ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ክምችት ታቅፎ 16 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ብድር ማስፈቀዱ ተተቸ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር በጠራው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ የኢኮኖሚ ምሁራን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚከተላቸው የቁጥጥር አሠራሮችና የባለሙዎቹ አቅም የአገሪቱን ኢኮኖሚ አረጋግቶ ለመምራት አላስቻሉም በማለት ትችት አቅርበው፣ ባንኩ ዳግመኛ መዋቀር እንደሚያስፈልገው ጠይቀዋል፡፡
የኢኮኖሚክስ ማኅበሩ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀውና ‹‹የፋይናንስ ተቋማት ወቅታዊ ቁመናና ለውጥን የመቋቋም ብቃት›› በሚል ርዕስ በተካሄደው ውይይት፣ የመድረኩ አጋፋሪና ሰብሳቢ በመሆን የመሩት ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ከሁለት አሥርታት በላይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማት ወሳኝ ድርሻ መጫወታቸውን ባለሙያው አስገንዝበው፣ ይሁንና አገሪቱ በተገበረቻቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ላይ የዋለው ገንዘብና ያስገኘው ውጤት ብሎም በተቆጣጣሪ ባንኩ አቅም ውስንነት የተፈጠሩ ችግሮች ባንኩን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ባንኩ ካለው አቅም፣ ከሚተገብራቸው ፖሊሲዎችና ከሚመራባቸው አሠራሮች አኳያ ዳግም መዋቀር እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ሌላው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያውና በዘርፉ አንጋፋ ልምድና ሰፊ የአካዴሚ ተሞክሮ ያላቸው ገብረ ሕይወት አገባ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ቁመና፣ ከአገሪቱ የልማት ፍላጎት አኳያና ዘርፉ ምን ይጎድለዋል? ምንስ እያደረገ ነው? የሚሉ ነጥቦች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ዘላቂ፣ ሁሉን አሳታፊና ለሁሉ የሚጠቅም ልማት ይፈልጋሉ፤›› ያሉት ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፣ ‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሻለ ሕይወት ሊኖረው ይገባል፤›› በማለት ተቋማቱም ለዚህ ዓላማ መሠለፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የቁጠባ ገንዘብ በማሰባሰብ በተደራሽነትና በአካታችነት ላይ በመሥራት ኢኮኖሚው እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረግ የፋይናንስ ተቋማት ግዴታ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውጪ የግል ባንኮች የረዥም ጊዜ ብድር ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው፣ ይህም የአደጋ ሥጋትን በመሸሽ ሰበብ እንደሆነና በዚህ ሳቢያም ሰፊ ክፍተት እንደተፈጠረ የኢኮኖሚ ምሁሩ አብራርተዋል፡፡ የአገሪቱ ሰፊ ሀብት በአብዛኛው በንግድ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ እንደሆነ ያወሱት ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፣ አብዛኞቹ የሚሰጡት ብድርም የንብረት ዋስትና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ አዋጭ የፕሮጀክት ሐሳብ ያላቸው ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
በንብረት ዋስትና ላይ የተመሠረተው ብድር የንብረት ዋጋ መዋዠቅ ወይም መገሸብ ቢያጋጥመው ኖሮ አገሪቱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ትልቅ ቀውስ በፋይናንስ ተቋማቱ በኩል ሊከሰት ይችል እንደነበርም አውስተዋል፡፡ ‹‹የንብረት ዋጋ መውደቅ አላጋጠመም፡፡ ይህ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ የንብረት ዋጋ ቢወድቅ ኖሮ አደጋው የከፋ ይሆን ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የቤትና የሌላውም ንብረት ዋጋ በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ ከመሄድ በቀር ዋጋው ሲቀንስ እንደማይታይ ተሰታፊዎችም አጠናክረዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ባንኮች በንብረት ዋስትና ላይ ብቻ የተመረኮዘ የብድር አሰጣጥ በመከተላቸው ነው የሚል ክርክር ቀርቧል፡፡
እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች ያንሸራሸሩት ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፣ ብሔራዊ ባንክ የሕግ ማዕቀፉና የቁጥጥር አቅሙ ደካማ መሆን ቁልፍ ከሚባሉ የፋይናንስ ዘርፉ ችግሮች ዋናው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ የሚመራበት የቁጥጥር ሥርዓት በራሱም ሆነ በሚቆጣጠራቸው ተቋማት ላይ ወጪን የሚያስከትል እንጂ፣ አቅምን ማጎልበትና መደገፍ ላይ የተመረኮዘ አሠራር ስለማይከተል ዘርፉን ጫና ውስጥ እንደከተተው አብራርተዋል፡፡
የንስር ማይክሮ ፋይናንስ መሥራችና የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል አዲሱ በበኩላቸው፣ የፋይናንስ ተቋማት ማለትም ባንኮች፣ መድን ድርጅቶች፣ ማይክሮፋይናንስና ማሽነሪዎችን በሊዝ ብድር የሚያቀርቡ ተቋማት በጠቅላላው ያንቀሳቀሱት ሀብት 1.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶው የባንኮች ድርሻ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ እንደገና 60 በመቶ በላይ ድርሻውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደያዘው ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከ75 በመቶ ያላነሰው ሕዝብ የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻለ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ይህንን ለመለወጥ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ባንኮች ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ማበረታቻም ሆነ የውድድር ሜዳ ስለሌለባቸው ቴክኖሎጂ ተኮር የፋይናንስ አገልግሎት ቸል እንደተባለ ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ላሉት ለውጦች ብሔራዊ ባንክ ራሱን ማዘመን፣ የሰው ኃይሉም መሻሻል በተለይም ለሞባይል ባንኪንግና ለኢንተርኔት ባንኪንግ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልገው አብራርተዋል፡፡
ኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር በተሰኘው ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም የኢኮኖሚ ባለሙያ በመሆን የሚያገለግሉትና የኢኮኖሚክስ ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የሆኑት ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ ብሔራዊ ባንክ ካሉበት የማስፈጸም አቅም ውሱንነቶች በተጨማሪ የፖለቲካ ተፅዕኖ አለበት ሲሉ ተችተዋል፡፡ ይህንኑ ነጥብ ከቀረበላቸው ጥያቄ በመነሳት ያጠናከሩት ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩ የፖለቲካ ኃላፊዎች ጫና እንደሚታይበት፣ ብድር የተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማትና ሌሎችም እንዲከፍሉ ሲጠይቋቸው ‹‹ተዉ አትጫኗቸው፤›› እንደሚባሉ፣ ይህ ደግሞ የብድር አመላለስ ላይ ችግር በመፍጠር የተበላሸ ብድርን እንደሚያባብስ አብራርተዋል፡፡
እንደ ኢዮብ (ዶ/ር) ከሆነም የኢትዮጵያ የልማት ባንክ የተሸከመው የ40 በመቶ የተበላሸ የብድር መጠን በየትኛውም የፖሊሰ ባንክ መሥፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ምንም እንኳ ባንኩ የአስቀማጮችን ገንዘብ ባያበድርም፣ ለፕሮጀክቶች የሚያበድረው ገንዘብ የግብር ከፋዮች ሀብት በመሆኑ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ የባንኩ የተባለሸ ብድር እንዲህ በተባባሰበት ወቅት ተጨማሪ 16 ቢሊዮን ብር በዚህ ዓመት እንዲያበድር መፈቀዱ ተገቢ አይደለም በማለት ተቃውመዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የፋይናንስ ቀውስ ያልተከሰተው በአብዛኛው የመንግሥት ጥበቃ ስላለበት ነው፡፡ ዘርፉ ቆንጆ ቢመስልም ቆንጆ እያዩ ገደል የገቡ ብዙዎች ናቸውና ትኩረት ይሰጠው፤›› በማለት፣ በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በኮንትራት አስተዳደርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ገዥው ባንክም ሆነ ልማት ባንኩ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ያረቀቀው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ በፋይናንስ ዘርፉ ላይም ትኩረት እንዲሰጥ፣ በተለይም ብሔራዊ ባንክን መልሶ እንዲያዋቅርና እንዲሻሻል የሚያደርገውን አካሄድ እንዲከተል አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር በየወሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የውይይት መድረኮችን በቋሚነት ማዘጋጀት እንደጀመረ፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) አስታውሰው፣ በቀጣይም በግብርና ዘርፉ ላይ ያጠነጠነ ስብሰባ እንደሚጠራ አስታውቀዋል፡፡