Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜቴክ ቀሪ ገንዘባቸውን እንዲከፍላቸው ወይም ሕንፃውን እንዲመልስላቸው የቀድሞ ኢምፔሪያል ሆቴል ባለቤቶች ጠየቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጉዳዩን በተመለከተ ከሜቴክ አመራሮች ጋር ድርድር ጀምረዋል

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞውን ኢምፔሪያል ሆቴል ሕንፃ በመጀመርያ የገዛውን ድርጅት በመወከል፣ ቀሪ ገንዘባቸውን እንዲከፍል ወይም ንብረታቸውን እንዲመልስ የሕንፃው ባለቤቶች ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል ሕንፃ ወራሽ ባለቤቶች ሕንፃውን በመጀመርያ ለመግዛት ውል የፈጸመው የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ድርጅት አክሰስ ካፒታል በሽያጭ ውሉ መሠረት የሕንፃውን ሙሉ ዋጋ ሳይከፍል ሦስተኛ ወገን ለሆነው ሜቴክ እንደሸጠው በመጥቀስ፣ በዋናነት ሜቴክ ቀሪ ገንዘቡን ከእነ ወለዱ እንዲከፍላቸው የጠየቁ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሜቴክ ይኼንን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ፣ ንብረታቸው የሆነውን ሕንፃ እንዲመልስላቸው ለተቋሙ አመራሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በጠበቆቻቸው አማካይነት ከሜቴክ አመራሮች ጋር እየተደራደሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ከቦሌ ወደ መገናኛ በሚወስደው የቀለበት መንገድ አጋማሽ ላይ ከሚገኘው ወደ ገርጂ መገንጠያ አደባባይ አጠገብ ከ20 ዓመታት በፊት የተገነባው ሕንፃ፣ ለረጅም ዓመታት ኢምፔሪያል ሆቴል በሚል መጠሪያ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የሆቴሉ ባለቤቶች ሕንፃውን የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ፣ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ድርጅት ለነበረው አክሰስ ካፒታል ለመሸጥ ውል መፈጸማውን ባለቤቶቹ ይገልጻሉ፡፡ ሁለቱ ወገኖች በወቅቱ በፈጸሙት የሕንፃ ሽያጭ ውል አክሰስ ካፒታል የተባለው ድርጅት 47 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ለመክፈል፣ እንዲሁም ባለቤቶቹ ሕንፃውን በማስያዝ አግኝተውት ለነበረው የባንክ ብድር ቀሪ ዕዳና በሕንፃው ሽያጭ ምክንያት በሕግ የሚጠበቅባቸውን የካፒታል ገቢ ግብር ክፍያን አክሰስ ካፒታል አጠቃሎ ለመክፈል መዋዋላቸውን ባለቤቶቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለቤቶቹ አክሰስ ካፒታል በጥሬ ገንዘብ ለመክፈል ከተስማማው 47 ሚሊዮን ብር ውስጥ፣ እስካሁን የተከፈላቸው ከግማሽ በታች (20 ሚሊዮን ብር) ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አክሰስ ካፒታል የተጠቀሰውን መጠን ያህል ክፍያ ብቻ ፈጽሞ ሕንፃውን የተረከበ ቢሆንም፣ የሕንፃው ሕጋዊ ባለቤትነት ስም አልተዘዋወረለትም፡፡ ይሁን እንጂ አክሰስ ካፒታል ሕንፃውን በዚህ ሁኔታ በተረከበ በዓመት ጊዜ ውስጥ፣ ሕንፃውን በአሁኑ ወቅት እየተጠቀመበት ለሚገኘው ሜቴክ በ71 ሚሊዮን ብር ሸጦታል፡፡ ሜቴክ ክፍያውን ፈጽሞ ሕንፃውን ከተረከበ ስምንት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ የሕንፃው ሕጋዊ ባለቤትነት ግን አሁንም በሕንፃው የመጀመርያ ባለቤቶች እጅ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሜቴክ የቀድሞ አመራሮችና በአሁኑ ወቅት የከሰመው የአክሰስ ካፒታል መሥራችና ባለቤት፣ በቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል ሕንፃ ግዥ ስምምነት በሙስና ተጠርጥረው እስር ቤት ሆነው የዳኝነት ሒደቱን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

ሜቴክ በአሁኑ ወቅት እየተጠቀመበት ከሚገኘው ሕንፃ የመጀመርያ ሽያጭ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ያልተከፈላቸው የሕንፃውን ሕጋዊ የባለቤትነት አሁንም ድረስ የያዙት የቀድሞ ባለቤቶች በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚሁ ሕንፃ የመጀመርያ ሽያጭ የካፒታል ገቢ ግብር ያልተከፈለው የገቢዎች ሚኒስቴር በሌላ በኩል በመሆን ሜቴክ ገንዘባቸውን እንዲከፍል እየጠየቁ ነው፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ከመጀመርያው የሕንፃው ሽያጭ ሊከፈለው ይገባ የነበረው የካፒታል ገቢ ግብር 12 ሚሊዮን ብር ብቻ ቢሆንም፣ ይህ ግብር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሊከፈለው ባለመቻሉ በግብር ሕጉ መሠረት የሚጣለውን ወለድ በማከል ከፍሬ ግብሩ በተጨማሪ በርካታ ሚሊዮን ብር ጠይቋል፡፡ የሕንፃው የቀድሞ ባለቤቶች በበኩላቸው ከ27 ሚሊዮን ብር በሆነው ያልተከፈላቸው ቀሪ ገንዘብ ላይ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ሊያገኙ ይችሉ የነበረው ጥቅም፣ በባንክ የወለድ ምጣኔ ተሠልቶ እንዲከፈላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በሁለቱ ወገኖች የቀረበው የክፍያ ጥያቄ ድምር እስከ 140 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን፣ በደረሰበት የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በቋፍ ላይ የሚገኘው ሜቴክ ይህንን ክፍያ ለመፈጸም የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ቢጠይቅም መፍትሔ እንዳላገኘ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የሕንፃውን የባለቤትነት ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ እንዲፈታም የቦርድ አመራሩ ውሳኔ አሳልፎበታል፡፡ በዚህ የተነሳም ከሕንፃው ባለቤቶች ጋር ችግሩን ለመፍታት ድርድር ውስጥ የገባ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው የሜቴክ ሰነድ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል የካፒታል ገቢ ግብር ያልተከፈለው የገቢዎች ሚኒስቴር ያልተከፈለውን ግብር ለማስከፈል በሕግ የተሰጡትን መብቶች ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ሰሞኑን ለሜቴክ በጻፈው ደብዳቤ በማሳወቅ፣ ሕንፃውን ለቆ እንዲወጣ የሁለት ወራት የጊዜ ገደብ ሰጥቶታል፡፡ ይኼንን ጉዳይ ከሚዲያ እንደሰሙ የሚናገሩት የቀድሞ ኢምፔሪያል ሆቴል ባለቤቶች፣ የካፒታል ገቢ ግብር ሊከፈል የሚችለው በውሉ መሠረት ሙሉ ክፍያ ሲፈጸም ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ ነገር ግን ይህንን ጉዳይም ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር እንደሚወያዩበት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች