ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ያስቆጠው ንስር ማይክሮ ፋይናንስ፣ በአሁኑ ወቅት ከሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች አንዱ የሆነውንና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጠውን የላፕቶፕ ኮምፒውተር መግዣ ብድር በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
በእስካሁኑ ቆይታው አምስት ሺሕ ደንበኞችን ያፈራውና ከግማሽ ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለማበደር የበቃው ይህ አነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅት፣ በ215 ባለአክሲዮኖችን በመያዝ፣ በአምስት ሠራተኞች ሥራ ሲጀምር በአንዲት አነስተኛ ጽሕፈት ቤት ደምበል ሲቲ ሴንተር ሕንፃ ላይ በተከራየው ቤት ውስጥ እንደነበር የተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት ዋቅጋሪ ያስታውሳሉ፡፡ ተቋሙ የተመሠረተበትን አምስተኛ ዓመት፣ ቅዳሜ መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ቁጥራቸው 70 ከደረሰው ሠራተኞቹ ጋር በቢሾፍቱ ዘክሯል፡፡
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ፈታኝ ችግሮችን እንዳለፈ ያስታወሱት፣ የንስር ማይክሮ ፋይናንስ መሥራችና የቦርድ አባል አቶ ሚካኤል አዲሱ ከፈተናዎቹ ሁሉ ወጣትነትን አምኖ መቀበል ትልቁ ችግር እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ንስር ማይክሮ ፋይናንስን ለመመሥረት ከሰባት ዓመታት በላይ ዝግጅት ሲያደርግበትና ሲብላላ የቆየ ፕሮጀክት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሚካኤል፣ የፕሮጀክቱን ሐሳብ አቅሙ ላላቸው አካላት በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ካፒታል ለማሰባሰብ ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ላይ የመሥራቾቹ ወጣት መሆን ትልቅ እንቅፋት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሰዎች ሐሳባችንን ሳይሆን፣ ወጣትነታችንን ማመን ይከብዳቸው ነበር፤›› ያሉት አቶ ሚካኤል፣ በአሁኑ ወቅት ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር መስጠት የቻለ ተቋም በመመሥረት በተለይም ባንኮችና አነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች ትኩረት በማይሰጧቸው የሥራ ዘርፎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በማድረግ አጠቃላይ ሀብቱን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለ ተቋም ለማስተዳደር እንደተቻለ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ቢንያም ታደሰ የንስር ማይክሮ ፋይናንስ መሥራችና የቦርድ ጸሐፊ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ቢንያም ገለጻ፣ የንስር ዋነኛ ትኩረቱ ‹‹ሚሲንግ ሚድል›› እየተባሉ ለሚጠቀሱት፣ ከባንክ ለመበደር የሚጠየቁትን የብድር ዋስትና ማሟላት ለማይችሉ፣ ከአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢዎች የሚቀርበው ብድር አነስተኛ መሆኑ ለንግድ ሥራቸው ባለመመቸቱ የሚቸገሩትን ለማገዝ ነው፡፡ እንዲህ ባለው የብድር አገልግሎትም ከ1,800 ያላነሱ ደንበኞች ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አዳዲስ የብድር መስጫ መስኮችን በመፍጠር በተለይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች እገዛ የሚሰጥ፣ የላፕቶፕ ኮምፒውተር መግዣ ብድር ማቅረብ መጀመሩም ወጣቶች ላይ መሥራት ከመፈለጉ እንደሆነ አቶ ሚካኤል አስታውቀዋል፡፡ ይህን ብድር ለማግኘት ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድና ለብድር ዋስትና ደመወዝተኛ ወይም ሌላ የገቢ ምንጭ ያለውና በየጊዜው ብድሩን የሚከፍልላቸው ቤተሰብ ወይም ዘመድ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት አዲስ የብድር ዓይነት እንደሆነ ሲገለጽ፣ በመኪና ሊብሬ፣ እንዲሁም በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባፀደቀው መሠረት በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ዋስትና ብድር ለማቅረብ ንስር እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንዲሁም ለእናቶች በተለይም በጉልት ችርቻሮና በመሳሰሉት መስኮች ለሚተዳደሩም እንደ አቅማቸው ብድር በማቅረብ እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የአምስት ዓመታት ጉዞውን በዘከረበት ዕለትም ለኒያ ኦቲዝም ፋውንዴሽን የ200 ሺሕ ብር ዕርዳታ ከማቅረብ ባሻገር ልጆቻቸው በኦቲዝም የተጎዱ እናቶች፣ በቤት ውስጥ ለሚሠሯቸው ልዩ ልዩ የእጅ ሥራና የባልትና ውጤቶች ወይም ሌሎችም የምርት ዓይነቶችን ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን የብድር ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኑን አቶ ዳዊት ይፋ አድርገዋል፡፡ ሠራተኞቹም ደም በመገለስ ቀይ መስቀልን አግዘዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት ከ38 ያላነሱ አነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች ወይም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በብሔራዊ ባንክ ዕውቅና አግኝተው በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡