በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚወጡና ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች እንዲሁም የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመፈተን አልፎ አደገኛ ተገዳዳሪ ወደ መሆን ደረጃ መሸጋገሩ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
በሕገወጥ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎችን የተመለከቱ አኃዛዊ መረጃዎች የተጣረሱ ቢሆኑም፣ አንዳንድ ጥናትን መሠረት ያደረጉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከውጭ ከሚገቡ ዕቃዎች ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ በሕገወጥ መንገድ መዳረሻውን ኢትዮጵያ ስለማድረጋቸው ያመለክታሉ፡፡
በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጣው ዕቃና በውጭ መገበያያ ገንዘቦች የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ መጠንም ከፍተኛነቱ ይገለጻል፡፡ ይኼንን አገራዊ ችግር ለመቆጣጠር በመንግሥት ደረጃ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከአዲሱ በጀት ዓመት ጀምሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድን አሳሳቢነት በተመለከተ የተካሄዱ በርካታ የምክክር መድረኮች ላይ ሲወሳ ቢቆይም፣ በቅንጅት ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ስለመጀመራቸው የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የተጠናከረ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የጉምሩክ ኮሚሽ ይገልጻል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመትም ጠንካራ ሥራ እሠራለሁ ብሏል፡፡
አገራዊ የፀረ ኮንትሮባንድ ዘመቻ ለማስጀመር በተጠራው የውይይት መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የ2012 ዓ.ም. ቁልፍ አጀንዳችን በመሆኑ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ የተዘረጋና ኅብረተሰቡን የሚያሳትፍ እንቅስቃሴ ይደረጋል ማለታቸው ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ተኩል ጊዜ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በተከታታይ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በዚህ ዓመት በፀረ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከቀደመው የተሻለ ውጤት እየታየ ነው፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተደረገ ቁጥጥር ከፍተኛ ግምት ያላቸው የወጪና ገቢ ንግድ ምርቶች እየተያዙ ይገኛሉ፡፡ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥም 35 የኮንትሮባንድ መረጃዎች የተሰራጩ ሲሆን፣ 114.99 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የገቢ ዕቃዎችና ሕገወጥ ገንዘቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተመልክቷል፡፡
በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ ሊወጡ የነበሩና ግምታቸው 19.37 ሚሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጡ የወጪ ንግድ ዕቃዎች ስለመያዛቸውም ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በሐምሌ ወር ብቻ የግምት ዋጋቸው 134.37 ሚሊዮን ብር የገቢና ወጪ ንግድ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ሕገወጥ ገንዘቦች ተይዘዋል፡፡
ከጉምሩክና ከገቢዎች የወጡ መረጃዎች የሚያሳዩት፣ ከነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የተለያዩ አገር ገንዘቦች መያዛቸውን ነው፡፡
ይህም በአዲሱ በጀት ዓመት ሁለት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ የተያዘው የኮንትሮባንድ የወጪና ገቢ ንግድ ዕቃዎች ግምት ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያልቅ አመላክቷል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ከፍተኛ ግምት ያላቸው ዕቃዎችና በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የውጭ አገር ገንዘቦች መያዛቸውን ተቋማቱ ይፋ አድርገዋል፡፡
በእነዚህ ወራት ውስጥ የተያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃና የውጭ ገንዘብ መጠንም ቢሆን፣ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወቅት እንደተያዘ ሲገለጽ ከቆየው በላይ ስለመሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሆው በሐምሌ ወር ብቻ በቁጥጥር ሥር የዋለው የኮንትሮባንድ ዕቃና በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የተያዘው የውጭ ገንዘብ መጠን ነው፡፡ ከ2011 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር መጠኑ የ128 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ከመረጃዎቹ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ከፍተኛ ግምት ያላቸው የወጪና ገቢ ንግድ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች እንዲሁም የተለያዩ አገሮች መገበያያ ገንዘቦች የሚያዙት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቶቹ መረጃ መሠረት በ2011 በጀት ዓመት ብቻ 1.63 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ የነበሩ የውጭ አገር ገንዘቦች መያዛቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ከ1.63 ቢሊዮን ብር ውስጥ 1.29 ቢሊዮን ብር የሚገመተው ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ነው፡፡ ቀሪው 334.8 ሚሊዮን ብር ደግሞ የወጪ ንግድ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ሕገወጥ የገንዘቦች ዝውውር ነው፡፡
በዚህ ሕገወጥ መንገድ በሚካሄድ ንግድ የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተለያዩ ሲሆኑ ወርቅ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ ሞባይል ቀፎዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ይጠቀሳሉ፡፡ የተለያዩ መድኃኒቶች የጦር መሣሪያዎች ነዳጅና ሌሎች የከበሩ መአድናትም አሉበት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ወርቅ ያሉ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየወጡ ሲሆን፣ በዚህ ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በአንድ ጊዜ ግምታዊ ዋጋቸው ከሰባት እስከ 11 ሚሊዮን ብር የሚደርሱ ጥፍጥፍ ወርቆች ተይዘዋል፡፡
አገሪቱ በየዓመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በመቆጣጠር የሚያዘው መጠን ከፍ ያለ በመምጣቱ ከስፋቱ አንፃር ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባ ይገለጻል፡፡ ይሁን እንጂ የኮንትሮባንድ ንግድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አደንዛዥ ዕፆች ዝውውር ከፍ እያለ መምጣቱ ደግሞ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ አዲሱ በጀት ዓመት ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት ሁለት ወራት ተኩል ብቻ ግምታቸው ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው አደንዛዥ ዕፅ ተይዟል፡፡ ከተቋማቱ መረጃ መረዳት እንደተቻለው ባለፉት ሁለት ወራት በአንድ ጊዜ ግምታቸው 19 ሚሊዮን ብርና 27 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ኤርፖርት መያዙ ይጠቀሳል፡፡
ኮሚሽኑ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ዋና ዋና ከሚባሉ የኮንትሮባንድ ዓይነቶች ውስጥ የሚካተት ስለመሆኑ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁንም የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ከወትሮ በተለየ በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር የሚጠቀሰው የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ብዙ የሚሰማ ይሰማ ያልነበረ አሁን ግን ከፍተኛ ግምት ያላቸው አደንዛዥ ዕፆች የተያዙ ነው የሚለው መረጃ በተደጋጋሚ እየተሰማ መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት እያመላከተ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያም የገቢዎች ሚኒስቴር መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገለጸው በአፋር ክልል ዞን ሦስት ወረር በሚባል አካባቢ 1,702 ኪሎ ግራም ካናቢስ የሚባል አደገኛ ዕፅ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቀዋል፡፡
በአፋር የተያዘው አደንዛዥ ዕፅ ግምታዊ ዋጋው እስካሁን ይፋ ባይሆንም መጠኑ እስካሁን በአንዴ ከተያዙት የአደንዛዥ ዕፆች ከፍ ያለ እንደሆነ ይገመታል፡፡ እንዲህ ያሉት መረጃዎች የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መጠን እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክቱ ሆኗል፡፡
በቀደመው ዓመትም ሆነ ባለፉት ሁለት ወራት ተኩል ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ ወደ አገር የሚገባው ይበዛል፡፡ ሆኖም ወደ ውጭ የሚወጡ በተለይ አገሪቷ በሕጋዊ መንገድ ብትልካቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ አሁንም ግን ምርቶች ላይ ቁጥጥሩ በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆኑን ያሳያል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንድ በአገሪቱ የቀንድ ከብት የኮንትሮባንድ ንግድን በተመለከተ ጥናት ያቀረቡ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደሚገልጹት፣ ከአገር ወደ ውጭ የሚሸሸው የውጭ ገንዘብና ወርቅ ብቻ ያለመሆኑን ጠቁመው የቀንድ ከብት የኮንትሮባንድ ንግድ የአሳሳቢነቱን ያህል ቁጥጥር እየተደረገበት ያለመሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የጉምሩክ መረጃም በኮንትሮባንድ የሚወጣውን የቀንድ ከብት የተመለከቱ አኃዛዊ መረጃ ያለመስማታቸው ግር እንዳላቸውና በዚህ ረገድ የሚደረገው ቁጥጥር ከሌላው በተሻለ ምቹ ቢሆንም የቀንድ ከብት ኮንትሮባንድ ጉዳይ ለምን ቸል እንደተባለ ግራ ያጋባል ባይ ናቸው፡፡ ቡናና ሌሎች የከበሩ መአድናትም በተመሳሳይ እየወጡ ቢሆንም እነዚህ ላይ ያለው ቁጥጥር የላላና እስካሁን ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ነው ይላሉ፡፡
ኮሚሽኑ የኮንትሮባንድ መከላከል ሥራውን በ14 ቅርንጫፎች የሚያከናውን ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የገቢ ዕቃዎችን የኮንትሮባንድ ንግድ በቁጥጥር ሥር በማዋል የመጀመርያውን ድርሻ የያዘው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ነው፡፡ የሐዋሳና የጅግጅጋ ቅርንጫፎች ተከታታይ ደረጃቸውን ይዘዋል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የገቢ ዕቃዎች የኮንትሮባንድ ተግባር ውስጥ እነዚህ ቅርንጫፎች ቀዳሚውን ሥፍራ እንደያዙ መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡
ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ለትክክለኛ ግብር ከፋዮች የማበረታቻ ዕውቅናና ሽልማት በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተሰጠበት ወቅት፣ የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዳስታወቁት፣ በ2011 ዓ.ም. 198.2 ቢሊዮን ብር ታክስ ተሰብስቧል፡፡ ይሁን እንጂ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ሸቀጦች ስለመያዛቸውም አስታውቀው ነበር፡፡
በ2011 ዓ.ም. ስድስት ወራት ውስጥ በተካሄዱ የግብር ንቅናቄ ኩነቶች በኅቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩ 12 ሺሕ ነጋዴዎችን ወደ ግብር ሥርዓቱ ማስገባት መቻሉንም ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ከፍተኛ ታክስ ከፋይ ሆነው ነገር ግን በተጭበረበረ ሰነድና በሐሰተኛ ማስረጃ ግብር የሰወሩትን በስም በማጋለጥ፣ በኮንትሮባንድ ላይ በተካሄደ ዘመቻ ጭምር በርካታ ዕቃዎች መያዛቸውንም አስታውሰዋል፡፡