Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ1.2 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ የሚጠይቅ ውዝፍ ፍላጎት ለማስተንፈስ የተነሳው ባንክ   

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሚታየው የመኖሪያ ቤት ችግር ከፍተኛነት ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ችግሩን ለማቃለል ሲደረጉ የቆዩ ጥረቶችም የቤት ፈላጊዎችን ፍላጎት ሊያሟሉ ባለመቻላቸው የቤት ዕጦት ችግር ይብሱን እያየለ እንዲመጣ አስገድዷል፡፡

ረቡዕ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን ያስታወቀውና በምሥረታ ላይ የሚገኘው ጎህ የቤቶች ባንክ አደራጅ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን ናና እንደገለጹት፣ በአገሪቱ የተከማቸውን ውዝፍ የቤት ፍላጎት ለማሟላት 1.2 ሚሊዮን ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ የቤት ፍላጎቶችን ለማሟላት ከ100 ሺሕ ቤቶች በላይ በየዓመቱ መገንባት ግድ ይሆናል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡

 የአፍሪካ ተደራሽ ቤቶች ፋይናንስ ማዕከል የተሰኘ ተቋም ባካሄደው ጥናት መሠረት፣ በአገሪቱ ከተሞች ካሉት ቤቶች ውስጥ 70 በመቶዎቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ለሰው ልጅ መኖሪያነት የማይመቹ በመሆናቸው ፈርሰው መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአሮጌዎቹ መኖሪያ ቤቶች የቆርቆሮ ክዳኖች ዝገውና ተበሳስተው በላስቲክ የተሸፈኑና በድንጋይ የተደገፉ፣ ግድግዳዎቻቸው የዘመሙና በድጋፍ የቆሙ፣ የአፈር ወለላቸው  ክረምት በመጣ ቁጥር የሚጨቀይ፣ መውጫ መግቢያቸው የተፋፈጉና ለመተላለፍ የማያመቹ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ የሌላቸው ስለመሆናቸው አቶ ጌታሁን አብራርተዋል፡፡ ችግሩ የቤት እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ደረጃውን ያልጠበቀና የማይመች ቤት መገንባት ጭምር እንደሆነም የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የባንኩ አደራጅ ቦርድ ሰብሳቢ ይናገራሉ፡፡

የጎህ ቤቶች ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ መጀመርን አስመልክቶ በክብር እንግድነት የተገኙት የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ አቶ ጌታሁን የጠቀሷቸውን አኃዛዊ መረጃዎች አጠናክረዋል፡፡ በከተሞች አካባቢ የሚታየው የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ዝቅተኛ መሆኑ፣ በመላው የኢትዮጵያ ከተሞች የ1.2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጉድለት መኖሩን እንደሚያረጋግጥ እሳቸውም ጠቅሰውታል፡፡  

መንግሥትም ይህንን ሁኔታ በሚገባ በማጤን በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ በዚህ ረገድ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን በመቅረፅና ሥራ ላይ በማዋል ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ለቤት ግንባታ ምቹና አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ጀምሮ የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራሞችን በመቅረፅ በአገሪቱ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰባችን ክፍሎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት ማድረጉንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል 1,673 ቤቶችን በቤቶች ኮርፖሬሽን በኩል ለመገንባት የ1.2 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ ወደ ሥራ እንደተገባ በመግለጽ፣ ለቤቶች ግንባታ እስካሁን የተሠራውንና የታቀደውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት እየገነባም የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎትና አቅርቦት ሊጣጣም እንዳልቻለ የጠቀሱት አይሻ (ኢንጂነር)፣ የቤቶች ግንባታን ማስፋፈት የውዴታ ግዴታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ እውነታም ክፍተቱን ለመሙላት በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን በማስተባበርና በመቀናጀትም ጭምር ሊረባረቡ እንደሚገባ አመላካች መሆኑን ያሳያል በማለት የችግሩን ስፋት ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ላይ በመኖሪያ ቤቶች ችግር ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት አንጋፋው የባንክ ባለሙያና ከአደራጆቹ አንዱ የሆኑት አቶ እሸቱ ፋንታሁን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቤት አቅርቦት ችግርና በላይ በላዩ እየተከማቸ የመጣው የቤት ፍላጎት፣ አቶ ጌታሁንም ሆኑ ሚኒስትር አይሻ ከጠቀሷቸው አኃዞችም በላይ እንደሚሆን ይሞግታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቤት ችግር 1.2 ሚሊዮን ነው መባሉን  እንደማይስማሙ የገለጹት አቶ እሸቱ፣ ‹‹10 ሚሊዮን ወይም 20 ሚሊዮን ቢባል እንኳ አይገልጸውም፤›› ይላሉ፡፡

ቤት የሚያስብል ይዘት የሌላቸው መጠለያዎች ቁጥር በርካታ መሆኑ ለዚህ አባባላቸው አንዱ መነሻ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል ታዳጊ አገሮች ይህ ነው የሚል ሥራ ባለመሥራታቸው፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መባባሱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች ለቤት ግንባታዎች የሚውለው ሀብት ዝቅተኛ በመሆኑ ሚሊዮኖች ቤት አልባ ለመሆን እንደሚገደዱ አውስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የቤት ልማትን ለማስፋፋትና እጥረቱን ለማጥበብ የተኬደበት መንገድ በርካታ ፈተናዎች ያስተናገደና ከስኬት ይልቅ ውድቀት የበዛበት እንደነበር ጠቁመው፣ ምቹ ሁኔታዎች በነበሩባቸው ጊዜያትም ችግሩ ሊፈታ እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡  

በቤት ግንባታ ዙሪያ በዓለም ዙሪያ ያለውን ገጽታም አስቃኝተዋል፡፡ በዘርፉ ይፋ የተደረጉ አኃዛዊ መረጃ በማጣቀስ እንዳመለከቱትም፣ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በቤት ልማት ላይ ያለባቸውን ችግርን ለመቅረፍ እጅግ ብዙ ሥራ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ነው፡፡ በተለይ ለቤት ግንባታ እየዋለ ያለው የሀብት መጠን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ እየተከማቸ የሚገኘው የቤት ፈላጊ ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡

በዚህ ረገድ በአፍሪካ የሚታየው ሁኔታ ከሌሎች አካባቢዎች እንደሚለይ ለማመላከትም፣ የአውሮፓ ባንኮች ከሚያመነጩት ሀብት ከ30 እስከ 106 በመቶ ለቤት ግንባታ ያውላሉ ብለዋል፡፡ ከፍተኛውን ብድር የሚሰጡትም ለቤት ግንባታ እንደሆነ ማሳያዎችን ያቀርባሉ፡፡ በአፍሪካ የተደረገው ጥናት ግን አገሮቹ ከሚያመነጩት ሀብት ውስጥ ለቤት ግንባታ የሚውሉት አንድ በመቶ እንኳ እንደማይሞላ ተወስቷል፡፡ በጠቅላላው ታዳጊ አገሮች በቤት ግንባታ ላይ የሚያውሉት ኢንቨስትመንት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በገለጻቸው አመላክተዋል፡፡ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ለቤት ሥራ ከተደራጁ የፋይናንስ ተቋማት ብድር የሚያገኘው ሕዝብ ቁጥር 500 ሺሕ እንደማይበልጥ ይገመታል፡፡

በአንፃሩ ያደጉ አገሮች ከብሔራዊ ሀብታቸው እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን ለቤት ሥራ ብድር ያውላሉ ተብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ለግለሰብ ገንቢዎች ብሎም በጋራ ለሚኖሩ ዜጎች የሚውል ነው፡፡ የኢኮኖሚያቸውም ምንጭ ከዚሁ የቤት ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡  

በማደግ ላይ የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ለቤት ልማት ትኩረት እንዳልሰጡ አመላካች አኃዞችን ያጣቀሱት አቶ እሸቱ፣ እነዚህ አገሮች እጅግ ደካማ ፖሊሲ መከተላቸውም ከዘርፉ ዝቅተኛ ውጤት ጋር እንደሚያያዝ ያነሳሉ፡፡ የፖሊሲ፣ የመሬት አስተደደር ሥርዓት፣ ለቤት ሥራ ትኩረት አለመስጠትና የመሳሰሉት ከዋና ዋና ችግሮች ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ የአብዛኛዎቹ ታዳጊ አገሮች ከቤት ሥራ ጋር የተያያዘ ፖሊሲ ቀጣይነትና ትኩረት የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች ችግር በአፍሪካ ውስጥ 2014 ዓ.ም. ጥናት ከ40 እስከ 80 ካሬ ሜትር ቦታ የሚያስፈልጋቸው በከተማ ውስጥ ያሉ (ገጠሩን ሳይጨምር) የመካከለኛና ዝቅተኛ ኅብረተሰብ ክፍል ወደ 51 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለ ያሳያል፡፡

አፍሪካ ውስጥ 17 አገሮች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተመዘገበ የቤት እጥረት አለባቸው፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የቤት ግንባታ ላይ ያተኮረ ባንክ ለማቋቋም ሲገባም ታሳቢ የተደረገው የአንድ ሚሊዮን ቤት ፍላጎት መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በጥቅል ሲታይ በጥናቱ መሠረት ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ ከተሞች 40 ካሬ ሜትር በሚሆን ቦታ ላይ ቤት ለመገንባትና ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ከተፈለገ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አፍሪካ 2.1 ትሪሊዮን ዶላር ለዚህ ሥራ ማዋል ይጠበቅባታል፡፡

እንዲህ ያለው ችግር በመንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ ስለዚህ እንደ ጎህ ያለ ባንክ መቋቋሙ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የባንኩ አደራጆች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን፣ በምሥረታ ላይ ያለው የጎህ ቤቶች ባንክ ዓላማም ይህንን አገራዊ ጥልቅና ሰፊ ችግር ለመፍታት በመንግሥት፣ በማኅበረሰቡና በግሉ ዘርፍ የሚደረገውን ጥረት ማገዝና የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ሥር የሰደደውን ችግር ደረጃቸውን በጠበቁ ዘመናዊ ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ በማስቻል ቢቃለል ተገቢ ይሆናል ይላሉ፡፡ ባንኩ ተመሥርቶ ሥራ ሲጀምር አዳዲስ የመኖሪያ ቤት ለሚገነቡ፣ ያላቸውን ቤት ለማደስ፣ ለማሻሻልና ለማስፋፋት ለሚፈልጉ፣ መኖሪያ ቤት ሠርተው ለሚያከራዩና ለሚሸጡ፣ እንዲሁም መኖሪያ ቤት ለሚገዙ እንደየፍላጎታቸው፣ የመክፈል አቅማቸውና አዋጪነታቸው ተመጣጣኝ የገንዘብ ብድር ይሰጣል፡፡ ይህንን በማድረግ የቤቶችን ልማት በመላ የአገሪቱ ከተሞች በፍጥነትና በጥራት ያስፋፋል የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ተመሥርቶ ሥራ ሲጀምር በአገራችን የባንክ ኢንዱስትሪና በቤቶች ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደሚያምኑም ያመለከቱት አቶ ጌታሁን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች በተለያዩ ምክንያቶች የቤት ብድር የሚሰጡት ፈራ ተባ እያሉ በመሆኑ፣ ጎህ ቤቶች ባንክ ይህንን ሰብሮ ለቤቶች ብድር በመስጠት ላይ ያተኩራል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትም በአነስተኛ ወጪ ውጤታማ ሥራ ይሠራል፡፡ ከሌሎች ባንኮች፣ እንዲሁም አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋርም ከውድድር ይልቅ በትብብር መሥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩም ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ሥራ ሲጀምር፣ በቤቶች ግንባታ ሥራ የዘርፉን ተዋናዮች በማስተባበርና በጥናት ላይ በመመሥረት የመኖሪያ ቤቶችን በጥራት በተፋጠነ ጊዜና፣ ወጪ በሚቆጥብ መንገድ እንዲገነቡ ብሎም የተጠቃሚውን አቅም ባገናዘበ ዋጋ እንዲያቀርቡ ጥረት እንደሚያደርግ የባንኩ አደራጆች አብራርተዋል፡፡ ባንኩ በአብዛኛው በቤቶች ብድር ላይ የሚያተኩር ቢሆንም፣ የቁጠባና የአጭር ጊዜ ብድርን ጨምሮ ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን ለተገልጋዮች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ እሸቱ ከሆነም፣ እንዲህ ያለው ውጥን ከግብ ለማድረስ አሁን ባለው የመንግሥት ፖሊሲ ምቹ መሆን የግድ መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በዚሁ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እጅግ ከፍተኛ አገራዊ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑንም ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ የግድ እንደሆነ በዘርፉ የተደረገው ጥናት ያሰፈረውን የድምዳሜ ሐሳብ ገልጸዋል፡፡ በጥናቱ መደምደሚያ የተቀመጠው ሐሳብ፣ ከጦርነት በላይ ለአፍሪካ መበጣበጥ፣ ለአፍሪካ መጥፋትና መውደቅ ምክንያት ሊሆን የሚችል ችግር የቤት ዕጦት እንደሚሆን ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ከመሆኑ ባሻገር በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ሌላው ጠቀሜታ ሥራ ዕድል መፍጠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የአፍሪካ አገሮች በአሥር ዓመት ውስጥ ተባብረው የቤት እጥረቱን ቢያቃልሉ ለ280 ሚሊዮን ወጣቶች ሥራ የመፍጠር አጋጣሚ ይፈጥራል ያሉት አቶ እሸቱ፣ የአፍሪካ መሪዎች ይህንን ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦትን በተመለከተም በአገራችን የፋይናንስ ተደራሽነት በተለይ ለቤቶች ግንባታ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የዓለም ባንክ መረጃዎች በኢትዮጵያ ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ውስጥ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙት 35 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን ያመለከቱት አይሻ (ኢንጂነር)፣ የጎህ ባንክ መከፈት ይህንን ተደራሽነት በማስፋት የራሱ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በአገራችን ከሚገኙ ባንኮች ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ግዥና ማስፋፊያ የሰጡት የብድር መጠን ከጠቅላላው የብድር ክምችት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ በይፋ የተመሠረተው ጎህ የቤቶች ባንክ አክሲዮን ማኅበር የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፋይናንስ ተደራሽነት ችግርን በማቃለል በኩል ትልቅ አቅም እንደሚሆን እተማመናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የባንኩ ሥራ መጀመር ለኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለሪል ስቴት አልሚዎች፣  በራሳቸው ቤት ለሚገነቡ ዜጎች አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ያለውን የመኖሪያ ቤት ዕጥረት ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትር ዓይሻ ባደረጉት ንግግር፣ ለቤት ሥራ ገንዘብ የሚያቀርበው ባንክ ሐሳብ፣ ‹‹ከቢዝነስም በላይ ነው፤›› ብለውታል፡፡ መንግሥት የፋይናንስ ተቋማትን ለማገዝ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ በሥራ ወቅት ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ መንግሥት የበኩሉን ዕገዛ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለዚህም መንግሥት የፋይናንስ ተቋማትን ሪፎርም ለማድረግ እየሠራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በየትኛውም አገር ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እዚህ ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ ዕድል መሰጠቱም መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ሌሎች ለቢዝነስ ምቹ የሆኑ ሪፎርሞችም ብዙ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ለምሳሌ ቢዝነስ ለመጀመር እዚህ አገር የነበሩ የተወሳሰቡ ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ነው፡፡

እንዲህ ባለው ባንክ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ዋጋ ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ ባለሀብቶችም በዚህ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ የሚል እምነት ያላቸው መሆኑንም በመግለጽ ባለሀብቶች በዘርፉ መሳተፋቸው ለራሳቸውም ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

በዕለቱ በመድረኩ ላይ ሐሳባቸውን ያንፀባረቁት ሦስቱም ተናጋሪዎች እንዲህ ያለው ተቋም አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ያለውን ጎህ ባንክ ሒደት በተመለከተ አቶ ጌታሁን፣ ‹‹ጎህ ቤቶች ባንክ በአገራችን ካሉት ባንኮች ልዩ የሆነ፣ የመጀመርያው የግል በቤቶች ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር ባንክ ከመሆኑም በላይ ባንኩ አትራፊ በመሆኑ ዜጎች የዚህ ባንክን አክሲዮን በመግዛት ሊጠቀሙ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡  

ባንኩን የማቋቋሙ እንቅስቃሴ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አዋጪነቱ ላይ ጥናት ስለመደረጉ የገለጹት አቶ ጌታሁን፣ የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው ባንኩ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ማኅበራዊ ልማትና ሥራ ፈጠራ የራሱን በጎ ሚና የሚጫወት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ተቋሙን ለሚመሠርቱት ባለአክሲዮኖች ጠቀም ያለ ትርፍ ያስገኛል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ አቶ እሸቱም ባንኩ ባደረገው ጥናት ሥራ ቢጀመር በመጀመርያው ዓመት 40 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፍ በየዓመቱ ትርፉን እያሳደገ የሚሄድ መሆን የሚያሳዩ አኃዛዊ መረጃዎችን አመላክተዋል፡፡

ጎህ ባንክ ዋና መሥራች ውስጥ አምስቱ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አምስቱ ደግሞ ከዚሁ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ምሁራንና ባለሀብቶች መሆናቸው መገለጹ አይዘነጋም፡፡ ጎህ የቤቶች ባንክ የአክሲዮን ሽያጩን በተመለከተ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው አንድ አክሲዮን አንድ ሺሕ ብር አለው፡፡

እያንዳንዱ አክሲዮን ገዥ ቢያንስ 50 አክሲዮኖችን መግዛት የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ከፍተኛው የአክሲዮን ግዥ ጣሪያ 50 ሺሕ ነው፡፡ አከፋፈሉም ግማሹ አክሲዮን በተገዛበት ወቅት ወዲያው ይፈጸማል፡፡ ባንኩ የሚቋቋመው በአንድ ቢሊዮን ብር በተፈረመ ካፒታልና በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንደሆነም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች