Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ላይ ለመድረስ ረጅም መንገድ መጓዝ ይጠበቅባታል›› ሚስተር ድሬክ ሒውስተን፣ የቱሪዝም ባለሙያ

ላለፉት 20 ዓመታት በአፍሪካ የጉብኝትና የጉዞ መርሐ ግብሮች ላይ በማተኮር፣ ‹‹ስፖትላይት ትራቭል ኤክስፖ›› በሚል ስያሜ በቱሪዝም መስክ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ የሒውስተን ትራቭል ማርኬቲንግ ሰርቪስስ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ሚስተር ሒውስተን፣ የጉዞ ዓውደ ርዕያቸው መዳረሻ ካደረጓቸው ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ስትሆን ለአራት ዙር ያህል ዓውደ ርዕያቸውን በአዲስ አበባ አሰናድተዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም በስካይ ላይት ሆቴል የጉዞ መዳረሻዎችን የሚያስቃኙና በቱሪዝም መስክ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን የዳሰሱ፣ በርካቶች የተሳተፉበትን የጉዞ ዓውደ ርዕይ ያሰናዱት ሚስተር ድሬክ ሒውስተን፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው የሒውስተን የጉዞ ድርጅት መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡ በበርካታ አገሮች የሚንቀሳቀሰው ይህ ድርጅት፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ባካሄደው ርዕይ የዘርፉን ተዋንያን ሲያገናኝ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትም ከተሳተፉትና ዓውደ ርዕዩን ካገዙት አንዱ ነበር፡፡ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ከሚያስዋውቅባቸው አዳዲስ መንገዶች አንዱ በሆነው በሥሪ ዲ ቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል መነጽር ወይም ጉግል የታዘገ የቨርቹዋል ማስጎብኛ ዘዴ፣ በርካቶችን ሲያዝናናበት በነበረው በዚህ ዓውደ ርዕይ የበርካታ አገሮች ተሳታፊዎች ታድመው  ነበር፡፡ ከኬንያ፣ ከታንዛኒያ፣ ሲሼልስ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎችም አገሮች የተውጣጡ ሆቴሎች፣ የአየር መንገድ ኩባንያዎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎችም ታድመዋል፡፡ ምንም እንኳ የቱሪዝም መስኩ በአፍሪካ እያደገና እየተስፋፋ ቢመጣም፣ ያልተፈቱ ሥጋትና ማነቆዎች አሉበት፡፡ በተለይም የፀጥታና የብጥብጥ ሥጋቶች ጎብኚዎችን እንደሚያሸሹ የታወቀ ነው፡፡ ይህንን በመፍራት አገሮች ለዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያወጡ ከርመዋል፡፡ ኢትዮጵያም ላለፉት አራት ዓመታት ይህን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ ከሰሞኑም አሜሪካና እንግሊዝ አዳዲስ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች በማውጣት ዜጎቻቸው ቢቻላቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ፣ ከተጓዙም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እያሳሰቡ ነው፡፡ በተለይ እንግሊዝ ከጥቂት ቀናት በፊት ያወጣችው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ወደ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች እንዳይጓዙ ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች በሚፈታተኑት የቱሪዝም ዘርፉ ተስፋና ዕድገት እንዳለ የሚገልጹት ሚስተር ሒውስተን፣ ዘርፉን በሚመለከት ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም በተለይም በጉዞ ገበያው ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚታይበት ፈታኝ ጊዜ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከመነጋገራችን በፊት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የጉዞ ገበያ እንዴት እንደሚካሄድ ቢያብራሩልን?

ሚስተር ሒውስተን፡- ‹‹ስፖት ላይት ትራቭል ኤክስፖ›› ብለን የሰየምነው ጽንሰ ሐሳብ ዓላማው በአፍሪካ መካከል የጉዞና የጉብኝት እንቅስቃሴን ለማስፋፋት ያለመ ነው፡፡ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ አፍሪካ ክፍሎች መጓጓዝ ስለሚችሉባቸው አማራጮች የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚደረጉ ጉዞዎችና ጉብኝቶች እንዲስፋፉ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በአዲስ አበባ ለአራተኛ ጊዜ ያዘጋጀነው ይህ የጉዞ ዓውደ ርዕይ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ከቦታ ቦታ በመሄድ ጉብኝት እንዲያደርጉ ለማበረታታት በማሰብ የተሰናዳ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የአገር ውስጥ ጉብኝትና የጉዞ እንቅስቃሴዎችም ትኩረት ይሰጣቸዋል ማለት ነው?

ሚስተር ሒውስተን፡- በጉዞና ጉብኝት እንቅስቃሴ ውስጥ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ወይም የአገር ውስጥ ጉብኝት አንደኛው ትኩረታችን ነው፡፡ ይሁንና በአብዛኛው በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረጉ ጉብኝቶች እንዲስፋፉ፣ የሰዎች የመዘዋወርና የመጎብኘት ልማድ እንዲዳብር ለማድረግ እንሠራለን፡፡ እስካሁንም በዘርፉ ጥሩ ተቀባይነት አግኝተን እየሠራንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋምዎ እንዴት ነው የሚንቀሳቀሰው? ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር አብሮ በመሥራት ነው? እንዴት ነው በየአገሩ የምትንቀሳቀሱት?

ሚስተር ሒውስተን፡- በአፍሪካ በቱሪዝም መስክ ከተሰማሩ አካላት ጋር በሙሉ አብሬ እሠራለሁ፡፡ ለ‹‹ትራቭል ኤክስፖ ስፖት ላይት›› የምሠራውን፣ መቼና የት ዝግጅቴን እንደማካሂድ፣ እነ ማን እንደሚሳተፉበት፣ ምን ምን ጉዳዮች እንደሚካተቱበት አስታውቄና ዋጋዬን ገልጬ እልክላቸዋለሁ፡፡ በዓውደ ርዕዩ አንደኛው የጉዞና የጉብኝት ኩባንያ ከሌላው ጋር ይገናኛል፣ ይወያያል፣ የንግድ ስምምነት ያደርጋል፡፡ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት ድርጅቶችና ሌሎችም ይሳተፋሉ፡፡ በአብዛኛው ዓላማው የጉብኝት ገበያን ማስፋፋትና ማሳደግ ነው፡፡ ተሳታፊዎች እርስ በርሳቸው ይገናኛሉ፣ ይወያያሉ፣ አብረው ለመሥራት ይስማማሉ፡፡ በዚህ መንገድ የቱሪዝምና የጉዞ ገበያው እየተስፋፋ ይመጣል፡፡  

ሪፖርተር፡- በአራተኛው የአዲስ አበባ የጉዞና ጉብኝት ዓውደ ርዕይ እነ ማን ተገኝተው ነበር?

ሚስተር ሒውስተን፡- አየር መንገዶች በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋናው ተሳታፊ ነበር፡፡ የቻርተር በረራ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ተካተዋል፡፡ የኬንያ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ከታንዛኒያ ዛንዚባር ከተማ እንዲሁም ከሲሼልስ የመጡ የሪዞርትና የባህር ዳርቻ ሆቴሎች፣ የሲሼልስ ቱሪዝም ቦርድ ተወካዮች፣ የደቡብ አፍሪካ ተሳታፊዎችና ሌሎችም ተካተዋል፡፡ የሲሼልስ ተሳታፊዎች የቱሪዝም ፓኬጅ መዘርጋት ይፈልጋሉ፡፡ በየዕለቱ የሚደረግ በረራ በኢትዮጵያና በሲሼልስ መካከል እንዲስፋፋና የሁለቱ አገሮች ዜጎች ከአንዱ ወደ ሌላው አገር ጉብኝት ማድረግ የሚችሉባቸውን ፓኬጆች ለመዘርጋት ፍላጎት አላቸው፡፡ በተለይም ከአዲስ አባባ ወደ ሲሼልስ የሚጓዙ የኢትዮጵያ ቱሪስቶችን ይፈልጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የጉዞና የጉብኝት ዘርፉ እያደገ ነው? በእርስዎ ዕይታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አካሄዱ እንዴት ይገለጻል?

ሚስተር ሒውስተን፡- ዘርፉ በጣም እያደገና እየተለወጠ መጥቷል፡፡ የሆቴሎች መስፋፋት፣ የዜጎች የገቢ መጠን መጨመርና ለጉብኝትና ለጉዞ ያላቸው ፍላጎት ማደግ ዘርፉንም እያሳደገው መጥቷል፡፡ በርካታ የጉዞና የጉብኝት ተቋማት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ የጎብኚዎች ቁጥር ማደጉ ለብዙ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የትራንስፖርት ግንኙነት በተለይም የአየር ትራንስፖርት የማይታሰብ ከመሆኑና ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ተጉዞ መልሶ ወደ ሌላኛው የአፍሪካ አገር መጓዝ አሁንም ያለ ከመሆኑ አኳያ፣ በአፍሪካ የሚታየው የጉዞና የጉብኝት እንቅስቃሴ ፈታኝ ሊባል አይችልም?

ሚስተር ሒውስተን፡- ይህ እንግዲህ የቆየ ወይም ያረጀ ሐሳብ ነው፡፡ አሁን በጣም በፍጥነት እያደገና አንዱን አገር ከሌላው በትራንስፖርት የማገናኘት ሒደቱ፣ በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻዎች መስፋፋት ጋር ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ የኬንያ አየር መንገድም የተወሰነ ሚና ይጫወታል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትንሹ ወደ 45 የአፍሪካ ከተሞች ይበራል፡፡ ይህ በየቀኑ እየተቀየረ ነው፡፡ በየጊዜው ተጨማሪ አዳዲስ የበረራ መዳረሻዎች እየተካተቱ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ተቋማት ዋናዎቹ የጉዞና የጉብኝት ዘርፉን የሚያንቀሳቅሱ ኃይሎች በመሆናቸው፣ አፍሪካ ከሌላው ጊዜ በተሻለ በአየር ትራንስፖርት እየተሳሰረች ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቶጎ የበረራ ማዕከል ወይም ‹‹ሃብ›› አላቸው፡፡ ስለዚህም መንገደኞችን ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ደቡባዊ አፍሪካ ማጓጓዝ አስችሏቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማላዊ በሚገኘው ማዕከሉ፣ እንዲሁም በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ በረራ እያከናወነ ብቻም ሳይሆን፣ በዚያ በሚገኘው የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ በባለድርሻነት በመሳተፍ አገልግሎቱን ማስፋፋቱ፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በፈጣን ሁኔታ እየቀረው ይገኛል፡፡

      ከዚህ ቀደም ከማፑቶ ወደ ሰሜናዊ ሞዛምቢክ ለመጓዝ ሦስት ሰዓት ይፈጃል፡፡ ይሁንና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነበር፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመኖሩ ከዚህ ቀደም በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ የነበረው አሁን ተለውጦ ወደ ሁሉም አካባቢ መጓዝ ተችሏል፡፡ አሁን አንዱን አገር ከሌላው፣ አንዱን ከተማ ከሌላው ከተማ የማገናኘት እንቅስቃሴ በጣም እያተሻሻለና እየተለወጠ መጥቷል፡፡ በየጊዜው የሚታየው ለውጥ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ ከግንኙነት ባሻገር ሌላው በአፍሪካ ቱሪዝም ውስጥ የሚታየው ትልቅ ፈተና የቪዛ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ቪዛ በመጀመሯ፣ አሥር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኦንላይን ቪዛ ማግኘት መቻል ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሆናበታለች፡፡ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም አገሮች ይህንን ምሳሌ ይከተላሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ አንዳንድ አገሮች እንዲህ ያለውን ለውጥ ለመተግበር እተንቀረፈፉ ነው፡፡ ስለዚህ የአየር ትራንስፖርት ግንኙነትና የቪዛ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮች በቶሎ ተቀርፈው የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያሻሽሉት ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም መስኩ በተለይም በአስጎብኚነት በጉዞ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ትልቁ ሥጋታቸው ምንድነው? ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ አስጎብኚ ድርጅቶች የፀጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ በሌሎች አካባቢዎችስ ምንድነው ፈታኝ የሚባለው? የጉብኝትና የቱሪዝም ዘርፉ ችግር ምንድነው?

ሚስተር ሒውስተን፡- ወደ አፍሪካ ለሚመጡ ጎብኚዎች ፈታኝ የሚባሉት ፀጥታና ጥቃቶች፣ በተለይም በሆቴሎች አካባቢ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለበርካታ የቱሪዝም ዘርፉ ተዋናዮች አስቸጋሪ ሆነው የሚገኙ ናቸው፡፡ በጥቅሉ አፍሪካን በዓለም የቱሪዝም ገበያ ለማስተዋወቅ ሲፈለግ ፈታኝ የሆኑ ማነቆዎች አሉ፡፡ ዋና ዋናዎቹ ግን ከፀጥታና ከመሠረተ ልማት ጋር የሚያያዙት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የጎብኚዎች ቁጥር በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይም ከአውሮፓ የሚመጡ ጎብኚዎች ወደ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች የሚያደርጉት ጉዞና ጉብኝት እየጨመረ ነው፡፡

      ኢትዮጵያ በዚህ መስክ ቀድማ ትጠቀሳለች፡፡ በየዓመቱ የአሥር በመቶ የቱሪስቶች ቁጥር ዕድገት እየታየባት እንደምትገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጎብኚዎች እየመጡ ነው፡፡ ፈተናዎች ቢኖሩም አፍሪካ ከሁሉም አገሮች ለሚመጡ ቱሪስቶች ዋና መዳረሻ እየሆነች ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም አገር የየራሱ የቱሪዝም መስህብ አለው፡፡ አያንዳንዱ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ለአድቬንቸር ምቹ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌዠር ወይም መዝናኛና ሪዞርት ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ልታስፋፋው የሚገባት የቱሪዝም መስክ ‹‹ማይስ›› የተገኘውን ዘርፍ ነው፡፡ ይኸውም ስብሰባዎች፣ ኮንፈረንሶችና ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ተጓዦች ማበረታቻ የሚሆኑ አሠራሮችን ያቀፈውን ማይስ ቱሪዝም ማጎልበት፣ ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ይህንን መስክ ለመጀመር እንቅስቃሴው እንዳለ አውቃለሁ፡፡ በርካታ አማካሪዎችም እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሚያከናውን ቢሮ መቋቋሙም ይታወቃል፡፡ ይህ አንዱ ቢዝነስ ቱሪዝም የተሰኘው ዘርፍ ለማሳደግ ትልቅ መሣሪያ በመሆን ስለሚያገለግል ኢትዮጵያም ለዚህ ትኩረት መስጠቷ ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በርካቶች አድቬንቸር ወይም አስቸጋሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በመጎብኘት ምርምርና ሙከራዎችን በማካሄድ የሚሳተፉባቸው፣ እንዲሁም አሁን እንደተነጋገርነው ለስብሰባና መሰል ተሳትፎዎች የሚመርጧቸው የቱሪዝም መስኮችን ጨምሮ በርካቶች አሉ፡፡ ዋናው ግን የመዝናኛ ወይም ሌዠር የሚባለው የቱሪዝም መስክ በአፍሪካ ብዙም የጎላ ድርሻ ያለው አይመስልም፡፡ ስለዚህ ምን ይላሉ? የሌዠር ቱሪዝም በኢትዮጵያ እያደገና እየተስፋፋ ነው?

ሚስተር ሒውስተን፡- ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በሌዠር ቱሪዝም መስክ ላይ ብቻ በማተኮር ለበርካታ ዓመታት ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ የአድቬንቸር ዘርፉም በርካታ መስህቦች ያሉበት ነው፡፡ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሚታዩ በርካታ መስህቦች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሚጎበኙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ላሊበላ፣ አክሱምና ሌሎችም አሉ፡፡ በኬንያም የእንስሳት ፓርኮች፣ ሐይቆችና የባህር ዳርቻዎችን ጨምሮ ሌሎችም መስህቦች ያሉባቸው ወይም ሳፋሪ የሚባሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች በርካታ ገቢ ሲያስገኙ ቆይተዋል፡፡ በታንዛኒያም እንዲህ ያሉት መዳረሻዎች ተመራጭ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በአንድ በማቀናጀት ጎብኝዎችን የበለጠ መሳብ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ታንዛኒያ ወይም ኬንያ ከሚገኙ አስጎብኚዎች ጋር አጋር ሆነው መሥራት የሚችሉባቸው ዕድሎች አሉ፡፡

      ኢትዮጵያን ሊጎበኝ የሚመጣው ቱሪስት ቢያንስ ስድስት ቀናት ማሳለፍ የሚችልባቸው መስህቦች ስላሉ እዚህ ላይ መሥራቱ ይጠቅማል፡፡ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርጎ ባህር ዳርቻ መዝናናት ቢፈልግ ወደ ኬንያ፣ ታንዛኒያ አልያም ወደ ሲሼልስ እንዲያቀና ማድረግ የሚችልባቸው የትብብር ሥራዎች መፈጠር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ሎጆችና ሪዞርት ሆቴሎች ያስፈልጓታል፡፡ ይህ ሲሆን ለንግድ ወይም ለስብሰባ አልያም ለትራንዚት የመጣው ጎብኚ፣ እግረ መንዱን አስደሳች ቆይታ ማድረግ የሚችልባቸው የመዝናኛ ቦታዎች መስፋፋት አለባቸው፡፡ በጎንደርና በአንዳንድ አካባቢዎች የሎጅና የሪዞርት ሆቴሎች እየተፈጠሩ በመሆኑ ተስፋ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በመጪዎቹ ሦስት ወይም አምስት ዓመታት ውስጥ በቱሪዝም መስኩ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የሚጠበቀው ለውጥ ምንድነው?

ሚስተር ሒውስተን፡- በርካታ የቱሪዝም ተዋናዮች ወደ አፍሪካ እየመጡ ነው፡፡ በርካታ የውጭ ሆቴሎች እየገቡ ነው፡፡ ሒልተንና ራዲሰን ሆቴሎችን ካየህ በመቶ የሚቆጠሩ ሆቴሎች እያስተዳደሩ ነው፡፡ በየሳምንቱ አዳዲስ ሆቴሎች እየተከፈቱ ነው፡፡ ሸራተን፣ ማሪዮት፣ ራማዳ ወይም ዊንድሃም የተሰኙ ሆቴሎች እየተስፋፉ ነው፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች በመጡ ቁጥር፣ ጎብኚዎች ቢሻቸው ከፊንላንድ አልያም ከጀርመን እንደ ልባቸው ለመምጣት የሆቴል ዕጦት ሥጋት አያድርባቸውም፡፡ ወደ አፍሪካ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጉዞ ከእስካሁኑም የበለጠ እየተስፋፋ እንደሚመጣ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም በተመድ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መረጃ መሠረት፣ የአፍሪካ የቱሪዝም ዘርፉ ዕድገትና የጎብኚዎች ቁጥር ከዓለም አቀፉ አማካይ ቁጥር በላይ እያደገ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ወደፊትም የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ እያደገ እንደሚመጣ ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ከሌሎች አገሮች በተለይም ከአጎራባች አገሮች አኳያ ደረጃ አውጡ ቢባሉ እንዴት ይገልጹታል?

ሚስተር ሒውስተን፡- እንደማስበው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ላይ ለመድረስ ረጅም መንገድ መጓዝ ይጠበቅባታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን ታስተናግዳለች፡፡ ኬንያና ታንዛኒያም በርካታ ሚሊዮኖችን እያስተናገዱ ነው፡፡ በቱሪዝም መስክ ኢትዮጵያ የሌላት ነገር ቢኖር ሳፋሪ ነው፡፡ እርግጥ በመስኩ ይህ ከትልልቆቹ አምስቱ የቱሪዝም መስህቦች ‹‹ቢግ ፋይቭ›› ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ ይህ ባይኖራችሁም ሌሎች ትልልቅ መስህቦች አሏችሁ፡፡ በርካታ አስደናቂ መስህቦች አሏችሁ፡፡ ሩዋንዳን ብናይ፣ ወይም በምዕራብ አፍሪካ አገሮች ያለውን ሁኔታ ብንመለከት አሁንም ሳፋሪ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡

      በአትዮጵያ ለቱሪስት መስህብ የሆኑ በርካታ ስጦታዎች አሉ፡፡ ተጓዦች ወይም ቱሪስቶች እነዚህን መስህቦች በሚገባ እንዲጎበኙ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በተገቢው መንገድ የሚንቀሳቀሱ፣ በሚገባ የሚሠለጥኑ፣ ሙያቸውን የሚያከብሩና ጠንቅቀው የሚያውቁ አስጎብኚዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የትራንስፖርት ዘርፉን ደረጃዎች ማሻሻል አለባችሁ፡፡ ደረጃው ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን፣ ቱሪስትም ቢገለገልበት ተገቢነት ሊኖረው የሚችል መደበኛ ትራንስፖርት መኖር አለበት፡፡ ያሉት አውቶቡሶች ደረጃቸው መሻሻል አለበት፡፡ ሌሎቹም ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሆቴሎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ በርካታ ጎብኚዎች በመጡ ቁጥር፣ የበለጠ ጨምረው መምጣት እንዲችሉ የሚያስችሉ አሠራሮችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጪው ዓመት የት ነው የዚህ ተመሳሳይ ዝግጅት መዳረሻው? ዳግም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ወይስ ወደ ኬንያ ያቀናሉ?

ሚስተር ሒውስተን፡- እንደ አስፈላጊነቱ እዚህም ኬንያም አለሁ፡፡ ዋናው ተፈላጊነቱና ተሳታፊዎች ያላቸው ፍላጎት እንጂ ሁለቱም ዘንድ ማካሄድ ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...