ከወሬው በመቀነስ ሥራው ላይ መበርታት ከተቻለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕምቅ ሀብትና ኃይል ተዓምር ማሠራት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያን የበደሏት ወደ ተግባር መመንዘር የማይችሉ አተካራዎችና ወንዝ የማያሻግሩ ወሬዎች ናቸው፡፡ ከበፊት ጀምሮ የሚሠሩ ሰዎች ቢከበሩ፣ ከምርታቸው በተጨማሪ ለሰብዕናቸው ዋጋ ቢሰጥና የሥራ ክቡርነት ታላቅ ወግና ማዕረግ ቢያገኝ ኖሮ፣ ከሚሠሩ ይልቅ የማይሠሩ አድርባዮችና አስመሳዮች ልቀው አይገኙም ነበር፡፡ የሥራ ክቡርነትን የተረዱ ሰዎችን ገንዘብ ሲያሳድዱ እንደሚውሉ ቀበኞች የማየት ልማድ፣ በኢትዮጵያ ምድር ከሚሠሩ ይልቅ ለሚያወሩ የተመቻቸ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ውጤቱ ግን ድህነት፣ ኋላቀርነትና ልመና ብቻ ነው፡፡ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ታታሪ ሰዎችን ማግኘት ባለመቻሉ፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅቶች የተሰማሩ ሰዎች ውጤት ከሚጠበቀው በታች የወረደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ በርካታ ማዕድናት፣ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦች፣ አመቺ የአየር ፀባዮች፣ ከሁሉም በላይ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል ይዛ ስንዴ ከውጭ ትገዛለች፣ ባስ ሲልም ትመፀወታለች፡፡ በአገር ውስጥ መመረት የሚገባቸው መሠረታዊ ሸቀጦች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ከውጭ ይገዛሉ፡፡ ከአፍሪካ በእንስሳት ሀብት አንደኛ ሆና ሥጋ፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ዓሳ፣ ወዘተ ብርቅ ናቸው፡፡ ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የሚሠሩ ቢከበሩ ግን ሥራ አለርጂክ አይሆንም ነበር፡፡
በፖለቲካው መስክም ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዴት ተስተካክሎ ዴሞክራሲን ማስረፅ ይቻላል ከማለት ይልቅ፣ የአገሪቱ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች በታሪክ መጥፎ ጠባሳዎች ላይ ውሎና አዳራቸውን አድርገው ይሻኮታሉ፡፡ ካለፉት ስህተቶች በመማር ዕርምት ከማድረግ ይልቅ፣ ስህተቶችን ለመድገም ይጣደፋሉ፡፡ ኢትዮጵያን ካለችበት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ በማውጣት የተሻለች አገር ማድረግ እየተቻለ፣ እርግማን ያለ ይመስል በቂም በቀል ዓይን መተያየት ይመረጣል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ችግር ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡ በአገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪኮች መሠረት፣ ብዙ አገሮች በርካታ ችግሮችን አልፈው ነው እዚህ የደረሱት፡፡ ጥፋቶችን እያረሙ፣ የተዛቡ የታሪክ አስተምህሮዎችን እያስተካከሉ፣ የተሻሉ ልምዶችን እያጎለበቱና አገርን እያስቀደሙ አገር ገንብተዋል፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ስለማይቀድም አገራቸውን በጋራ አሳድገዋል፡፡ ከወሬና ከአሉባልታ በመራቅ የሥራን ክቡርነት በመቀበላቸው፣ በቴክኖሎጂ ግስጋሴ ርቀው ተጉዘዋል፡፡ የጋራ እሴቶች፣ መስተጋብሮችና ፍላጎቶች እንዲጣጣሙ በማድረግ፣ በልዩነት ውስጥ አንድነት መፍጠር እንደሚቻል አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ እንዲህ ዓይነት ራዕይ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡
በሥራ ቦታዎችም በርካታ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማትና በግል ድርጅቶች ውስጥ ከሚሠሩ ይልቅ የማይሠሩ ከፍተኛ ቦታ ያገኛሉ፡፡ አንደበታቸው ጥሬ የሚቆላ አስመሳዮች ምንም ዓይነት ውጤታማ ሥራ ሳያከናውኑ አንገታቸውን ደፍተው የሚሠሩ ትጉሃን በሥልጣንም፣ በጥቅምም ሆነ በሌሎች ነገሮች ይበልጣሉ፡፡ የትጉሃን ዋጋ እያነሰ የአስመሳዮቹ ከፍ እያለ ብዙዎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ለአገሩና ለወገኑ እያሰበ የሚሠራው ከጀርባ በሴረኞች እየተዶለተበት፣ አስመሳዩ ግን ለሹመትና ለተሻለ ነገር ይታጫል፡፡ የሥራ ባህል አለርጂክ የሆነባቸው ግለሰቦች ወይም ስብስቦች ትጉሃንን ተስፋ ሲያስቆርጡ ዝም ይባላል፡፡ ብዙ መንግሥታዊ ድርጅቶች ውስጥ ሥራን በአግባቡ ከማቀላጠፍ ይልቅ፣ በደንብና በመመርያ እያሳበቡ አይቻልም ማለት ቀላል ነው፡፡ ይቻላል በማለት ለሥራ የመነሳት ወኔን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የማያሠራ ደንብና መመርያ እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ ማቅረብ አይፈለግም፡፡ መሥራት ተጠያቂነት ያለበት ጭምር በመሆኑ፣ ባለመሥራት ተጠያቂነትን መሸሽ የዘመኑ ፋሽን ነው፡፡ በግል ድርጅቶችም የሚሠራ ሰውን ደካማ ጎን እየፈለጉ ለበላይ አካል ማሳጣትና ሥራን ማሽመድመድ፣ የአስመሳዮችና የአድርባዮች ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ ከግላዊ ጥቅምና ዝና ያለፈ ጭንቀት የሌለባቸው ደካሞች አደባባዩን ስለሞሉት፣ የሥራ ሰዎች ግን እየተሸማቀቁ ይኖራሉ፡፡ ተስፋ እየቆጠሩም አማራጭ ይፈልጋሉ፡፡
የመሥራት ባህል አለመዳበር የጎዳው ግን አገርን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዕለት ዕርዳታ ጥገኛ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ በቀን አንድ ጊዜ የረባ ምግብ የማያገኙ ሰዎች ቁጥር ከዕርዳታ ፈላጊዎቹ ይልቃል፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፡፡ ሥራ አጥነቱ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው፡፡ በከተሞች ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት መጠኑ በጣም እየጨመረ ነው፡፡ የውጭ ብድር ዕዳ አገሪቱ አናት ላይ ያናጥራል፡፡ አሁንም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ነው፡፡ ብዙዎቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአቅም በታች ነው የሚያመርቱት፡፡ የአገሪቱ ግብርና የምግብ ዋስትናን አላረጋገጠም፡፡ የሕዝብ ቁጥር ከመጠን በላይ እየጨመረ ከመሆኑም በላይ፣ ከተሞች ሥራ በሌላቸው ዜጎች እየተጥለቀለቁ ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ሥራና ሠራተኞችን ማገናኘት ይገባል፡፡ ምርታማነትን ማሳደግ የግድ ይላል፡፡ አገር የምታድገውና የምትበለፅገው በወሬ ሳይሆን በሥራ ብቻ ነው፡፡ ለሥራ ቅድሚያ ካልተሰጠ ከባድ ችግር አለ፡፡ ኢትዮጵያ የሚሠሩ እንጂ ወሬ ላይ የተጣዱ አስመሳዮች ምንም አይፈይዱላትም፡፡
ከችግሮቹ በመለስ ግን ተስፋ እንዳለ መዘንጋት አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ ከተሠራባት እንኳን ለራሷ ለአፍሪካም ትተርፋለች፡፡ በሁሉም መስክ የሚሠሩ ከተከበሩ ሥራ ፈጣሪዎች ይበዛሉ፣ ሀብት ይትረፈረፋል፣ ድህነት በእርግጥም ታሪክ ይሆናል፡፡ የሚሠሩ ካልተከበሩ ግን ከምኞት የዘለለ ውጤት አይገኝም፡፡ ከአጉል ምኞት በመውጣት ተስፋ መሰነቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ተስፋ እንዲለመልም ግን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመላቀቅ ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዘዴ ያለው በሥራ ውስጥ ነው፡፡ ሥራ ክቡር ነው፣ የሚሠራም ምሥጉን ነው መባል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የጎደላት ከፍተኛ የሆነ የሥራ ባህል ነው፡፡ የሥራ ባህል ሲኖር ፖለቲካውም፣ ኢኮኖሚውም ሆነ ማኅበራዊው ጉዳይ በሙሉ በቀና መንገድ ይጓዛል፡፡ አብሮ ከመብላት በተጨማሪ አብሮ መሥራት ይለመዳል፡፡ አብሮ መሥራት ሲቻል የተባበረ ኃይል ይፈጠራል፡፡ ይህ የተባበረ ኃይል ውጤቱ ከፍተኛ ስለሚሆን ከፍተኛ ትርፍ ይገኛል፡፡ የአፈጻጸም ድክመት አይኖርም፡፡ መለገም አይታሰብም፡፡ አድርባይነትና አስመሳይነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ወሬ፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ጭፍን ጥላቻና ድጋፍ፣ ቂም በቀል፣ ክፋት፣ ሴራ፣ አሻጥር፣ ወዘተ ከሥራቸው ተመንግለው ይወድቃሉ፡፡ በሁሉም መስኮች የሚሠሩ ይከበሩ!