እነሆ መንገድ። ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ ልንወርድ ነው። ዱካው በማይመተረው መንገድ ዛሬም ልንጓዝ ነው። የእንጀራ ነገር ሆነና ሠልፍ ይዘናል። ዳዋ የሚበላው መሬት አጥቶ፣ ጎዳናው እግር በእግር ተጨናንቆ ሥጋ ላይ መብቀል ያስባል። እንዲህ ያለ ሐሳብ አለ ‘እኩይ ሐሳብ’ የሚባል። ሰውነት ሳይሸመግል ለጋነቱን የመንገድ ድውይ ይጫወትበታል። “ድኩማን” ይላል ተራ አስከባሪው። “ማንን ነው?” የወይን ፍሬ የመሰለች ሸጋ ልጅ ትጠይቃለች። “እኛን ነዋ። ማላገጡ ነው በእሱ ቤት፤” ይላታል ሪዙን እያፍተለተለ ከኋላዋ የቆመ ወጣት። “ድኩማን እባካችሁ ሠልፉን አስተካክሉት። አጣመማችሁት እኮ፡፡ ምሳ አልበላችሁም እንዴ?” የሠልፉ ጌታ። “ወቸው ጉድ። ደግሞ ብለው ብለው በሠልፍ አማካኝተው ሆዳችንን መሰለል አመጡ?” አንዲት ወይዘሮ ግራ እየተጋባች ትጠይቃለች። “መቼ እነሱ ናቸው መንገዱ ነው እንጂ፣ የማያሳየን የማያመጣብን የለ። እኛም ተሰብረን የማንታሽበት ጥግ የለ፤” ከወይዘሮዋ ፊት የተሰየመ ጎልማሳ ይናገራል።
ወዲያ ደግሞ አንዲት ጠምበለል በስልኳ ስታወራ እንሰማታላን። “ዘፈን ለመምረጥ ነበር የደወልኩት፤” ትላለች። “እሰይ! ያንችው ይሻላል አንደኛውን…” ሲል ጎልማሳው ጢማሙ ወጣት፣ “ቂልነት ነው እንጂ አሁን ለዘፈን ምርጫ በምናጠፋው ካርድ ፈንታ፣ አጠራቅመን በስንዴ ዱቄት ዳቦ ብንደፋበት ስንት ቀን አንበላውም?” ይላል። “አንተ ደግሞ መቼ እኛ ከተደፋንበት ተነሳንና ነው ዳቦ የምንደፋው?” አለችው የወይን ሐረጊቱ። “ . . . ደማም ሰው ደማም ሰው ስምህን ልዋሰው’ የሚለውን ጋብዝልኝ፤” የዘፈን ምርጫው ቀጥሏል። ይኼን የሰማ አንድ ዋዘኛ ጉረሮውን ጠራርጎ፣ “ማን ነው የሚያውሳት? ሰው ካልተደራጀ ለሥራ ማስኬጃ የሚያበድረው ቢያጣ በተናጠል ስም ወደ መዋስ ገባ እንዴ?” ይላል። “ስም ኑሮ ይሆናል እንዴ?” ብሎ አንዱ ቢጠይቅ “እንጃ!” እያለ ሁሉም ተከታትለው ወደመጡት ታክሲዎች በየተራ ተሳፈሩ። ዋስና ገላጋይ ያጣ ሁላ!
ጉዟችን ተጀምሯል። ወያላው ጋቢና የተሰየመውን ወጣት ያንገራግራል። “ከፈለግክ ወርደህ በባቡር መሄድ ትችላለህ፤” ይለዋል። “ብፈልግ በባቡር ብፈልግ በታክሲ ብፈልግ በፐብሊክ ሰርቪስ የመጓዝ መብቱ የእኔ ነው። ዕድሜ ለለውጡ መንግሥቴ። አርፈህ ሥራህን ሥራ። በሰው ምርጫ አትግባ፤” ይለዋል ወጣቱ ተሳፋሪ። “እግዚኦ! ብሎ ብሎ መንግሥት የግል ሆነ?” ወይዘሮዋ ናት ከሾፌሩ ጀርባ ተሰይማ የምታሽሟጥጠው። ከጎኗ ጎልማሳው አለ። “ምን ታደርጊዋለሽ? አንዳንዱ እኮ በብብቱ የሚታቀፈው እሳት ይሁን ውኃ አያውቅም፤” ሲላት መሀል መቀመጫ ከጎኔ የተሰየመችዋ የወይን አምባ፣ “ምናልባት ቅኔን ለባለ ቅኔ ቢተውት? እሳት ይለኮሳል፣ ውኃ ይቀዳል፣ ወይ ይደፋል እንጂ በብብት ይያዛል? እግዜር ያሳይህ እስኪ፤” ትለኛለች። ይኼን ስትል የሚሰማት ከጀርባችን የተሰየመ ተሳፋሪ ደግሞ፣ “ሁሉም ሰው የፈለገውን የመናገር ነፃነት አለው የእኔ እህት። የአለቃነትና የተቆጣጣሪነት መንፈስ ነው አንድም ዴሞክራሲያችንና የመናገር ነፃነታችን እንዳሰብነው እንዳያብብ እያደረገው ያለው፤” አላት። አንዳንዱ ደግሞ ምኑን ከምኑ እንደሚያገናኘው እንጃ!
“ይኼ የድኅረ ዘመናውያን ‘መንገዶች ሁሉ ሮም ያደርሳሉ’ ይሉት አስተሳሰብ እኮ በጠበጠን እናንተ!” ትላለች መጨረሻ ወንበር አንገቷ ላይ ስስ ጨርቅ የጠመጠመች ወጣት። “ልክ ምንድነው? ልክ እንዴት ያለ ነው?” እያለ ከጎኗ የተቀመጠ አውቆ አበድ መሰል ትክን ሲያደርጋት እያየ ወያላው፣ ‘የተሳፋሪዎቼን በሰላም የመጓዝ መብት የሚተናኮል ወደ ሠልፉ ይመለሳል’ እያለ የማስፈራርያ ጥቅስ ይጽፋል። “አታስፈራሩና! አንገት የደፋነው የምር መሰላችሁ እንዴ?” ይላል መጨረሻ ወንበር በጥግ በኩል የተቀመጠ። “ሰው ጨዋታ ጠፋበትሳ በአፉ የሚስተውና የሚያስተው በዛ፤” የምትለኝ ደግሞ ከጎኔ የተቀመጠችዋ ቀዘባ ናት። “የሚጨበጥ ነገር ሲጠፋ ታዲያ ምን ይደረግ?’ እንዳልላት ኋላ አጉል ተግባብቼ የምይዘው የምጨብጠው ባጣስ ብዬ ዝም። ያውስ እንዲህ የሚጨበጥ የሚያዝ ሲጠፋና ቆርጦ ቀጥሉን፣ የሰይጣን ተላላኪውንና ደም የጠማውን ዕብድ ሃይ የሚል በጠፋበት ጊዜ?! ኧረ ጎመን በጤና ያሰኛል!
“ሒሳብ ወጣ! ወጣ!” ወያላው በሙሉ ዓይኑ ለማየት ተፀይፎ ያጣድፈን ጀመረ። “አወይ ሥልጣን!” ይላል ከኋላ አንዱ። “ከላይ ካልተሰጠ በቀር ሥልጣን የለም’ ብለህ እመን ልጄ፤” ወይዘሮዋ መነሻውን በደንብ ሳታጣራ ታማታን ትጀምራለች። “አምነናል!” ይላል ወጣቱ በሽሙጥ። ወያላው ፈገግ እያለ፣ “ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ?” በሚል አስተኔያዊ ዕይታ እየገረፈን ሒሳቡን ይሰበስባል። “እንኳንም ግብር ሰብሳቢ አላደረጉህ፤” ትለዋለች ከጎኔ። ዘወር ብዬ ሳያት ጠቀሰችኝ። “እጅና እግር ይዘን እንዳልተፈጠርን ዕድሜ ልካችንን ወንበሩ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች ተጠያቂ ማድረግ መቼ ይሆን የምናቆመው?” ሲል ጎልማሳው፣ “ምነው ሆድን ዘለልከው?” ብሎ አንዱ ያስታውሰዋል። ‹‹ሆድ መስሎን የአዳምን ልጅ አውሬ አድርጎት ልቡን የነሳው…›› ትለኛለች ቀዘባዋ ጎሸም እያደረገችኝ፡፡ ዘንድሮ እኮ እህ ካሉ አናጋሪ በሽ ነው!
“ይኼው በሥራ እንዳንከበር በምግባር እንዳንመሰገን የሚያደርገን ማን ሆነና?” ሲለው፣ “እስኪ አሁን በሰው ቦርጭ ከመቅናት ሰው የራሱን አያይም?” ትላለች መጨረሻ ወንበር የተቀመጠችው። “ምን ትላለች? ምን አጠላለፈን ታዲያ? በታጋይነት ስም መስሎኝ ይኼው መንገዱ የመንታፊና የቀማኛ ብቻ ሆኖ የቀረው፤” ሲላት ደግሞ አጠገቧ የተሰየመው አኳኋኑ የሚያስፈራው ወጣት፣ “የጭቆናው ብዛት አይመስልህም የነፃነት ትግሉን ሜዳ ለጥጦ ጉድ የሠራን?” አለው። ወይዘሮዋ በስጨት ብላ፣ “አንዴ ሥልጣን ትላላችሁ፣ አንዴ እጅና እግር፣ አንዴ ደግሞ ሆድ፣ ደግሞ አሁን ነፃነትና ጭቆና። ወደ ገደለው ግቡ እንጂ፤” ከማለቷ ውቢት ከአፍዋ ተቀብላ፣ “መግደል ኃጢያት ነዋ፤” አለቻት። “የለም እንግዲያስ በቁም ማሰቃየትና ማስታመም ነዋ የሚሻለው? የት ሄጄ ልፈንዳ አሉ እማማ?” ብላ ወይዘሮዋ ተንተከተከች። ተሳፋሪው እየተያየ፣ ‹ለካ የሰው ልጅ በል ካለው ከብርቱካንነት ወደ ቦምብነት ይሸጋገራል?› እየተባባለ መሳለቅ ጀመረ። ስላቁ ቀርቶብኝ ከፍንጣሪው ባዳነኝ ማለት ይኼኔ ነው!
ጉዟችን ቀጥሏል። “ቅርብ ወራጅ አለ?” ወያላው ጠየቀን። ዝም፣ ዝም። “ደርቤባችሁ እስከ መጨረሻው ከምትጓዙ ንገሩኝ፤” አለ ደገመና። “ደርብብና። አዲስ ነገር ነው እንዴ መደረብ?” ቆንጅት መለሰች። “ደግሞ ዘመኑ የመጠጋጋትና የመተቃቀፍ ነው፤” ቀጠለች። ወያላው በመዳፉ መዝጊያውን ነረተና ታክሲዋን አስቆማት። በስልኩ የሚነጋገር አንድ ጎልማሳ ገባ። “እንዲያው ከየትም ብለህ አንድ ሰላሳ ሺሕ ብር የሚያበድረኝ ሰው ፈልግልኝ፤” ይላል። “ወይ! አንድ ሺሕ ብር ወረቀት በሆነበት ጊዜ ገንዘብ አበዳሪ ጠፋ?” ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመው ወጣት ነው። “የዘንድሮ ብር ንፋስ እንዳየ ዱቄት እንደሚበተነው መሰለህ የሚገኘው? እንደ አወጣጣችን መቼ ይገባና?” ይለዋል ከኋላ የተቀመጠ። “ሄዶ ሄዶ የት ነው የሚገባው ግን?” ስትል ‘ስካርፍ’ የጠመጠመችው፣ “የእኛን አትጠይቂም? ገንዘብማ ሲፈጥረው ኑሮው አየር ላይ ነው። ካላመንሽ አየር ወለዶቹን መጠየቅ ነው። ሥራ ፈጠራ እያሉ አየር በአየር ሲያጣፉ መሬት የረገጠው ገርጥቶ አለቀ፤” ይላታል። እንዲህ ነው እንግዲህ መጨረሻችን!
“የዘመኑ ልጆች መንግሥት ስታሳጡ መቼም የሚደርስባችሁ የለም። ዕውን የምንገረጣው አጓጓሉ መቀባባት የለመድነውን ‘ሎሽን’ ለመግዛት አቅማችን ቀንሶ ነው? ወይስ የመብላት አቅማችን ተዳክሞ?” ብትል ወይዘሮዋ ስልኩን ዘግቶ ጨዋታውን ሲያዳምጥ የቆየው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ “እንዴ?! ምራቃችንን ቱ ብለን አመዳችንን ለማበስም እኮ አልሆን ያለን ጊዜ ላይ ነን። ሎሽን የመጣው ልማት ከመጣ። ልማት ሳይመጣ ተፍተን የማንጨርሰው ምራቅ የት ደርሶ ነው አመዳችን ቡን ያለው አትሉም?” ብሎ አጦዘው። ይኼኔ ጋቢና ከተሰዩሙት ተሳፋሪዎች አንደኛው ጉሮሮውን ጠራርጎ እንትፍ ቢል ‹ቢያልፍለት ነው› ብሎ ተሳፋሪው ነውርን በዕድገት ተረጎመው። የትርጓሜውና የአንድምታው ብዛት አያምታታም? ጉድ እኮ ነው!
ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። “ወይ አዲስ አበባ!” ትላለች ወይዘሮዋ። “እንደ ቀልድ 139 ዓመት?” ብላ ስትገረም፣ “ምን ዘንድሮ እኮ ሰውም ከተማውም እኩል ዕድሜ መቁጠር ብቻ ሆነ። እንዲያውም የከተሞቹ ይሻላል ኧረ። እያደር ብሶብናል እኛማ፤” ሲል ጋቢና የተሰየመው ሳይታሰብ አወራ። “ምን ይላል ይኼ? ህያውን ከግዑዝ ጋር ያነፃፅራል እንዴ?” ጎልማሳው ያብዳል። “ዘመኑ የንፅፅርና የፉክክር ቢሆን ነዋ፤” ትላለች ቆንጂት። ወያላው በበኩሉ፣ “አዳሜ ባቡር ባቡር ብለሽ ባቡራችሁን አየንላችሁ። መሀል ወገቡን እንደ ተመታ እባብ እንደዚያ እየተጎተተ በዚህ የጥንቸሎች ዘመን የኤሊ ሞተር ገጥመው ተሳፈሩበት ሲሏችሁ እሺ ይባላል?” ይላል። “ታዲያ ምን ምርጫ አለ? የተገኘውን መጠቀም ነው፤” ስትል ወደ መጨረሻ፣ “ደግሞ አንሳፈርም በሉ እያላችሁ አድማ ማስመታት ጀመራችሁ? ቆይ፤” ብሎ አንዱ ወያላው ላይ ይዝታል። “ዛቻን ምን አመጣው?” ሲለው አንዱ ጠጋ ብሎ “ጥጋብ!” ይላል።
“እንዲህ በየመንገዱ እየተዛተብን እንዴት ነው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችን ሊጠበቅ የሚችለው?” ብሎ የቅድሙ ወጣት ሲጠይቅ “አቤት? ወዴት? በማለት እንጂ ‘ለምን? እንዴት?’ መሥራታቸውን እንጃ፤” ትላለች ወይዘሮዋ። “ወይ አዲስ አበባ። እዚህ አራዳ ላይ እዚህ ፒያሳ ሁሉ ነገር ተጀምሮ ዛሬ ማቆሚያ ጠፋ። በዚህ ቢሄዱ ግንባታ ነው፣ በዚያ ቢዞሩ ጥርጊያ ነው። መካብ ነው፣ ማፍረስ ነው። እንዴት ደስ ይላል ግን?” ሲል ጎልማሳው ቆንጂት ተራዋን ቀበል አድርጋ፣ “ምን ዋጋ አለው? ከተማው ሲቆረቆር ከነበረበት ቅርፅና ገጽታ ተቀየረ። ሰው ደግሞ ከተማዋን ሲቆረቁር ከነበረው መልካም ሥነ ምግባርና ይሉኝታ ፈቀቀ አለ። ቦታ ተቀያየርን። አዋክቦ መንጠቅ፣ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ሰብዓዊ ክብርን ማዋረድ፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ ጥጋበኝነት፣ ሴረኝነትና ክፋት ይኼው ይጫወቱብናል። ከተማው የሁላችንም የጋራ ቤት መሆን ሲገባው የራስ ለማድረግ አጥንት ላይ እንደሚናጠቁ ውሾች ላያችን ላይ ይፋጃሉ…” እያለች ሳለ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። ‹‹መጨረሻችን ባይሆን ኖሮ ደግሞ ስንቱን ያልተገራ አንደበት እንሰማ ነበር፡፡ ይህች ቆንጆ እንዲህ ያለ መልካም ነገር ስትናገር፣ ባልተገራ አንደበታቸው ጆሮአችንን የሚያጨቀዩት ደግሞ ይነሱብናል፡፡ ያልተገሩ አንደበቶች በዙ እኮ. . . ለጉድ የፈጠረን!›› ስትል ሌላዋ፣ የግድ ነውና በየአቅጣጫው ነጎድን፡፡ መልካም ጉዞ!