ከዚህ ቀደም በራሳቸው ካሳተሙትና ከመላው ዓለም ጋር ካስተዋወቃቸው ‹‹ሜድ ኢን አፍሪካ›› መጽሐፍ ጀምሮ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የአካዴሚ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ሚኒስትር አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፣ ከታዋቂ የእስያ ምሁራን ጋር በመሆን በጽሑፍም በአርትኦትም የተሳተፉባቸውን ተጨማሪ ሁለት መጻሕፍት ለንባብ አቀረቡ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአካዴሚ ጉዳዮች ላይ እያተኮሩ የሚገኙት አርከበ (ዶ/ር) ከከፍተኛ አማካሪነታቸው ባሻገር፣ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም ተመራማሪ አባል ናቸው፡፡ ከዚህ ተቋም ጋር በመሆን እስካሁን ከተሳተፉባቸው መካከል በቅርቡ የታተሙት፣ ‹‹ሀው ኔሽንስ ለርን›› ‹‹ቻይና-አፍሪካ ኤንድ አን ኢኮኖሚክ ትራንስፎሜሽን›› የተሰኙት መጻሕፍት ለንባብ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አርከበ (ዶ/ር) በእነዚህ መጻሕፍት የአርትኦት ድርሻቸውን ከጃፓኑ የኢኮኖሚ ኬኒቺ ኦህኖ (ፕሮፌሰር) እንዲሁም ከቻይናዊው ጀስቲን ዩፉ ሊን (ፕሮፌሰር) ጋር በመሆን ተወጥተዋል፡፡
መጻሕፍቱ በአብዛኛው በኢንዱስትሪያዊ ለውጦች፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ ከአርከበ (ዶ/ር) ጋር የተሳተፉት ምሁራንም በኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ መስክ መንግሥትን ሲያማክሩ የቆዩ ናቸው፡፡ ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፣ በጃፓን መንግሥት ድጋፍ በኢትዮጵያ በስድስት ወራቱ ሲካሄድ ዓመታት ባስቆጠረው ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ልማት ምክክር መድረክ ላይ በመሳተፍና ምክር በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በማማከር ሲሳተፉ እንደቆዩም አይዘነጋም፡፡
መንግሥት የመጀመርያውንና ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲያዘጋጅ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ መስክ፣ እንዲሁም ከካይዘን ሥርዓት ጋር የተገናኙ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብም ይታወቃሉ፡፡ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታም እነዚህን ጨምሮ በመንግሥት በኩል የሚታዩ ድክመቶችንም በማመላከት ይታወሳሉ፡፡
ጀስቲን ሊን (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ ቻይናውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ፣ ስኬታማነቱ ባይታይም የቻይና አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ እንዲፈልሱ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች እንደነበሩ በማሳሰብ በተደጋጋሚ ሲናገሩና ሲመክሩ የቆዩ ናቸው፡፡ በቻይና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የማምረቻ ወጪ መጨመር፣ በተለይም በፋብሪካ ሠራተኞች ደመወዝ መጨመር ምክንያት በርካታ ማምረቻዎች እየተዘጉ ወደ ሌሎች አገሮች ማማተር የጀመሩበትን አጋጣሚ ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ከወራት በፊትም ‹‹ዘ ኦክስፎድ ሀንድቡክ ኦፍ ዘ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ›› የተሰኘው መጽሐፍ ሲወጣም፣ አርከበ (ዶ/ር) በአርትኦትና የተወሰኑትን ምዕራፎች በመጻፍ መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን በተከታታይ ውይይት ከተደረገባቸው ከእነዚህ ሦስት መጻሕፍት ባሻገር፣ ሰኞ መስከረም 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ በሚቀርቡ ገለጻዎች ላይ ከእሳቸው ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ሽልማት የተቀዳጁ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ምሁራን እንደሚሳተፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡