Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የዋጋ ግሽበትን በጥንካሬ መቆጣጠር መቻል ያስፈልጋል›› አቶ ሚካኤል አዲሱ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

አቶ ሚካኤል አዲሱ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢንቨስትመትና በፋይናንስ ዘርፎች የአካዴሚና የሥራ ዓለም ተሞክሮዎች አካብተዋል፡፡ አቶ ሚካኤል የዓለም ባንክ የፋይናንስ አስተዳደር ስፔሻሊስት፣ እንዲሁም የፋይናንስ አስተዳደር አማካሪ በመሆን ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ፣ የዓለም ባንክ ድጋፍ የሚሰጥበትን የሴፍቲኔት ፕሮግራም በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የሚያደርግ አሠራር በመንደፍና በመምራት ጭምር መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ ዘመን ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ፈርስት ኮንሰልት፣ ካፒታሊንክ በተሰኙ ተቋማትና በሌሎች፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ መምህርነት ጭምር በተለያዩ የኃላፊነት መደቦች አገልግለዋል፡፡ ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከ200 በላይ ባለአክሲዮኖችን በማሰባሰብ ንሥር ማይክሮ ፋይናንስ የተሰኘውን አነስተኛ የገንዘብ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት በመመሥረትና በቦርድ አመራርነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ሚካኤል፣ በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ አገልግሎት ለፋይናንስ ዘርፉ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት ያልቻለውን 75 በመቶ ሕዝብ በቀላሉ ለአገልግሎቱ ተደራሽ ማድረግ የሚቻለውም፣ በዚህ መንገድ እንደሆነ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች በየዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ ተቀናቃኝ እንዳልተገኘላቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ ትርፋቸው በባለሙያዎችና በሌሎችም ዘንድ ትችት ቢሰነዘርበትም፣ አቶ ሚካኤል ግን የኢትዮጵያ ባንኮች በብር የሚያተርፉት መጠን፣ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አኳያ ሲታይ እንደሚታሰበው የተጋነነ እንዳልሆነ ሞግተዋል፡፡ ባንኮች የሚያስመዘግቡትን ትርፍ ብቻም ሳይሆን፣ የሚያበድሩበት ዘርፍ የተመረጠ መሆኑም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ይሁንና የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አሁን ስለደረሰበት ደረጃ፣ በዘርፉ ስለሚታዩ እክሎች፣ የፋይናንስ ተቋማት ስለሚያሰባስቡት ሀብትና የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነት ላይ ስለሚነሱ ጉዳዮች አቶ ሚካኤል ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፋይናንስ ኢንዱትሪ ውስጥ አብዛኛው የፋይናንስ አቅርቦት ለሚፈለገው ዘርፍም ሆነ ለሚያስፈልገው የኅብረሰተብ ክፍል ተደራሽ አይደለም ይባላል፡፡ በጥቅሉ ኢንዱስትሪውን እንዴት ይገልጹታል? ከየት ተነስቶ የት ደርሷል?

አቶ ሚካኤል፡- የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን አራት ተቋማት የያዘ ነው፡፡ ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንሶች፣ ኢንሹራንሶችና ለካፒታል ዕቃዎች በሊዝ የሚያበድሩ ኩባንያዎችን ያካትታል፡፡ ኢንዱስትሪው ረዥም መንገድ ተጉዞ መጥቷል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት የኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ያለውን ብናይ እንኳ፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የባንክ ኢንዱስትሪው ሀብት መጠን በአሥር እጥፍ አድጓል፡፡ በዚህ ሦስት ዓመት እንኳ፣ አጠቃላይ ባንኮች የሚያንቀሳቅሱት ሀብት ወደ ሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ ይህ በመጠን ብቻም ሳይሆን የፋይናንስ ሀብት የኢኮኖሚው ነፀብራቅም በመሆኑ ጭምር የሚታይ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት በዋናነት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ ገንዘብ ነው፡፡ ገንዘቡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ መሽከርከር አለበት፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ጉብዝና ብቻም ሳይሆን፣ ራሱ የኢኮኖሚው ማደግ የፋይናንስ ዘርፉንም ይዞት ስለሚነሳ ያሳድገዋል፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ትልቁ ስኬት ተብሎ የሚጠቀሰው ዋናው ለውጥ በቁጠባ ማሰባሰብ ላይ መንግሥት የተከተለው ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረገው ሩጫ፣ እንዲሁም የግል ባንኮችም ይኼንን ተከትለው ያደረጉት የቅርንጫፍ ማስፋፋት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡

የዛሬ አሥር ዓመት ቁጥራቸው 500 አካባቢ የነበሩት የባንኮች ቅርንጫፎች፣ ዛሬ ወደ 4,700 ደርሰዋል፡፡ የቆጣቢዎችን ቁጥር ስናይም በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን የሚደርሱ ደንበኞች የባንክ ሒሳብ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ከዚህ ውስጥ ተደጋጋሚውን በግማሽ እንኳ ብናወጣ ከ15 ሚሊዮን ያላነሱ ሰዎች የባንክ ሒሳብ አላቸው፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ወደ ችግሩ ስንመጣ ግን የተሰበሰበው ገንዘብ በምን መንገድ ለምን ተግባር ዋለ የሚለው ላይ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ገንዘቡ ከተሰበሰበ በኋላ ለአገር ዕድገትና ለዜጎች ለውጦች፣ እንዲሁም በፍትሐዊነት የሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ አከፋፍሏል ወይ የሚለውን ካየን ትልቅ ጥያቄ ምልክት እናስቀምጣለን፡፡ ምክንያቱም ቁጠባው በተለይ ከባንኩ ዘርፍ ከሚሊዮን ዜጎች ከተሰባሰበ ገንዘብ የተገኘ ሀብት ነው፡፡ ብድር ያገኙት ግን ግማሽ ሚሊዮን የማይሞሉ ግለሰቦችና የንግድ ተቋማት ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የፍትሐዊነት ክፍፍል ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ሌላው መንግሥት በፖሊሲ ቅድሚያ የሰጠው የተሰበሰበውን ሀብት፣ ለረዥም ጊዜ ሥር የሰደደ የመሠረተ ልማትና ሌሎችም ትልልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ሥራዎች ስላሉብኝ ለእነዚህ ማዋል አለብኝ በማለት የተሰበሰበውን ገንዘብ ኢንቨስት አደርጎታል፡፡ ይህ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን ኢንቨስት የተደረገባቸው መስኮች የታቀደላቸውን ዓላማ አሳክተው የወጣባቸውን ወጪም መልሰው፣ በገንዘብም ሆነ በአኗኗር ደረጃ ለሕዝቡ ዋጋውንና ውለታውን ከፍለውታል ወይ የሚለውን ስናይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ቁጠባን ካነሳን አይቀር ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ከሕዝቡ የተሰበሰበው የቁጠባ መጠን ከ24 በመቶ በላይ ነው፡፡ ይሁንና በፋይናንስ ረገድ፣ በተለይም ከገንዘብ ተጠቃሚነት በመነጨ ለመቆጠብ የሚደረገው እንቅስቃሴና መጠኑ ግን ይህ ነው የሚባል አይደለም የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ሚካኤል፡- ቁጠባን በሁለት ብንከፍለው አንደኛው የፈቃደኝነት ቁጠባ የምንለው ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ተቋም ዛሬ ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ ወደፊት የተሻለውን አጥንቼና ዓይቼ በማለት ገንዘቡን ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ ባንክ ያስቀምጠዋል፡፡ ሁለተኛው ቁጠባ ደግሞ የግዴታ ቁጠባ ነው፡፡ ይህም ለጡረታና ለመድን ዋስትና የሚደረግ የቁጠባ ዓይነት ነው፡፡ ምናልባት የውዴታ ግዴታ ቁጠባ የምንለውና ለቤት መግዣ በተለይም ለቁጠባ ቤቶች መግዣነት፣ ለመንገድ ፈንድና ለመሳሰሉት ጉዳዮች የምንቆጥበው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛው የቁጠባ ዓይነት ነው ያደገው ቢባል፣ ይህ ነው ተብሎ በግልጽ የሁለቱን ለይቶ የሚያሳይ ጥናት እስካሁን አላየሁም፡፡  ነገር ግን አንድ ሰው ስለቆጠበ ሕይወቴ ይለወጣል ብሎ መነሳት የለበትም፡፡ ቁጠባ ማለት ሌላ ሥራ እየሠራሁ ገንዘቤ ግን ይቀመጥልኝ የሚል ሐሳብ ያዘለ ነው፡፡ ያንን ገንዘብ ወስዶ የሚነግድበት ሰው ግን ሊቀየርበት ይችላል፡፡ ሌላ ሥራ እየሠራ ገንዘቡን ወደ ጎን አድርጎ እየቆጠበ የሚቆይ ሰው ሕይወቴ ለምን አልተቀየረም ብሎ ቅሬታ ቢያሰማ፣ ፍትሐዊነት አይኖርም፡፡ ቢያንስ ያስቀመጠው ገንዘብ ዋጋው ተጠብቆ ሊቆይለት ግን ይገባል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ክፍተት በተለይም የዋጋ ግሽበቱ ገንዘቡን ሳስቀምጥ ከማገኘው ወለድ በላይ ከሆነ ምጣኔው ያከስረኛል፣ አንድ ሚሊዮን ብር አስቀምጬ ምናልባት 70 ሺሕ ብር ላገኝበት እችላለሁ፣ ያስቀመጥኩት ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ሲታይ ግን ወደ 500 ሺሕ ብር ወርዶ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ሚሊዮን ብር የሚሸጠው ዕቃ ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ካሻቀበ፣ ያስቀመጥኩት ገንዘብ ዋጋም በግማሽ ቀንሷል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በዋጋ ግሽበቱና ከቁጠባ የሚገኘው በወለድ ምጣኔ ገቢ ላይ የሚታየው ትልቅ ክፍተት እየታየበት ነው፡፡ የፈቃደኝት ቁጠባ አሁን በብዛት ወደ መቀነሱ አቅጣጫ እያመራ ነው፡፡ ሕዝቡም ይህንን ማወቅ አለበት፡፡ ከቁጠባ በሚገኝ በወለድ ብቻ ሕይወቴ ይቀየራል ማለት የማይሆን ነው፡፡ ነገር ግን ቢያንስ የዋጋ ግሽበቱን የሚመጥን ወለድ መታሰብ አለበት፡፡ ወለድ መጨመር ብቻም ችግሩን አይፈታውም፡፡ የዋጋ ግሽበት የግድ መስተካከል መቻል አለበት፡፡ የዋጋ ግሽበትን በጥንካሬ መቆጣጠር መቻል ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ባንኮች ስንጥቅ አትራፊዎች ናቸው ይባላሉ፡፡ እርስዎ ግን ከአፍሪካ አኳያ ሲታዩ እንደሚታሙት ስንጥቅ አያተርፉም ብለዋል፡፡ ነገር ግን የሚያበድሩባቸው መስኮች የተመረጡና ለትርፍ የሚመቹ ናቸው ይባላል፡፡ ከትርፋቸው ባሻገር ትርፍ የሚያሰባስቡባቸው የኢኮኖሚ መስኮችስ እንዴት ይታያሉ?

አቶ ሚካኤል፡- ባንኮችን ማየት ያለብን የግለሰቦችና የተቋማት ጥርቅም እንደሆኑ አድርገን ነው፡፡ የአክሲዮን ድርሻ በመያዝ ባንኮችን የሚመሠርቱት ግለሰቦችና ተቋማት ናቸው፡፡ እኔ እንደ አንድ ግለሰብ የሥጋት አደጋው የጨመረና ትርፋማነቱ የቀነሰ ነገር ወይም ደግሞ ቀላል፣ የአደጋ ሥጋቱ ዝቅ ያለና አትራፊነቱ ከፍተኛ ከሆነው ዘርፍ ምረጥ ብባል የበለጠ ወደሚያተርፈውና ትንሽ አደጋ ወዳለው ወዲያውኑ ማዘንበሌ የማይቀርና ተፈጥሯዊም ነው፡፡ ባንኮችም ይህንኑ ነው እያደረጉ ያሉት፡፡ የረዥም ጊዜ ብድር በርካታ የአደጋ ሥጋት ያለበት ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ግብርና ማኑፋክቸሪንግ ወይም ፋብሪካ ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ላይ የሚውለው ብድር፣ ከአጭር ጊዜ ብድር ወዲያው ተወስዶ ዕቃ ከውጭ መጥቶበት ወይም  ከዚህ ተገዝቶ ወይም ደግሞ ከሕንፃ ኪራይ የሚገኝ ገቢ ላይ ሊገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ሲታይ፣ አማራጩ በቀላሉ ገንዘቡ ተቀንቀሳቅሶ ጥቅም ወደሚያስገኘው ዘርፍ ላይ የሚውለው ብድር ነው ሚዛኑን የሚጫነው፡፡ የአጭር ጊዜ ብድር ፍላጎት ገና አልተሟላም፡፡ ባንኮችም ሆኑ ሌሎች እንደ ማይክሮ ፋይናንስ ያሉ አበዳሪ ተቋማት፣ የዚህ ዘርፍ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ በቀላሉ ወደዚህ ዘርፍ ያተኩራሉ፡፡ ጥቅሙም የሥጋት መጠኑም ከረዥም ጊዜ ብድር አኳያ የተሻለ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ይህንን በማድረጋቸው ማትረፍ ችለዋል፡፡

ነገር ግን ትርፋቸው ከዋጋ ግሽበቱ አኳያ በብር ስለሆነ የሚያተርፉት አሁንም ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚያደረግባቸው ስለሆኑ፣ በሌሎች የኢኮኖሚው መስኮች አስተማማኝ የአክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረጉ እንደ ባንኮች አስማማኝ ስለማይሆን በማለት፣ አብዛኛው ሰው ባንኮች ውስጥ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ ሌላው አማራጭ ገንዘብ መቆጠብ ስለሆነም በዚህም ባንኮች የተሻለ አትራፊዎች ናቸው፡፡ ይህ ትርፍ ግን ከዋጋ ግሽበት አኳያ ሲታይ፣ ከሌሎች ተመሳሳይ የአፍሪካ ባንኮች ጋር ሲተያይ ‹‹ሪተርን ኦን ኢኩቲ››፣ ‹‹ሪተርን ኦን አሴት›› በሚባሉት መለኪያዎች ሲመዘን፣ ለአብዛኛው ሰው እንደሚመስለው ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ ትርፍ አያተርፉም፡፡ ካሉን አማራጮች አትራፊ፣ ከደኅንነት አኳያ ካሉት የንግድ ዘርፎች ደህና የሚባሉት ባንኮች መሆናቸው የማይካድ ነው፡፡ አትራፊነታቸውም ጥርጥር የለውም፡፡ በየዓመቱ በ30 እና በ40 በመቶ እያደጉ የመጡትም በአትራፊነታቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አትራፊነታቸው ግን ብሔራዊ ባንክ ከእያንዳንዱ ብድር ላይ የ27 በመቶ ቦንድ እንዲገዙ በሚያስገድድበት፣ ከሚሰጡት ብድር ቀንሰው ለመጠባበቂያ በማስቀመጥ፣ የተበላሸ ብድር ጣሪያና ሌሎችም ማሟላት የሚጠበቅባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ታክለው ነው እያደገና እየተስፋፋ የመጣው፡፡ ይህስ እንዴት ይታያል?

አቶ ሚካኤል፡- መንግሥት በፖሊሲ ምክንያት ባንኮች ላይ የገንዘብ ጫና ማድረግ ከጀመረ በኋላ ባንኮች ትርፋማነታቸው ሊቀንስ ነው፣ ሊከስሩ ነው፣ አደጋ ውስጥ ገቡ በሚባልበት ጊዜ ለሁሉም በሚያስገርም ሁኔታ አትራፊ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ አንዱ ምክንያት ቅድም እንደ ጠቀስኩት የኢኮኖሚው መስፋፋትና ማደግ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ ቢያስቀምጥም፣ ኢኮኖሚው ግን በየዓመቱ በአሥር በመቶ ሲያድግ ነበር፡፡ ስለዚህ ባንኮቹ የ27 በመቶ የቦንድ ጫና ቢኖርባቸውም፣ ሌላ የሚገፋቸው የአሥር በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ድጋፍ ነበራቸው፡፡ ከአስቀማጮች የተሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ላይ የታየው ለውጥም አግዟቸዋል፡፡ ለባለ አክሲዮኖችና ለሠራተኞች በቂ ክፍያ እየከፈሉ ለመቀጠል፣ በብሔራዊ ባንክ በኩል የሚሾልክባቸውን ገንዘብ በሌላ መንገድ ማካካስ አስፈልጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ቁጠባ ነው፡፡ በሰፊው ወደ ቁጠባ ሥራ በመግባት በአማካይ ከ25 እስከ 30 በመቶ የቁጠባ ዕድገት አሳይተዋል፡፡ ይህ ዕድገት ላለፉት ሰባት ወይም ስምንት ዓመታት ሲታይ ነበር፡፡

ስለዚህ በአንዱ የተቀነሰባቸውን በሌላው እያካካሱ ወደ ቁጣባ በሰፊው መሄድ ችለዋል፡፡ የቦንድ ግዥው ግዴታ ባይጣልባቸው ኖሮ ምን ያህል ሊያተርፉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ሌላው አቅጣጫ በኢትዮጵያ ሕግ የማበደሪያ ከፍተኛ ጣሪያና ዝቅተኛው ወለል መጠን አልተቀመጠም፡፡ ስለዚህ አበዳባሪ ተቋማቱ በአንዱ በኩል የተጎዱ ወይም የሚቀንስባቸው ሲመስላቸው የሚያስክፍሉት ወለድ ላይ አንድ ወይም ሁለት በመቶ ጭማሪ ጣል እያደረጉ በማካካስ፣ ትርፋማነታቸውን ለማስቀጠል ወይም የበለጠ እንዲጨምር ያደርጉታል፡፡ ለዚህ ነው ዝቅተኛው የቁጠባ ወለድ ምጣኔ ከቀድሞው የአምስት በመቶ መጠን ወደ ሰባት በመቶ ከፍ የተደረገው፡፡ ይህ በመደረጉ ግን አበዳሪዎቹ የሚያበድሩበትን የወለድ ምጣኔ በሁለት በመቶ እንዲጨምር አድርገዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክ የሚወሰድባቸው ሀብት መጠን ሲጨምር የማበደሪያቸውን ወለድ ከፍ በማድረግ ትርፋማነታቸውን አስቀጥለዋል፡፡ ስለዚህ የገንዘብ መስፋፋትና የዋጋ ማስተካከያ ዕርምጃዎች እየታዩ ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ከወለድ አኳያ ሌላው ነጥብ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የመሳሰሉ ተቋማት የሚያቀርቡት የማስተካከያ ዕርምጃ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ወለድን የሚያስተዳድርበት አግባብ ገበያ መር ይሁን ይላሉ፡፡ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ቁጥጥር የሚደረግበት የወለድ ምጣኔን ይከተላል፡፡ ይህ መሆኑ ለዋጋ ግሽበትና ለሌሎችም መሠረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት ነው በማለት ይጠይቃሉ፡፡ እነ አይኤምኤፍ ወለድ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ እንዴት ያዩታል?

አቶ ሚካኤል፡ዓለም አቀፍ ተቋማት በአጠቃላይ ጽንሰ ሐሳባቸው አብዛኛው ነገር በገበያ እንዲመራ ይደረግ የሚል ነው፡፡ የገንዘብ አገልግሎት እንደ ማንኛውም ምርት ሸቀጥ ነው፡፡ መሸጫና መግዣ ዋጋ አለው፡፡ ለቁጠባ የምንከፍለው መግዣ ዋጋ ነው፡፡ አበድረን የምናስከፍለው ደግሞ መሸጫ ዋጋ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም በገበያ ይመራ ነው ጥያቄው፡፡ መሸጫ ዋጋው ወይም የብድር ወለዱ በገበያ ነው የሚመራው፡፡ የቁጠባው ግን አስቀማጩ ያስቀመጠውን ገንዘብ ማጣት ስለሌለበትና ጥበቃም ስለሚያስፈልገው፣ ብሔራዊ ባንክ የራሱን ምጣኔ አስቀምጧል፡፡ ይህ ግን ሙሉ ለሙሉ ለገበያ ይለቀቅ ከተባለ ግን፣ ቢያንስ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይስተካከሉ ለገበያ ዋጋ ክፍት ማድረጉ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ተፅዕኖዎች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድመ ሁኔታዎቹ ምንድን ናቸው?

አቶ ሚካኤል፡- ከቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት ነው፡፡ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ መስተካከል አለበት፡፡ ከባንክ ብድር ውጪ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮች መኖር አለባቸው፡፡ እንዲህ ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ነክ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ካልቻሉ፣ የቁጠባ ዋጋ ወይም ወለድ ወደ ላይ ሲጨምር የማበደሪያውም ዋጋ ይጨምራል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ድጋሚ ወደ ሌላ የዋጋ ግሽበት መግባትን ያመጣል፡፡ በግሌ በቁጠባ ወለድ ላይ የዋጋ ወለል መቀመጡ ገበያውን ያን ያህል ጎድቶታል ብዬ አላስብም፡፡ እንዲያውም በበርካታ መስኮች የፋይናንስ ዘርፉ ጥብቅ ቁጥጥር ቢኖርበትም፣ በወለድ ምጣኔ ላይ ግን የብሔራዊ ባንክም ሆነ የመንግሥት ፖሊሲ ክፍትና ለገበያ የተተወ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡– በአገሪቱ በርካታ የግል ባንኮችና የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት አሉ፡፡ የማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶችም በርካታ ናቸው፡፡ ዕቃ በማቅረብ የኪራይ ብድር የሚሰጡ ኩባንያዎችም እየተበራከቱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት የቻለው ሕዝብ ቁጥር 20 በመቶ ገደማ ነው፡፡ ባለፉት 20 እና ከዚያም በላይ ዓመታት ይህን ያህል አነስተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የገንዘብ አገልግሎት ማግኘቱ እንዳለ ሆኖ፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት አሁን ባለው ሁኔታ ነገሮች ከቀጠሉ፣ መበደኛ የፋይናንስ አገልግሎት ያላገኘው ሕዝብ ቁጥር ምን ያህል ሊሆን ነው?

አቶ ሚካኤል፡- አሁን 38 ለአነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶች ገንዘብ የሚያቀርቡ የገንዘብ ተቋማት አሉ፡፡ 18 የግልና የመንግሥት ባንኮች፣ እንዲሁም በርካታ የመድን ኩባንያዎችና ሰባት ያህል የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ የቁጥራቸው መብዛት አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የቁጥራቸው ብዛትና አካታች የገንዘብ አገልግሎት ተደራሽነት ሲታይ ይህ ነው የሚባል ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም፡፡ በተለይ በግል የሚቋቋሙት የፋይናንስ ተቋማት ለትርፍ የሚቋቋሙ በመሆናቸው፣ አካሄዳቸውን የሚያደርጉት ከፍተኛ ትርፍ ወደሚያገኙበትና ዝቅተኛ የአደጋ ሥጋት ወዳለበት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አዋጭ ዘርፍ በብዛት የሚገኘው ከተማ አካባቢ ነው፡፡ ከተማው ላይ የገንዘብ አገልግሎት ተደራሽነት ጥያቄ ብቻም ሳይሆን፣ ቅርንጫፎችና የገንዘብ አገልግሎት ሰጪዎች መበራከት የሚያስፈልግበት ወቅት ነው፡፡ በዋና ዋና ከተሞች ይህ መስፋፋት አለበት፡፡ ትልቁ ነገር የአዳዲስ ተቋማት መምጣት ሳይሆን፣ ምን ዓይነት ተቋማት ምን ዓይነት ቴክኖሎጂና ስትራቴጂ ይዘው ይመጣሉ የሚለው ነው መሠረታዊ ጉዳይ፡፡ መበደኛ የገንዘብ አገልግሎት ተጠቃሚው ሕዝብ ቁጥር ከ22 እስከ 25 በመቶ ይደርሳል ከተባለ፣ የቀረው 75 በመቶ በአብዛኛውና በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በጣም ሩቅ በሆኑ፣ እምብዛም የመሠረተ ልማት መስፋፋት በሌለባቸው፣ መረጃና ቴክኖሎጂ ባልተዳረሰባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ነው፡፡

ስለዚህ ወደ እነዚህ አካባቢዎች በመሄድ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም አለ ወይ? በመቋቋም ላይ የሚገኙ ወደ አሥር የሚጠጉ አዳዲስ ባንኮች አሉ፡፡ እነዚህ ወዴት ይሄዳሉ? መደበኛ አገልግሎት ማግኘት ያልቻለውን የሕዝብ ክፍል ያዳርሳሉ የሚለው ብዙም የሚሆን አይመስልም፡፡ ይልቁንም ወደፊት የት ይደርሳል ለሚለው፣ መንግሥት በአገር አቀፍ ስትራቴጂውና በፖሊሲው አካታችና ተደራሽ የገንዘብ አገልግሎት የሚያገኘውን ሕዝብ ቁጥር ወደ 80 በመቶ የማድረስ ዕቅድ እንዳለው አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ዋናና ሥር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ነው፡፡ ቅርንጫፍ በማስፋፋት ብዙም የሚዘለቅ አይደለም፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶች እስከ 5,000 የሚደርሱ ቅርንጫፎች አሏቸው፡፡ በተለይም የመንግሥቶቹ በአብዛኛው በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡ ባንኮችም 5,000 ገደማ ቅርንጫፎች አሏቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን 10,000 ቅርንጫፎች ወደ 20,000 ብናሳድጋቸውም፣ የኢትዮጵያ ቀበሌዎች ብዛት 20,000 በመሆኑ፣ በአንድ ቀበሌ አንድ ቅርንጫፍ ብቻ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህም ቢደረግ ገጠራማ አካባቢ ያለው ነዋሪ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር በእግሩ ተጉዞ ወደ መደበኛ የፋይናንስ ተቋማት በመሄድ አገልግሎት ማግኘት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ከቀበሌ አካባቢ ርቆ የሚኖረው ሰው አገልግሎት በአቅራቢያው ማግኘት ይቸግረዋል፣ አንደርስበትም፡፡

ስለዚህ አሁን ዓለም በሙሉ እየሄደበት የሚገኘው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ማስፋፋት ላይ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከ40 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ደንበኞች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል 30 ሚሊዮኖቹ በስልካቸው በሚመቻቸውና በራሳቸው ቋንቋ አገልግሎቱን እያገኙ ነው፡፡ ይህ በሌሎች አገሮች ባንክ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ በሞባይል ቴክኖሎጂ ወይም ቅርንጫፍ አልባ በሆነ የባንክ አገልግሎት 40 በመቶውን ሕዝብ ማዳረስ ይቻላል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቴክኖሎጂ ካልመጣ በቀር መሠረተ ልማቱ እስከ ጥግ እስኪስፋፋና እስኪዳረስ መጠበቅ ሊኖርብን ነው ማለት ነው፡፡ መንገድ፣ መብራት፣ ውኃና ሌላውም እስኪስፋፋ መጠበቁ ግድ ይሆናል፡፡ በቴክኖሎጂ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊውን ሕዝብ ማግኘትና ማዳረስ ስለሚቻል፣ ከዚህ ውጭ አካታችና ሰፊ ተደራሽነትን የሚያመጣ የፋይናንስ አገልግሎት ይዘረጋል፣ ይሳካል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሀብት ሳይነካ ተከድኖ እየኖረ ነው ማለት ነው?

አቶ ሚካኤል፡ ሙሉ በሙሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ከማይክሮ ፋይናንስና ከባንክ ጋር እንዲተሳሰሩ ተደርጎ የተወሰነውን ክፍል ማዳረስ ተችሏል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለውን 75 በመቶ መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት ያልቻለ ሕዝብ ብዛት በ20 ወይም በ30 በመቶ ዝቅ ለማድረግ፣ አሁን ባለው ሁኔታና የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳየው ቴክኖሎጂ አዋጭ ተኮር አገልግሎት ላይ ማተኮሩ የግድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአገሪቱን የመሠረተ ልማትና የኑሮ ሁኔታ ዕድገት እስኪቀየር መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ዕውን እስኪሆን ድረስ ግን ምንም በማያሻማ ሁኔታ፣ አብዛኛውን መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት ያልቻለውን ሕዝብ ማዳረስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች...