Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከ160 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በበጀት ዓመቱ ሁለት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላከ 57 ሺሕ ቶን የሚጠጋ የቡና ምርት 168 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በሁለት ወራት ውስጥ ማለትም ከሐምሌ እስከ ነሐሴ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ 52,300.00 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 183.57 ሚሊዮን  ዶላር ገቢ እንደሚገኝ ታቅዶ ነበር፡፡ ሆኖም  ከዕቅዱ በላይ 57 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 167.65 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊገኝ እንደቻለ ታውቋል፡፡

ይህ አፈጻጸም በ2011 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከተላከው የቡና መጠን ጋር ሲነፃፀር፣ የ6,585.14 ቶን ጭማሪ አሳይቷል ያለው ባለሥልጣኑ፣ ከመዳረሻ ገበያዎች አኳያም ጀርመን ትልቁን ግዥ በመፈጸም ቀዳሚዋ እንደሆነች አስታውቋል፡፡

ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት፣ በ2012 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ብቻ ከቡና በተጨማሪ 32,254 ቶን ሻይና ቅመማ ቅመም በመላክ 108.37 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር አስታውቆ፣ 31,916 ቶን ምርት ወይም የዕቅዱን 98.95 በመቶ ያሟላ ምርት እንዳቀረበና 88.22 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳስገኘ ገልጿል፡፡ ሆኖም ገቢው ከዕቅዱ የ81.40 በመቶ ክንውን የታየበት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከተላከው መጠን አኳያም የ7,024 ቶን ወይም የ28 በመቶ እንዲሁም በገቢ ረገድ የ5.5 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ተመዝግቦበታል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ 56,479.97 ቶን የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ወደ ውጭ እንደሚላክ፣ ከዚህም በጠቅላላው 189 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 59,965.49 ቶን ወይም ከዕቅዱ 104.4 በመቶ እንደተላከ ባለሥልጣኑ አስታውቆ፣ 169.76 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊገኝ መቻሉን ገልጿል፡፡ በአፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የ6,557 ቶን እንዲሁም የ5.27 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ጭማሪ መመዝገቡ ታውቋል፡፡

ከዚህ ውስጥ የቡና ወጪ ንግድ በተናጠል ሲታይም በነሐሴ ወር 29,944  ቶን ቡና ወደ ውጭ እንደሚላክና 105 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ ታቅዶ፣ በውጤቱም 30,279 ቶን ወይም ከዕቅዱ 101 በመቶ በላይ  ቡና ተልኮ 87 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊገኝ ችሏል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ሲታይ፣ በመጠን የ6,585.14 ቶን ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ በገቢ በኩልም የስድስት ሚሊዮንን ዶላር ጭማሪ ተመዝግቦበታል፡፡

የኢትዮጵያን ቡና ከሚገዙ መዳረሻ አገሮች አኳያም፣ በሁለቱ ወራት ውስጥ ከተላከው ቡና ውስጥ ጀርመን 13,434 ቶን ወይም 24 በመቶ ድርሻ በመያዝና የ33.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ20 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የ22.85 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ14 በመቶ የገቢ ድርሻ የያዘ 8,551 ቶን ቡና በመግዛት ትከተላለች፡፡

ጃፓን 7,218 ቶን ቡና በ19.62 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ሦስተኛዋ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ ስትሆን አሜሪካ አራተኛ፣ ቤልጂየም አምስተኛ፣ ቡብ ኮሪያ ስድስተኛ፣ ጣሊያን ሰባተኛ፣ ሱዳን ስምንተኛ፣ ፈረንሣይ ዘጠነኛ እንዲሁም አውስትራሊያ አሥረኛ ደረጃ በቅድመ ተከተል ይዘዋል፡፡ እነዚህ አገሮች በመጠን የ85 በመቶ፣ በገቢ ረገድም የ82 በመቶ ድርሻ በመያዝ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ፣ አሥሩ ዋና ዋና የቡና መዳረሻ አገሮች ከ2011 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት አኳያ፣ 34 በመቶ የመጠን ጭማሪና በገቢ የ14 በመቶ የገቢ ዕድገት የታየበትን ግዥ ፈጽመዋል፡፡

የቡናው ዘርፍ በጀት ዓመቱን እንዲህ ቢጀምርም፣ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ በዓለም ገበያ በመታየቱ ሳቢያ፣ ከ760 ሚሊዮን ዶላር ብዙም ያልገፋ ገቢ በማስገኘት ዓመቱን ማገባደዱ ይታወሳል፡፡ ይህም ይባል እንጂ በቡና ንግድ መስክ አዳዲስ ወንጀሎች እየተከሰቱ ዘርፉ ማመስ የጀመሩበት ዓመት ሆኖ የተሸኘው የ2011 ዓ.ም. የታሸጉ ኮንቴይነሮች በምሥጢራዊ ዘዴ እየተከፈቱ ቡና መቀሸቡ አቤቱታ የቀረበበት ዓመት ነበር፡፡

የኮንቴይነር ቅሸባ ካጋጠማቸው መካከል ቴስቲ ኮፊ ትሬዲንግ፣ ሙለጌ፣ ሲዳማ ቡና አምራቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን፣ አባሃዋ ትሬዲንግና ፋህም ጄኔራል ትሬዲንግ ከታሸገ ኮንቴይነር ውስጥ ቡና እንደተወሰደባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከስድስቱ ኩባንያዎች የተዘረፈው ቡና መጠኑ 150 ኩንታል እንደሚደረስ ተዘግቧል፡፡ ይሁንና ታደሰ ደስታና ትራኮን ትሬዲንግ ብቻቸውን 400 ኩንታል የሚጠጋ ዝርፊያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ሦስት ጊዜ ዝርፊያ እንዳጋጠማቸው ለሪፖርተር ያስታወቁት፣ የታደሰ ደስታ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ደስታ፣ ወደ ሩስያ፣ ፖርቹጋልና ታይዋን ከተላኩ ቡናዎች ውስጥ በሦስት ኮንቴይነሮች ላይ ቅሸባ ተፈጽሟል፡፡ ይኸውም ወደ ሩስያ ከተላከ ቡና መካከል ከአንድ ኮንቴይነር ውስጥ ባለ 60 ኪሎ ግራም 70 ኬሻ ተወስዷል፡፡ ወደ ፖርቹጋል ከተላከው ቡናም ከአንድ ኮንቴይነር ብቻ 64 ኬሻ ባለ 60 ኪሎ ግራም ቡና መጉደሉ ሲታወቅ፣ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ወደ ታይዋን ከተላከ የልዩ ጣዕም ቡና ውስጥ ከአንድ ኮንቴይነር በ30 ኪሎ ግራም መጠን የታሸገና ብዛቱ 124 ኬሻ እንደተወሰደ አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ አንድ ኮንቴይነር ውስጥ በአብዛኛው 320 ኬሻ ቡና እንደሚይዝ ያብራሩት አቶ ታደሰ፣ ከአንድ ኮንቴይነር ግማሽ ያህሉ ቡና መዝረፍ የተጀመረበት ክስተት መታየቱ ቅሸባው አደጋ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል፡፡ ከሦስት ኮንቴይነር ውስጥ የተዘረፈው ቡና መጠን በኩንታል ሲገለጽ መጠኑ 135 ኩንታል እንደሚያወጣና በመሸጫ ዋጋውም እስከ 42 ሺሕ ዶላር እንደሚደርስ መገለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን ችግር ለመቆጣጠር መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራ ግብረ ኃይል እንዳቋቋመና የወንጀል ክትትል እያካሄደ እንደሚገኝ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይህ ይባል እንጂ የደረሰበት ውጤት ምን እንደሆነ እስካሁን ይፋ አላደረገም፡፡

በሌላ በኩል ከዋጋ በታች በመሸጥና የሽያጭ ስምምነትን በመጣስ በተደጋጋሚ ሕግ ሲተላለፉ ተገኝተዋል ባላቸው ቡና ላኪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥሪም ማስጠንቀቂያም አስተላልፎ ሊቀርቡ አልቻሉም ባላቸው 81 ነጋዴዎች  ላይ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በሐምሌ ወር ዕግድ ማውጣቱን አስታውቆ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 26 ቡና ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ መወሰኑም አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ከ266 ያላነሱ ነጋዴዎች ላይ ከዋጋ በታች በመሸጣቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደጻፈላቸውም ተዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች