Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበተፈጥሮ ልዩ ተሰጥኦ የታደሉ ተማሪዎች ተለይተው የሚማሩበት ልዩ የአዳሪ ትምህርት ማዕከል ሊቋቋም...

በተፈጥሮ ልዩ ተሰጥኦ የታደሉ ተማሪዎች ተለይተው የሚማሩበት ልዩ የአዳሪ ትምህርት ማዕከል ሊቋቋም ነው

ቀን:

ተማሪዎቹ ከመላ አገሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጥንቃቄ ይመለመላሉ ተብሏል

የማዕከሉ ግንባታ በቡራዩ ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ተጀምሯል

በተፈጥሮ ልዩ ተሰጥኦ የታደሉ ሕፃናት ከልጅነታው ጀምሮ ልዩ ክትትል ተደርጎባቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ሲደርሱ ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ቡራዩ ከተማ በሚቋቋመው፣ “የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ማዕከል” የሚል ስያሜ በተሰጠው ልዩ ተቋም በመግባት የሚመጥናቸውን ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ ሊደረግ ነው፡፡

- Advertisement -

 አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ “የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ማዕከል” የሚል መጠሪያ የሚሰጠውን የትምህርት ማዕከል ለማቋቋም የሚያስፈልግ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው፡፡

 “የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ማዕከል” በሚለው ስያሜ ውስጥ ተሰጥኦ የእንግሊዘኛውን አቻ ቃል “Gift” የሚያመላክት ሲሆን፣ ተውህቦ ደግሞ የእንግሊዝኛውን አቻ ቃል “Talent” ትርጓሜ ይይዛል፡፡

‹‹ተሰጥኦ›› የሚለው ቃል የሰው ልጅ በተፈጥሮ የታደለውን የላቀና ልዩ ችሎታውን የሚገልጽ እንደሆነ ያስረዱት ኃላፊው፣ “ተውህቦ” ማለት ደግሞ በአንድ የትምህርት ዓይነት ወይም ተግባር ለአብነት ያህል በሒሳብ ትምህርት ወይም በሙዚቃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ፣ ይህንንም የላቀ ችሎታ በትምህርት ማምጣትና ማሳደግ የሚችሉ ግለሰቦችን የሚመለከት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሠለጠኑ የሚባሉት አገሮች እዚህ ደረጃ የደረሱት ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ዜጎቻውን በባትሪ ፈልገው የማደንና የመጠቀም ስትራቴጂ ስለተከተሉ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸው፣ “ኢትዮጵያም እንዲህ ዓይነት ፀጋ የታደሉ ሕፃናት ይወለዱባታል፡፡ ልዩነቱ ኢትዮጵያ እነዚህ ስጦታዎቿን ስትገላቸው እንጂ ስትፈልግና ስታድናቸው አልነበረም፤” ብለዋል፡፡

በደርግ ዘመን ወሎ አካባቢ የተገኘ መሐመድ ኢድሪስ የተባለ ታዳጊ የሒሳብ ሊቅን ኢትዮጵያ ሳትጠቀምበት እንዴት እንደተቀጨ ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡ ታዳጊ ወጣቱ ተፈጥሮ በቸረችው ልዩ ችሎታ በወቅቱ ከሒሳብ ማስያ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በመፍጠን የሒሳብ ስሌት ይሠራ የነበረ ከመሆኑም በላይ፣ ሒሳባዊ ስሌቶችን ለማከናወን ይከተላቸው የነበሩት ዘዴዎች ልዩና አስደናቂ እንደነበሩና በወቅቱም በዩኒቨርሲቲ መምህራን ጭምር ብቃቱ የተመሰከረለት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ይሁንና በወቅቱ የነበረው መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን ችሎታ በወጉ በማስተናገድ ወደ ውጤት የሚመራበት አቅጣጫ ስላልነበረው፣ ወጣቱ በዝዋይ የሕፃናት አምባ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር መደበኛ ትምህርት እንዲከታተል በመደረጉ ችሎታው ለፍሬ ሳይበቃ በወጣትነት ዕድሜው ሊቀጭ መቻሉን በፀፀት ያስታውሳሉ፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የመንግሥት ትኩረት የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ እንጂ፣ እንዲህ ያሉ ሕፃናትን ፈልጎ የማዳንና በተፈጥሮ ያገኙትን ፀጋ ለአገር ጥቅም እንዲያውሉ ታስቦበት እንኳ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎች የተለየ ክህሎታቸውን አለመመንዘራቸው ብቻ ሳይሆን፣ በኅብረተሰቡም መገለል ደርሶባቸው ሲባክኑ እንደሚታዩ ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት የተመጣበትን የስህትት መንገድ ማረም፣ እንዲህ ዓይነት ፀጋን የታደሉ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ከመላ አገሪቱ በማደን ክህሎታቸውን እንዲያበለፅጉ ለማድረግ ታስቦ ማዕከሉን የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ማዕከል ገብተው እንዲማሩ የሚደረጉ ተማሪዎች በዋነኛነት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ፣ ማዕከሉ ከልጅነታቸው አንስቶ አስፈላጊውን ክትትል ሲያደርግባቸው የቆዩ ልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ያላቸው ተማሪዎች እንደሚሆኑ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

 እነዚህ ተማሪዎች በማዕከሉ በሚኖራው ቆይታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመደበኛው ካሪኩለም ልዩ በሆነ መንገድ እንዲከታተሉና በመደበኛነት የሚሰጠውን ትምህርት በአጭር ጊዜ የሚያጠናቅቁበት ፈጣን የትምህርት ፕሮግራም እንደሚመቻች፣ ከዚህም ባለፈም ልዩ ዝንባሌና ተሰጥኦውን ባገናዘበ ከባቢ ትምህርት እንዲሰጣቸውና አቅማቸው እስከፈቀደም ድረስ የመደበኛ ትምህርት መከታተያና መዘዋወሪያ ጊዜን ሳይጠብቁ ወደሚፈለገው ከፍታ ወይም ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲሸጋገሩ እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በማዕከሉ ከሚሰጣቸው የመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ፣ በሜካኒካልና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ በኤሌክትሮኒክስና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን፣ በባዮ ኬሚካል፣ በቀመርና አስትሮፊዚክስ፣ እንዲሁም በሳይበር ቴክኖሎጂ የሙያ ዘርፎችና በሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በተግባር የታገዘ ተጨማሪ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ማዕከል ግንባታም፣ በቡራዩ ከተማ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በ2010 ዓ.ም. የተጀመረ መሆኑ ታውቋል፡፡

የማዕከሉ የማስተማሪያ ቋንቋ እንግሊዝኛ እንደሚሆን፣ የዚህ ምክንያትም እንግሊዝኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማስተማሪያ ቋንቋ ከመሆኑ በተጨማሪም አብዛኞቹ የማስተማሪያና አጋዥ መጻሕፍት በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡

ማዕከሉን የሚያቋቁም ደንብ ዝግጅት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ረቂቅ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ የማዕከሉ ተጠሪነትም ለዚሁ ሚኒስቴር ሆኖ ዓላማውን ለማስካት የሚያስችል ከምሁራን የሚውጣጣ ቦርድ በበላይነት እንደሚያስተዳድረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ