Friday, May 24, 2024

ግብፅ ከሰሞኑ ማራመድ የጀመረችው አቋም አንድምታ ምንድነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጀመር በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት ቀስ በቀስ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በኋላም ኢትዮጵያን፣ ግብፅንና ሱዳንን ወደ አካተተ ትብብር አዘንብሎ ነበር፡፡ አገሮቹ ማስጠበቅ የሚሹት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ ምክንያታዊ ሙግ ውስጥ በመግባቱ ተፈጥሮ የነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት መስከን እንደቻለ፣ በተለይ አገሮቹ ላለፉት አራት ዓመታት የመጡበትን መንገድ የተከታተለ ሊገነዘበው የሚችለው ነባራዊ እውነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን መሠረት ያደረገና 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የሚያጠራቅም ግዙፍ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ ልትገነባ ቀርቶ ያለ ግብፅ ዕውቅናና ፈቃድ የዓባይን ውኃ ሊጠቀም የሚችል ምንም ዓይነት የልማት ሥራ ልታከናውን አትችልም የሚል እምነትና ፖለቲካዊ አቋም ስታራምድ የከረመችው ግብፅ፣ የህዳሴ ግድቡ ከተጀመረ በኋላ ይህንኑ አቋሟን በማራመድ ብትቀጥልም እ.ኤ.አ. በ2015 የሦስቱ አገሮች መሪዎች የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በፈረሙት የትብብር መርህ ስምምነት (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ)፣ ግብፅ የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት በይፋ ተቀብላለች፡፡

በዚህ የትብብር መርህ ስምምነት ምክንያትም ኢትዮጵያ መገንባት የጀመረችው የህዳሴ ግድብ ሊያስከትላቸው ይችላሉ የሚባሉ ሥጋቶችን ሦስቱም አገሮች አንዱ የሌላውን ጥቅምና ፍላጎት በማጤን፣ አንዱ በሌላው ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት ሳያደርስ፣ የአገሮች ሉዓላዊነትን በማይጋፋ፣ ትብብርን በተላበሰ የውይይት መንፈስ ልዩነቶቻቸውን በጋራ ለመፍታት ወደሚያስችል መግባባት መምጣታቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን ስምምነት መሠረት በማድረግም ከሦስቱም አገሮች በተወከሉ ባለሙያዎች መማክርት በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን ሥጋትና ግድቡ በጥቅሞቻቸው ሊፈጥር ይችላል ያሉትን ጉዳት ለማስወገድ ለዓመታት የሄዱበት መንገድ ስክነት የተሞላበት ቢሆንም፣ የግድቡ ግንባታ መቀጠልና ጥቅሞቻቸውና ሥጋቶቻቸው በጀመሩት ውይይት ፈጣን እልባት ማግኘት አለመቻሉ፣ በተለይም በግብፅ ዘንድ ጭንቀትን አንዳንዴም ተስፋ መቁረጥን ሲፈጥር እንደነበር ቢታወቅም ከጀመረችው የትብብር መንገድ እንድታፈነግጥ አላደረጋትም ነበር፡፡

በ2010 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ በኢትዮጵያ በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ አመራሮች በውስጥ ጉዳያቸው በመጠመዳቸው ምክንያት፣ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የተጀመረው ድርድር ሲጓተት የግብፅ መንግሥት ይሁንታ እንደነበረበት፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ቅድሚያ ትኩረት ካደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የህዳሴ ግድብን የተመለከተ መሆኑን የሚገልጹት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው ኃላፊዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ በሁለተኛው ሳምንት የግድቡን ግንባታ በአካል እነደጎበኙ ያስረዳሉ፡፡

ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ወደ ግብፅ በመጓዝ ከግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ጋር፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብፅ የነበራቸው ቆይታ በወቅቱ በግብፅ ሚዲያዎች ተላልፎ የነበረ ሲሆን፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ የግብፅን የውኃ ድርሻ እንደማትጎዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ቃል እንዲገቡ ሲጠይቋቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዓረብኛ ቋንቋ እንዲናገሩ በተጠየቁት መሠረት ኢትዮጵያ የግብፅን የውኃ ድርሻ ሳትጎዳ፣ የዓባይ ውኃን ለልማት እንደምታውል መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህ በኃላ በነበረው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም የሦስቱ አገሮች የባለሙያዎች ቡድን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ለመወያየት ተገናኝቶ አለማወቁ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥም ከግብፅም ሆነ ከሱዳን በኩል ጫና ለመፍጠር አለመሞከሩ በመሪዎቹ መካከል ስምምነት ስለመኖሩ እንደሚያመለክት፣ ሪፖርተር ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ኃላፊዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት ከአራት ወር በኃላ ጠንካራ የሆነ ድምፅ ከግብፅ በኩል ባለፈው ነሐሴ ወር ተደምጧል፡፡ የዚህ ጠንካራ ድምፅ ይዘት በህዳሴ ግድቡ ላይ የተጀመረው ውይይት ያለ ውጤት መጓተቱ፣ የግድቡን የውኃ አሞላል በተመለከተ የተጨበጠ ስምምነት አለመደረሱ፣ በግብፅ ላይ የፈጠረውን ቅሬታና የተናጠል መንገድ የመከተል አዝማሚያ ስለመኖሩ ያመላከተ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህንኑ መልዕክት የያዘውን አቋም የግብፅ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ ሥልጣን ለያዙት የሱዳን አቻቸው ካደረሱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ይህንኑ የመንግሥታቸውን አቋም ለኢትዮጵያ አቻቸው ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) አቅርበው በይዘቱ ላይም የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት እንዲካሄድ የመንግሥታቸውን ጥሪ አቅርበው ተመልሰዋል፡፡ ግብፅ ውይይቱ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ እንዲደረግ ብትጠይቅም፣ በኢትዮጵያ በኩል የውይይቱ ጊዜ እንዲገፋ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ተላልፎ ባለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በግብፅ ካይሮ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ሳይንሳዊና የሦስቱንም ባለድርሻ አገሮች ጥቅም ባማከለ ቅኝት ሲያደርጉት ከነበረው ውይይት ወደ ጎን በመውጣት፣ የራሷን የተናጠል የውኃ ሙሌት ዕቅድ የያዘ ሰነድ ለመድረኩ አቅርባለች፡፡

በውኃ፣ መስኖና ኤሌክሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ግብፅ ከመጓዙም በፊት መረጃው ደርሶት ስለነበር አቋም የያዘበት ጉዳይ በመሆኑ፣ በካይሮ በተካሄደው ውይይት በግብፅ በቀረበው ሰነድ ላይ እንደማይነጋገር አሳውቋል፡፡ የውይይቱ ትኩረት በግብፅ የቀረበው ሰነድ ችግሮች ዙሪያና አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ በተባሉ መፍትሔ ሐሳቦች ላይ ማጠንጠኑን፣ የሚኒስትሩ አማካሪና የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ግብፅ በተናጠል ባቀረበችው ሰነድ ከተመለከቱትና በኢትዮጵያ መንግሥት በእጅጉ ከተተቹት ነጥቦች ዋነኛው፣ “የግድቡ የውኃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ እንድትለቅና ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ ዝቅተኛ የውኃ ይዞታ የግድቡ 165 ሜትር መሆኑን ማረጋገጥ፣ የአስዋን የውኃ መጠን በዚህ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውኃ ላይ መልቀቅ እንደሚኖርባት የሚጠይቅ ነው፤” ሲሉ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ውይይት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹ግብፅ ከዚህም በላይ የክትትልና ሱፐርቪዥን አካል ቢሮውን በሁለቱም አገሮች በመክፈት ሥራውን በቅርበት እንዲያከናውን የሚለው ሉዓላዊነትን ጭምር የተዳፈረ ነው፡፡ ስለዚህ በፍጹም ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በግብፅ በኩል የቀረበው ሐሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ አገሮች መካከል የተፈረመውን የዓባይ ውኃ አጠቃቀም የመርህ ስምምነት የጣሰና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ያልተከተለ እንደሆነና በግድቡ ምን ያህል ውኃ ነው የሚያልፈው? መቼና እንዴት ነው ውኃው የሚለቀቀው? የሚሉ ከውይይት ያልተሻገሩ ሐሳቦችን ሳይንስን ባልተከተለ በሚመስላቸው መንገድ ወስነው፣ በሌሎቹ ተደራዳሪ አገሮች ሊጭኑ የሞከሩበት ከትብብር መንፈስ ያፈነገጠ መሆኑን በመግለጽ የግብፅን ድርጊት ኮንነዋል፡፡

 “ግብፆች ተነስተው ይህንን ተቀበሉ የሚሉበት የድርድር ሒደት ተቀባይነት የለውም፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ግብፅ ከትብብር መንገድ በመውጣት በተናጠል ያቀረበችው አዲስ ሐሳብ ኢትዮጵያን አላስፈላጊና ጎጂ ግዴታ ላይ የሚጥል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዳደረገችው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በኩልም ግብፅ ያቀረበችው ሐሳብና መንገድ በትብብር ላይ ተመሥርቶ ከተጀመረው ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት መንገድ ያፈነገጠ በመሆኑ፣ እንዲሁም በአንድ አገር ግድብ ላይ ውሳኔን የመጫን ድርጊት መሆን እንደተነገራቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡና መረጃዎችን መሠረት ባደረገ፣ ሳይንሳዊ አሠራሩን በተከተለ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ለማገንዘብ መሞከሩን አስረድተዋል፡፡

“የውኃ ሙሌቱም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች በሒደት የሚወሰኑ እንጂ፣ አሁን ሊቋጭ የሚችል ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩን ባለሙያዎቻችን የሚገልጹት እንጂ፣ የግብፅ ኤክስፐርት ዓባይ ላይ ቁጭ ብሎ የሚናገረው አይደለም፤” ሲሉም ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሐሳቡን አለመቀበሏን ተከትሎ በተደረገው ውይይት የሦስቱ አገሮች ማለትም የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የባለሙያዎች ቡድን የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ የየአገሮቻቸውን የአሞላል ዕቅድ ይዘው ከመስከረም 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሱዳን ተገናኝተው እንደሚመክሩ መወሰኑን ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

አዲሱ የግብፅ አቋም አንድምታ ምንድነው?

የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን ዋና ተደራዳሪና የሚኒሰትሩ አማካሪ ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ በግብፅ በኩል የቀረበው ሰነድ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያሳጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 እንደ እሳቸው ማብራሪያ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለግብፅ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚኖርባት በመጥቀስ ግብፅ ያቀረበችው ጥያቄ፣ የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት ሒደት ከዚህ ቀደም ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ተፈጥሯዊ የዓባይ የውኃ መጠን በማይቀንስ መንገድ ይሆናል እንደ ማለት ነው፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ማብራሪያ ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት ግብፅ ከኢትዮጵያ ከሚፈሰው የዓባይ ውኃ የምታገኘው የውኃ መጠን ወደዚያ ገደማ በመሆኑ ነው፡፡

ይህንን የግብፅ ጥያቄ ኢትዮጵያ ተቀበለች ማለት፣ አይደለም የህዳሴ ግድቡን መሙላት በዓባይ ገባር ወንዞች ላይም ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ልማቶችን ማካሄድ አትችልም እንደ ማለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ግብፅ በፈረመችው የመርህ ስምምነት ላይ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለችውን የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት ወደ ኋላ ለመመለስ ምኞት ያለው እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በዓባይ ገባር ወንዞች ላይ የሚካሄድ ልማትም ሆነ የህዳሴ ግድቡ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ተፈጥሯዊ የውኃ መጠን ሊያስጠበቅ የማይችል መሆኑ ለማንም ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ በግብፅ በኩል እንዲህ ያለ ፕሮፖዛል መቅረቡ ግብፅ የራሷን ጥቅም ብቻ ለማረጋገጥ ያዘጋጀችው ስለመሆኑ ጌድዮን (ኢንጂነር) ጠቁመዋል፡፡

 በሌላ በኩል የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት በዝቅተኛ የአየር ንብረት ወቅት የግብፅን የአስዋን ግድብ ውኃ ከተወሰነ መጠን በላይ መቀነስ የለበትም የሚል ቅድመ ሁኔታ በግብፅ ፕሮፖዛል ላይ መካተቱ፣ ሌላው የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት በሌላ አገር ጥቅም አለመጓደል ላይ የተንጠለጠለ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡን ውኃ ሙሌት በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን አቋም ሲያስረዱም፣ “ግድቡን ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መሙላት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ማለትም ግብፅና ሱዳንን ከግምት በማስገባት፣ ግድቡ ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መሙላት እንደሚቻል ዝርዝር ሳይንሳዊ ማጣቀሻዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ፕሮፖዛል ለሁለቱም አገሮች እንዲቀርብ ተደርጓል፤” ብለዋል፡፡

ግብፅ በድንገት ይህንን አዲስና ካለፉት ዓመታት ከመጣችበት መንገድ የወጣ አቋም ለማራመድ ምን ገፋፋት የሚለው ጥያቄ በሒደት እየተገለጠ የሚመጣ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ያነጋገራው አንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ግብፅ ያንፀባረቀችው አዲስ አቋም ሳይሆን በምክክር ታሽቶ የሰከነ የመሰለው የቀድሞ አቋሟ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ግብፅ የቀድሞ አቋሟን በድጋሚ አንፀባረቀች ማለት ወደ ኋላ ተመለሰች ማለት እንዳልሆነ፣ ይህንንም ለማድረግ የሚቻልበት ነባራዊ ሁኔታ ካለፈ እንደቆየ የሚናገሩት እኚሁ ኃላፊ፣ ወደዚህ አቋም ምን ገፋፋት ለሚለው ግን ሦስት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ፡፡

በቀዳሚነት ያስቀመጡት ዋነኛ ምክንያት በሱዳን ተከስቶ የነበረው የፖለቲካ ቀውስና ይህ ቀውስ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  የተጫዋቱት አዎንታዊ ሚና፣ ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን የፖለቲካ ተዋናዮችም ሆነ በመላው የሱዳን ሕዝብ ዘንድ ያገኙት ዕውቅና በግብፅ ዘንድ ሥጋት እንደቀሰቀሰ ይገልጻሉ፡፡

 ኢትዮጵያ በቅርቡ የሱዳን የፖለቲካ ቀውስ እንዲፈታ ያበረከተችው አስተዋፅኦ ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ላይ ከዚህ ቀደም ያንፀባረቀችው አቋም ታክሎበት፣ ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ የበላይነትን እንድትይዝ ያደርጋታል የሚል ሥጋት መቀስቀሱን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ግብፅ አዲሱን አቋሟን ያቀረበችውም ከዚሁ የሱዳን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከተፈታበት ወቅት ጋር የተገናኘ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የህዳሴ ግድቡ የገጠመውን የግንባታ መጓተት ለመፍታት ትኩረት በመስጠት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው መፋጠን እንዲችል የቀየሱት ስትራቴጂ ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ይኸውም ከኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ውስጥ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁት የተርባይን ጀኔሬተሮች የማምረት ተግባር፣ በሁለት የቻይና ኩባንያዎች በቻይና እንዲመረቱ መወሰኑ ሌላው የሥጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

አጠቃላይ የተርባይን ጀኔሬተሮች የማምረቱ ሥራ በቅርብ ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑና ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት የግድቡ ግንባታን እንደሚያፋጥነው ግብፅ መገመቷና፣ የግድቡ ውኃ አሞላልን የተመለከተው ድርድር ደግሞ ባለበት የቆመ መሆኑ ሥጋት የጫረባት ግብፅ፣ ድርድሩ ወደ መስመር እንዲገባ የተለየ ጫና ለመፍጠር የቀየሰችው ሥልት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በግብፅ ውስጥ የሚስተዋለው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ (ዕድገት መቆም) በአገሪቱ ዜጎች በተለይም በወጣቶቿ ላይ እየፈጠረ ያለው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይወልድ ትኩረት ማስቀየሪያ አጀንዳ ሊፈጥርላቸው እንደሚችል ያስረዱት ኃላፊው፣ ለዚህ አስተያየታቸው ማጠናከሪያም ሰሞኑን የግብፅ ፕሬዝዳንት ለግብፅ ወጣቶች ያስተላለፉት መልዕክት ይህን ሁኔታ እንደሚያስረዳ ገልጸዋል፡፡

“በግብፅ ተፈጥሮ የነበረው የተቃውሞ ማዕበል ባይከሰት ኖሮ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቧን በዓባይ ወንዝ ላይ ባልገነባች ነበር፤” ያሉት ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ የግብፅ ወጣቶች አሁንም ፖለቲካ ነክ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ላይ ተጠምደው አገራቸውን ዋጋ ከማስከፈል እንዲጠነቀቁ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -