Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየተዘነጋው የባህል መድኃኒትና ሕክምና

የተዘነጋው የባህል መድኃኒትና ሕክምና

ቀን:

የባህል መድኃኒትና ሕክምና ባለቤት አልባ፣ የተናቀ፣ የተገለለና ጥርት ያለ መረጃ የሌለው ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአጠቃላይ ‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› ሆኖ ከርሟል ለማለት ይቻላል፡፡ የለም እንዳይባል እንቅስቃሴውን የሚያስተባብር አካል ከተቋቋመ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ አለ እንዳይባል ደግሞ በውስጡ ያሉት ተመራማሪዎች ባላቸው ሥልጣንና ኃላፊነት የሚሠሩና የሚንቀሳቀሱ ብሎም የባህል መድኃኒትና ሕክምናውን በቅጡ ያስተዋወቁና ያስፋፉ አይደሉም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባህል መድኃኒት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ፣ የባህል መድኃኒትና ሕክምናን ዘርፍ ለማበልጸግ የሚረዱ አሠራሮችን ለማመቻቸትና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል እንቅስቅሴ ተጀምሯል፡፡ ጤና ሚኒስቴርም ሆነ ሎሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በገቡት ቃል መሠረትም በባህል መድኃኒትና ሕክምና ዙሪያ ቀደም ሲል የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችንም ለማስፈጸም የ90,000,000 ብር በጀት ተይዟል፡፡

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር መምሪያ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተካ እንደሚሉት፣ የበጀት ድጋፉ የተገኘው ለ2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሥራ ላይ የሚቆየውም ለአንድ ዓመት ነው፡፡ በጀቱንም የያዘው ጤና ሚኒስቴር ነው፡፡ በዚህም ከሚከናወኑት ተያያዥ ጉዳዮች መካከል የባህል መድኃኒትና ሕክምና አዋቂዎች ማኅበርን ማጠናከር፣ ለዘርፉ አዋቂዎችና ማኅበረሰቦች ሥልጠና መስጠትና ዘርፉ ከመደበኛው የጤና ሥርዓት ጋር ተቀናጅቶ አገልግሎ ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ የባህል መድኃኒትና ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ ከእምነትና ሃይማኖት ጋር ይያያዛል፡፡  በማዳን የሚታወቅም ነው፡፡ ሕክምናው ትኩረት የሚያደርገውም የሕመም (በሽታ) ምልክት ባለበት የሰውነት አካል ላይ ነው፡፡

ወ/ሮ ፍሬሕይወት አንድ የቆየ ጥናትን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 80 ከመቶ ያህሉ፣ ከእንስሳት ደግሞ 90 ከመቶ የሚደርሱት የሚታከሙት በባህላዊ መድኃኒት ነው፡፡ ሕዝቡ የባህል መድኃኒትና ሕክምና የሚጠቀመው በሦስት ምክንያቶች ማለትም በተደራሽነቱ፣ በአነስተኛ ገንዘብ በመገኘቱና ባህላዊ በመሆኑ ባለው ተቀባይነት ነው፡፡

ባህላዊ መድኃኒትና ሕክምናን አስመልክቶ ያለውም ዕውቀት በአብዛኛው በአፍ የሚተላለፍ ሲሆን፣ የተወሰነ ደግሞ በሰነድ ተይዞ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ከ400 ዓመት በፊት የተዘጋጀና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግዕዝ የተጻፉት ‹‹መጽሐፍተ ፈውስ›› እና ‹‹መጽሐፍ መድኃኒት››ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች አገር እንደ መሆኗ መጠን እዚህም እዛም ወይም በተበጣጠሰ መልኩ የተጻፉ መድኃኒቶች ሊኖሯት እንደሚችሉ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

የባህል መድኃኒቶች ምንጮቻቸው የእንስሳት ተዋጽኦ፣ ማዕድናትና በአብዛኛው ደግሞ ዕፀዋት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛው ታዳጊ አገሮች ባህላዊ መድኃኒት ሕክምናን እንደ መጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ አብዛኛው እናቶችም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምናን ቤት ውስጥ በባህላዊ መድኃኒት እንደሚያከናውኑት፣ በዚህም ውጤት እንደተገኘበት ወ/ሮ ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡

ለባህላዊ መድኃኒት ሕክምና መጠናከር በርካታ መልካም አጋጣሚዎች አሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋትና በተለይ በቅርቡ ከተቋቋሙት መካከል አብዛኞቹ ለባህላዊ መድኃኒት ሰፋ ያለ ትኩረት መስጠታቸው፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕላን ውስጥ ባህላዊ መድኃኒት ብዙ ቦታ መጠቀሱ፣ በአገሪቱ የተለያየ ባህል፣ ብዝኃ ሕይወትና ለባህል መድኃኒት የሚውሉ ብዙ ዕፀዋት መኖራቸው እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ መታከሉ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚስችሉ መደላድሎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደቂቅ አካላት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገነነ ተፈራ (ዶ/ር) በባህል መድኃኒት እንደ አህጉር አፍሪካ፣ እንደ አገር ደግሞ ኢትዮጵያ በእጅጉ የታወቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በኢትዮጵያ መደበኛው ሕክምና ሥራ ላይ የዋለው በ1860ዎቹ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የባህል መድኃኒት የሚያውቁ ብቻ ሳይሆኑ የማያውቁትም አዋቂ ነን እያሉ በርካቶችን ለተወሳሰበ ችግር ሲያጋልጡ ይስተዋላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባህላዊው ከመደበኛው እንዴት ተጣጥሞ መሄድ እንዳለበት በግልጽ የተቀመጠና በአግባቡ እየተሠራበት አይደለም፡፡

ዶ/ር ገነነ እንደሚሉት፣ የባህል መድኃኒትን ከመደበኛው መድኃኒት ጋር አጣምሮ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል መዋቅር ጤና ሚኒስቴር ሊያዘጋጅና በዚህ መዋቅር ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎች የሕግ ጥላና ሽፋን ሊሰጣቸው፣ በዘርፉ በቂ ዕውቀት የሌላቸውም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የጄነቲክ ሀብት አርብቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አየነው፣ የማኅበረሰቡ ዕውቀት ከጥቅሙ ባሻገር ሀብት መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ዓይነቱ ሀብት እንዳይሰረቅ ተገቢው ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የባህል መድኃኒትቶችን መመዝገብ ሕግ ማውጣትና አሠራር መዘርጋት፣ የመረጃ ቋት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት በስተቀር በብሔራዊ ደረጃ ባለመኖሩ፣ ይህንነ ማዘጋጀት መድኃኒቶቹን ጠብቆ ለማቆየት እንደሚያስችልም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ቤት አርአያ ሐይመተ (ዶ/ር) በባህል መድኃኒት ዙሪያ ብዙ ባለድርሻ አካላት እንዳሉ፣ ውይይትም እንሚካሄድ ነገር ግን አካላቱን የሚያሰባስብ ተቋም እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የመሠረታዊ መድኃኒቶች ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ መንግሥተአብ ወልደ አረጋይ በበኩላቸው፣ የባህል መድኃኒትና ሕክምናን ሥራ ላይ የሚያውሉ አገሮች ግልጽ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሕግ ማዕቀፍ ሊኖራቸው እንደሚገባና ዓለም አቀፉ ድርጅትም ዘርፉን ከማሳደግ አንፃር በርካታ ዕገዛ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) ዘመናዊና ባህላዊ መድኃኒት የሚባል አገላለጽ ተገቢ እንዳልሆነ፣ የባህል መድኃኒት ከጥንት ጀምሮ እያደገ፣ እየጎለበተና እየተሻሻለ የመጣ ስለሆነ ዘመናዊነት ንዳለው ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ይዞት የመጣው ባህላዊ መድኃኒት መደበኛው መድኃኒት ያልደረሰባቸውን በሽታዎች ሁሉ እየፈወሰ መሆኑ መታወቅ እንዳለበትም አክለዋል፡፡

የባህል መድኃኒት በኢትዮጵያ በአዋጅ የተካተተው በ1942 ዓ.ም. ነው፡፡ በ1950 ዓ.ም. ምዝገባና ፈቃድ ሲሰጠው፣ መመርያ የወጣለት ከ1957 ዓ.ም. እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ነው፡፡ በ1979 ዓ.ም. ባህላዊ መድኃኒትን የሚያስተባብር ቢሮ በጤና ሚኒስቴር ውስጥ ተቋቋመ፡፡ ቢሮው በ2005 ዓ.ም. ባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር መምሪያ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ሥር ተመድቦ እንዲንቀሳቀስ ተደረገ፡፡

መምሪያው በአዋጅ ከተሰጡት በርካታ ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል በባህላዊ መድኃኒት ዙሪያ የሚካሄደውን ምርምር መቆጣጠርና መከታተል፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ የባህል መድኃኒቶችን ወደ ምርት ማቅረብ፣ ባህላዊው መድኃኒቶች ከዘመናዊ መድኃኒቶችና ከመደበኛው የጤና ሥርዓት ጋር የሚቀናጁበትን ምክረ ሐሳብ ማቅረብና የፖስት ግራጂዌት ተማሪዎች በባህላዊ መድኃኒት ዙሪያ ለሚያካሂዱት ምርምር ተገቢውን ድጋፍ መስጠት ይገኙበታል፡፡

በባህል መድኃኒት ዙሪያ ላይ ትኩረት የሚያደርግና በኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የሚመራ ‹‹ብሔራዊ አማካሪ መድረክ›› ከሦስት ዓመት በፊትም የመድረኩም ዓላማና የትኩረት አቅጣጫ በኢትዮጵያ ውስጥ በባህላዊ መድኃኒት ላይ ትኩረት ያደረገ ብሔራዊ ምክር ቤት የሚቋቋምበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ባህላዊ መድኃኒት ከመደበኛው መድኃኒትና ከአገሪቱ የጤና ሥርዓት ጋር የሚቀናጅበትን ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...