Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበደመራ በዓል የፓትርያርኩ ማሳሰቢያ

በደመራ በዓል የፓትርያርኩ ማሳሰቢያ

ቀን:

የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማና በመላ አገሪቱ ዓርብ መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በታላቅ ድምቀት ተከበረ፡፡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የደመራ በዓል ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ፣ የመስቀል በዓልን ታላቅነትና ታሪካዊነትን ካስረዱ በኋላ፣ ‹‹አበው መስቀሉን ያከብሩታል እንጅ አይዳፈሩትም፤ ይሰግዱለታል እንጅ አያቃልሉትም፣ አበው ኢትዮጵያውያን መተባበርን፣ አንድነትና ፍቅርን ነው ለትውልዱ ያስተላለፉት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን አብያተ ክርስቲያናትን እየተደፋፈሩ፣ እያቃጠሉ፣ እየዘረፉና እየገደሉ አንድነትንና ሰላምን፣ ፍቅርንና ልማትን ማምጣት ይቻላል ወይ? እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብና አጉል ድፍረት በሕዝበ ክርስቲያኑና በእግዚአብሔር ላይ እየተፈጸመ ያለ ክፉና አጥፊ ድርጊት መሆኑ ታውቆ በአስቸኳይ መቆም አለበት፣ እስከ መጨረሻውም መገታት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ባለው ነገር ሁሉ በጭራሽ መግባባት አይኖርም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አበው መስቀልን ይሳለሙታል እንጂ አያቃጥሉትም፣ የአክብሮት ስግደት ይሰግዱለታል እንጂ አይረግጡትም፣ ያከብሩታል እንጂ አያዋርዱትም፣ ምክንያቱም በመስቀሉና በቃሉ ክብራቸውንና ደኅንነታቸውን እንዳገኙ አሳምረው ያውቃሉና ብለዋል፡፡ ‹‹ምኞታችን ሊሳካ ያልቻለው ከመስቀሉ እየራቅን ስለሄድን ነው፤›› ያሉት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን መሪዎችና ልሂቃን ከሃምሳ ዓመታት ላላነሱ ዘመናት ከእግዚአብሔር ርቀዋል፡፡ ከመስቀሉ ሥርም አልተገኙም ጠፍተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት በኢትዮጵያ ውስጥ አያስኬድም፣ እንደማያስኬድ በግልጽ እያታየ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ተው ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፡፡ እንደ ቀደምት አባቶቻችን ከቤተ ክርስቲያን አፀድና ከመስቀል ሥር እንገኝ፡፡ የጎደለንን ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና እኩልነት፣ ፍትሕና ወንድማማችነት በመስቀሉ ውስጥ ተትረፍርፎ እናገኘዋለን፡፡ ይቅርታና መተባበር፣ መከባበርና መተማመን በመስቀሉ ውስጥ ሞልቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፈውስ ከመስቀሉ ሥር እንደሆነ ሁላችንም እንወቅ፡፡ እንደ አባቶቹ በመስቀሉና በቃሉ ለመክበር የሚፈልግ ትውልድ ወደ መስቀሉና ወደ ቃሉ ሊመለስ ግድ ይለዋል፡፡ ያለበለዚያ ግን ምኞቱ ሁሉ ቅዠት ከሚሆን በቀር ሊሳካ አይችልም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የአገሪቱ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃንና አክቲቪስቶች ከጥላቻና ከመወራረፍ፣ ከስድብና ከመጠላለፍ፣ ከፉከራና ከመዘላለፍ ተቆጥበን በቅንነት፣ በአርቆ አስተዋይነትና በፍቅር ይህንን ታላቅ ሕዝብ እንድናገለግል፣ አንድነታችንንና ሰላማችንን እንድንጠብቅ አባታዊ መልዕክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤›› በማለት ንግግራቸውን በመልካም የበዓል ምኞት አሳርገዋል፡፡ በምሥሉ ላይ ሁለቱ ፓትርያርኮች አቡነ መርቆርዮስና አቡነ ማቲያስ ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር ይታያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...