኝ ፍቅር ያዘኝ ብላ መርዝ ስለጠጣች ለአቅመ ሔዋን የደረሰች የሠፈራችን ጉብል ላወጋችሁ ስለሻትኩ ነው። እንኳን እንዲህ ያለውን ወሬ ሰምተን እንዲሁም የሥራ ፈጠራውን በወሬ ፈጠራ ከተካነው (መተካካቱ የሚሠራው የት የት እንደሆነ እያያችሁ ነው?) ቆይተናል፣ ልጅቷ ያልተባለችውን ጠይቁኝ። ‹‹ዘመኑ የ‘ቶክ’ እና የ‘ቻት’ በመሆኑ ምን ያለችዋ ሞኝ ናት መርዝ የምታስበው?›› አንደኛው ጎረቤት ብሎ ሲያማት ከእኔ በላይ ተረበኛ የለም ባይ ይቀበልና፣ ‹‹አይመስለኝም! ጉዳዩ ቢጣራ ነው የሚሻለው። ከጀርባው የገዥው ፓርቲ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም፤›› እያለ በተቃዋሚዎች ያላግጣል። የሚያላግጠው መብዛት! እንደ ሐሰተኛ ነብይ የማይገናኘውን በማገናኘት የታወቁ አሉ። ‹ያለማስተንፈሻ መኖር አልቻል በተባለበት ጊዜ፣ ‘ያልተገላበጠ ያራል!’ ዓለም አቀፋዊ መርህ በሆነበት ዘመን፣ ምን ያለችው ሞኝ ናት መርዝ መጠጣት የሚታሰባት? መርዝ ብቻ ነው ያልተወደደው? እስኪ ይጣራልን፤›› ሲል ነገርን ከነገር የሚያገናኘውን አለመቁጠር ነው። ኧረ ነገረኛው በዛ፡፡

ምስኪኗን ሴት በአፌ፣ ‹‹እግዜር ካንቺ ጋር ይሁን!›› ብዬ በልቤ ደግሞ ‘ላንቺ ያለው ከሆነ የፈቀድሽው ይፈልግሽ አልነበር? ምን ያቻኩልሻል?’ እያልኩ ወደ ሥራዬ ተጓዝኩ። የሚሸጥ ‘ግራውንድ ፕላስ ቱ’ ቤት ነበረኝና ቀልቤን ነስቶኛል። እናላችሁ ወደ ሻጭና ገዥ ደንበኞቼ ስጓዝ የማስበው ሁለቱም ተስማምተውልኝ ጠቀም ያለ ኮሚሽን መቀበልን ነው። በታላቅ ጉጉት ውስጥ ሆኜ በስሜቴ እፈነድቃለሁ። ድንገት ግን መርዝ ጠጣች ያልኳችሁ ወጣት ነገር ከእኔ ሁኔታ ጋር የተመሳሰለ መሰለኝ። ድንግጥ አልኩላችሁ። የእኛ ያልሆነውን ለእኛ ካልሆነ እያልን የምንታገለው ትግል አጉል ሲያዳክመን ዕድሜያችንን፣ አቅማችንን ሀብታችንንና ጊዜያችንን ያባከነባቸውን ዘመናት በምናቤ ሣልኳቸው። መሆን ያለበት ላይቀር የሕይወትን የዕድል በሮች አጥብቦ መመልከት በጅምላ የምንነዳበት ክፉ ልማድ መሆኑ ይታየኝ ጀመር። ‹‹ወይ ጉድ!›› አልኩኝ ቆም ብዬ። ‹‹ስንቶቻችን እንሆን ጊዜ የሚፈታውን ችግር ከጊዜ ቀድመን ብዙዎቻችን ካልፈታን ብለን በምኞት ስካር ነገር ስናበላሽ የምንኖር?› ብዬ ኋላ ላይ የባሻዬን ልጅ ጠይቄው ነበር። የእኔ ነገር! ያለ እሱ አይሆንልኝም እኮ።

‹ብዙዎቻችንና መስመር የያዘውን ስናፈርስ፣ ሊያልቅ ያለውን ስንንድ፣ አስዋብን ብለን ስናበላሽ፣ ኳልን ብለን በትልልቅ የአገር ጉዳዮች ላይ ሳይቀር አመድ እያቦነንን እኛ ነን እንጂ ተጠያቂ ሌላ ማን ሊሆን?›› አለኝ። ቅልብጭና ግልጽ ባለች ዓረፍተ ነገር። መቼም ከአባቱ ከባሻዬ ያልወረሰው ነገር ቢኖረው ነገርን ጠመምና ለዘብ አድሮጎ መናገርን ብቻ ነው። አሁን ግን የሚናገረው ድፍንፍን ስላለብኝ እንዲያብራራልኝ ወተወትኩት። ‹‹ተመልከት እስኪ! ጊዜን ካልቀደምን ብለን ያበላሸነው እኮ ብዙውን ነገር ነው አንበርብር። በእርግጥ መልካም የሚባሉ ነገሮች ቢኖሩም ሕዝብን ከድህነት ማጥ ውስጥ ማውጣት፣ በዳዮችንና ክፉዎችን መቅጣት፣ ትውልዱን ከአይባሌ ነገር መጠበቅ፣ ፍትሕን ማስከበር፣ የሰው ልጅ መብትን መንከባከብ ድረስ ነው፡፡ ትግሉ ከትጥቅ ትግልነት መልኩን ቀይሮ አንዱ አንዱን ያላግባብ ወደ መቅደም ትግል ተሸጋገረ። የትምህርት ሥርዓቱ፣ አንዳንዱ የኢኮኖሚና የልማት ፖሊሲ፣ የተቃዋሚዎች ግምታዊ አካሄድ ሁሉም አቋራጭ በዛበት፤›› ብሎኝ በረዥሙ ተነፈሰ። አየሩ ተበክሎ መተንፈሱስ ቢሆን መቼ እንደ ልባችን ሆነ ብላችሁ ነው፡፡ 

የቀጠርኳቸው ደንበኞች ከመድረሴ በጥያቄ ተቀበሉኝ። ‹‹አንበርብር! የቤት ኪራይ እንደ እሳት እየተፋጀ ቁጥሩ በጣም እየጨመረ የመጣው ወጣት የኅበረተሰብ ክፍል እንዴት ይሆን ኑሮን እየተቋቋመ ያለው? (የቤት ኪራይ ነገር ዕድሜና ፆታ ይመርጥ ይመስል) የአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ ፈጠራውም እንኳን የኪራዩን ዋጋ የቻለለት አይመስል፤›› የሚል በሽሙጥ የታገዘ ጥያቄ ነበር የተወረወረልኝ። ወዲያው የአንድ ዘመዴ ተረብ ትውስ አለኝ። ‹‹አንድ ሰሞን ጥያቄዎችና ስሞታዎች ሁሉ ወደ መንግሥት ይጎርፉ ነበር፡፡ ሰሚ ጠፋ መሰል ሰው ሁሉ ስሞታውንና ጥያቄውን በየመንገዱ መዘርገፉን ተያይዞታል፤›› ብሎኝ ነበር። በጣም ከመገረሜ የመነጨ ሳቄን መቆጣጠር እየተሳነኝ፣ ‹‹እኔ ምን አውቄ! ይኼ እኮ ሰፊ ትንታኔና ጥናት የሚጠይቅ ነው፤›› በማለት መለስኩ። ይህንን ወሬያችንን የሰሙ ሁለቱ አዛውንቶች በሳቅ ተንከተከቱ። ‹‹አይ አንተ! እሱማ መቼ ጠፋን። ምሁር ተብዬ ሁላ ድምፁ ከጠፋ ደላላ ይተካው ብለን ነው እንጂ። መቼም እናንተ የማትገቡበትና የማታውቁት ጓዳ ጎድጓዳ የለም፤›› አይሉኝ መሰላችሁ? ቤት ለማሻሻጥ ያገናኘኋቸው እነዚህ አዛውንቶች በነገር ተግባብተው ወዲያው ዳር ሲያወጡኝ ባይ ሆድ ባሰኝ። ባልበላ አንጀቴ ጥርስ መንከሱ ‘በደብል ዲጅት’ የሚያድገውን ኢኮኖሚና የልማት ግስጋሴ የሚያደናቅፈው ቢመስለኝ ሳልወድ በግድ ሳቅ ሳቅ አለኝ። ሳቅና ሳግ እየተናነቀኝ ሥራዬን እስክጨርስ መታገስ ነበረብኝ። ከኑሮ ውድነቱ ይልቅ ሽሙጡና ምፀቱ አየለ እኮ?

በነገራችን ላይ በአንድ ወቅት በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ከደረሰው አሳዛኝ ታሪክ ጋር ተያይዞ አንድ ጨዋታ ላጫውታችሁ። ‘በምን ትዝ አለህ?’ ብትሉኝ የወጣቱን አጣብቂኝ የኑሮ ሁኔታ ባነሱት አዛውንቶች ነው። ‹‹እንደ እስራኤላውያን በአራቱም የምድር ማዕዘናት የተበተነ አገር የለም ይባል እንጂ እኛን የሚያክለን ያለም አይመስለኝም፤›› ስትለኝ ሰነበተች ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ። ‘የመከራ ዠንዲ ተነጥፎ ከቤቴ፣ እሱን ስጠቀልል ነው ከኋላ መቅረቴ’ እንዳለው (ዘመዶቹ በሞት ያለቁበት ሰው) ስለሆነ ስለዚህ ዘመን የስደት ጣጣ ምንም መልስ ሳልሰጣት ቀረሁ። የሆነው ሆኖ ‘ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው’ ሆነና በዜጎቻችን ላይ በሳዑዲ ደርሷል በተባለው ጥቃት ‘ዝምታ ነው መልሴ!’ ብለው መንግሥታችንን ቆጣ ብለው የተናገሩትን አግኝቻለሁ። በነሲብና በችኮላ የሚሰጧቸውን አስተያየቶችም ጆሮዬ አላለፋቸውም። ከዚህ ድፍረትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከተሞላበት ድርጊት ልማታዊው መንግሥታችን እንዴት የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ጨዋታ ለመጫወት አስቦ ዝም ይላል? እዚህ ያሉትን ሳዑዲዎች ነበር . . .››  የሚል አስተያየት ባላስጨርሳቸውም ሰማሁላችሁ። ‘ዓይን ላጠፋ ዓይኑን’ የሚለው ሐሙራቢያዊ ብያኔ ከመቼውም ጊዜ በላይ አመዛዛኝ ነኝ በሚለው በዘመኑ ሰው ጭንቅላት ውስጥ መንገዋለሉ አሳቀቀኝ። ‹‹በዚህ ዓይነትማ ነገ አንዳች ንትርክ ውስጥ ብንገባ ቆም ብለን እናስብ የሚል ሰው የለም ማለት ነው፤›› በማለት የባሻዬን ልጅ ስነግረው፣ እሱም በውጭ የሚኖሩ ወገኖቻችን ስቃይ ይልቅ በአገር ቤት የሚገኙ ወገኖቻችን ስሜታዊነት አብሽቆት ኖሮ እንዲህ አለኝ። ‹‹እነዚህ ዓይንን በዓይን ሲሉ የምትሰማቸው ‘ፀሐዩ መንግሥታችን’ ባለዲግሪና ባለማስተርስ አደረኳቸው እያለ ከሚመፃደቅባቸው መሀል ናቸው። ተምሮ እንዳልተማረ መሆን ማለት እንዲህ አይደል ታዲያ?! አገርና እናት ርቀዋቸው ሲሄዱ ባያስችሉም የተሻለ የትምህርት ሥርዓትና የኑሮ ሁኔታ፣ ለቀቅ ያለ የዴሞክራሲ አየር እስካልተነፈስን ድረስ ስደት የሚቆም አይመስለኝም፤›› ነበር አስተያየቱ። እንደ አስተያየት አይተነው ብናልፍስ?!

እስኪ እንሰነባበት። ከዚያ ከነገርኳችሁ ቤት ሽያጭ በኋላ የሚከራይ ‘ሎቤድ’ እና የሚሸጥ ‘ኤክስካቫተር’ ደንበኛ ለማግኘት መድከሜ አልቀረም። በነጋታው አንዱ ባይቀናኝም አንደኛው ስለተሳካልኝ ኪሴ ደለብ ብሎ ዋለ። ‘ዋለ’ ያልኩት እንዳላደረ ለማመልከት መሆኑ ይሰመርበት። የዘመኑ ገንዘብና የመስቀል ወፍ አንድ ሆነውላችኋል። በዓመት አንዴ እየታዩ ለዓመታት መጥፋትን ቋሚ መተዳደሪያቸው ያደረጉት ይመስላሉ። የሆነው ሆኖ ኪስ አበጥ ሲል ልብም ኮራ ይል የለ? በኮራው ልቤ ደረቴን ወደፊት ነፍቼ ከተማውን ቃኘሁት። መቅዳትና ማፍሰሱ፣ መካብና ማፍረሱ፣ ማልማትና ማውደሙ ትኩረቴን ከመቼውም ጊዜ በላይ ስቦኝ ስደመም የልጅነት ወዳጄን ሳላስበው አገኘሁት። ጥቂት ስለሕይወት አውርተን ስናበቃ ስለልማቱና ግንባታው የሚያስበውን ጠየቅኩት። እርሱም ሮም ከክርስቶስ ልደት በፊት በእሳት ተያይዛ ሙሉ ከተማዋ ወድማ እንደነበር ካጫወተኝ በኋላ፣ ከሞላ ጎደል ዛሬ ቢፈራርስም አስደናቂ የግንባታ ጥበብ የታየባቸውን ሕንፃዎች ስላስገነባው መሪዋ ‘ኔሮ’ የነገረኝ ነገር ቀልቤን ሳበው። ‹‹ኔሮ ከተማዋ ተቃጥላለች ብሎ ትቷት መሄድ አልፈለገም። መልሶ ለመገንባት ያለ የሌለውን የመንግሥትና የአምልኮ ቤቶቹን ገንዘብ አወጣው። ንዋየ ቅዱሳትን መዘበረ። ዜጎችን ችላ እያለ ስለህልሙ መሳካት ብቻ ሌት ተቀን ያልም ነበር። ሮም አንድ ቀን ባትገነባም ተገቢውን ጊዜና ዕቅድ በተከተለ ሁኔታ ከመገንባት ይልቅ ችኮላ ስለበዛባት የኔሮ መንግሥት ካዝና ተራቆተ። ውበቷ ደምቆ ሕንፃዎቿ እሳት ሊያነደው በማይችል ነሃስ ተለብጠው ቢሠሩም ዜጎች እጅግ አስቀያሚ በሆነ ድህነት ውስጥ እንዲማቅቁ አደረጋቸው፤›› ሲለኝ የመገረም ስሜት ተሰማኝ። ‘የማትበላ ወፍ ተይዛ በጭራ’ እንዳይሆን ሚዛን የሚደፋ ጉዞ መጓዝ እንዳለብን ገባኝ። ‘የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች’ እንዳይሆን፣ እሳቱን ለማንደድ ብቻ ስንደክም ወተቱ እንዳይገነፍልብን ፈራሁ። ፍርኃቴ ሲባባስ ለማባረር ቆርጬ የባሻዬን ልጅ የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። ቺርስ ለማለት፡፡ ከቺርስ በስተጀርባ ግን መነገር ያለበት ቁም ነገር ያለ መሰለኝ፡፡ ‹‹የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ›› ይባል የለ? ‹‹የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች››፣ ‹‹የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል››. . . ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አስተውለን ስንራመድ ካሰብንበት እንደርሳለን፡፡ ካሰብንበት ለመድረስ ዙሪያ ገባውን እየቃኘን እንጓዝ! ከማስተዋል በስተጀርባ ያሉ ጠቃሚ ጉዳዮች ይመርመሩ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት