መንግሥት የኢኮኖሚ መርህ እንጂ ሉዓላዊነትን የሚጋፋ አካሄድ የለም ብሏል
መንግሥት የኢኮኖሚ ሪፎርም አካል እንደሆነ የገለጸውና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ለማዞር የተያዘው መንገድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል፣ እንዲሁም የፕራይቬታይዜሽኑ አካሄድ እንደ ዓለም ባንክ ባሉ ተቋማት የቀረበ የርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ውጤት ነው በማለት ምሁራን ተቃወሙ፡፡ መንግሥት በበኩሉ ከሉዓላዊነትም ሆነ ከርዕዮተ ዓለም ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ሞግቷል፡፡
የማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ) የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ሐሙስ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠራው የውይይት መድረክ ላይ ከመንግሥት ወገን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ስለፕራይቬታዜሽን እንቅስቃሴ ለማስረዳት ተገኝነው ነበር፡፡ የመንግሥትን የፕራይቬታይዜሽን ሒደት በመቃወም ሐሳባቸውን ያካፈሉት ደግሞ የኢኒሺዬቲቭ አፍሪካ መሥራችና ኃላፊ አቶ ክቡር ገና ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ጠንከር ያሉ የክርክር ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሁለቱ ምሁራን ወገን እየገቡ ድጋፍና ተቃውሞአቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
እንደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪው ማብራሪያ መንግሥት ወደ ግል የሚዛወሩትን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በጥንቃቄ አጥንቶ፣ ዋጋቸውን መዝኖና ተምኖ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያረጋግጥ መንገድ እየተገበረው ይገኛል፡፡ በመሆኑም በአፈጻጸምና በምርት ድክመታቸው፣ በአገሪቱ ላይ ባደረሱት የብድር ጫናና ባስከተሉት ኪሳራ ዳግም እንዲያገግሙ እንኳ ዕድል የማይሰጡ ሆነው የተገኙትን ጨምሮ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ላይ በተከማቸው ከፍተኛ የውጭና የአገር ዕዳ ሳቢያ ራሳቸውን ለማሻሻል የውጭ ብድር ማግኘት ያልቻሉት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉት ድርጅቶች በከፊል፣ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የሚሸጡ የልማት ድርጅቶችን በዋቢነት አስታውሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን 13 የስኳር ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ሌሎችም በሙሉና በከፊል ለሽያጭ የቀረቡ ድርጅቶች ናቸው፡፡
እንደ ብሩክ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ከ13 የስኳር ድርጅቶች በአሁኑ ወቅት የስድስት ፋብሪካዎች የሀብት ዋጋ ትመናና ሌሎችም ጥናቶች እየተገባደዱ ነው፡፡ የወልቃይት፣ የከሰም፣ የበለስና የሌሎች ግንባታቸው እስከ 50 በመቶ የተጠናቀቀ ፕሮጀክቶች ያስከተሉትን ጫናም አጣቅሰዋል፡፡ በፕሮጀክቶቹ አካባቢ የሚኖሩ፣ ቃል ተገብቶላቸው መሬታቸውን ለአገዳ እርሻ አስረክበው የፋብሪካዎቹን ግንባታ እየተጠባበቁ የሚገኙ ዜጎች፣ ለልጆቻቸው ቃል የተገባላቸው የሥራ ዕድልም ሆነ ሥራ ይጀምራሉ የተባሉት ፋብሪካዎች የውኃ ሽታ ሆነው መቆየት ጥያቄ እያጫረባቸው እንደሚገኝ ብሩክ (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም እንዲህ ያሉትን ፕሮጀክቶች መንግሥት ውጤታማ ማድረግ ከፋይናንስ ዕጦትም ሆነ ፕሮጀክቶቹ ከሚጠይቁት ሰፊ የአስተዳደርና ሌሎችም መሠረታዊ ለውጦች አኳያ ወደ ግል ቢዛወሩ እንደሚሻል ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ከፍተኛ አማካሪው፣ ከስድስቱ የስኳር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የኢትዮ ቴሌኮም 49 በመቶ ድርሻ በመጪው መጋቢት ወር ወደ ግል እንደሚዛወርና ሁለት አዳዲስ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የሚደረግበትን የጊዜ ገደብ ይፋ አድርገዋል፡፡ በባቡር ፕሮጀክቶችና በሎጂስቲክስ ዘርፎችም ተመሳሳይ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በግሉ ዘርፍ አገራዊ ሚና ላይ ፅኑ ዕምነት ያላቸው አቶ ክቡር ገና ደግሞ፣ መንግሥት ለሽያጭ ያወጣቸው ድርጅቶች በተለይም ኢትዮ ቴሌኮምን የመሳሰሉ ነባርና ውጤታማ ድርጅቶች የአገሪቱን ሉዓላዊነት ሥጋት ላይ የሚጥሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል በማሳሰብ፣ የመንግሥትን ችኮላና ጥድፊያ በመቃወም ፕራይቬታይዜሽን ብቸኛ አማራጭ መሆን እንደማይገባው ተከራክረዋል፡፡ እንደ አቶ ክቡር ገና ማብራሪያ፣ የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል በሚዛወሩበት ወቅት ሕዝብ ከዚህ ቀደም ያገኛቸው የነበሩ ዕድሎች እንደሚጣበቡ፣ አንዳንዶቹ ለሕዝብ ክፍት የነበሩ ወደ ግል ሲዛወሩ ግን ይህንን ነፃነት የሚያሳጡ፣ የግል ድርጅቶች በተለይም የውጭዎቹ ትርፍ ተኮር ከመሆናቸው የተነሳ የሀብት አወቃቀርና የአሠላለፍ ለውጥ በማድረግ፣ ከሕዝባዊነት ወደ ጥቂቶች ሀብትነት የሚቀየሩ በመሆናቸው መንግሥት ሒደቱን ማጤን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
አቶ ክቡር ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት ፕራይቬታይዜሽን በአራት መንገዶች ይፈጸማል፡፡ መንግሥት የቀደመ ይዞታውን ወይም የሞኖፖል ሚናውን መተው ሲፈልግ የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍበትን መንገድ ነው በቀዳሚነት ያስረዱት፡፡ መንግሥት በትምህርት መስክ የነበረውን ብቸኛ ሚና ለግሉ ክፍት በማድረግ የወሰደውን ዕርምጃ ጠቅሰዋል፡፡ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር መንግሥት አሁን የመረጠውና እንግሊዝም ከ40 ዓመታት በፊት የተገበረችው፣ ነገር ግን ውጤቱ የባሰ ቀውስ አስከትሎ ያለፈ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ሌላው አማራጭ የመንግሥት ድርጅቶችን በኮንትራት ማኔጅመንት ለግል ድርጅቶች መስጠት ሲሆን፣ የመንግሥትና የሕዝብ ባለቤትነትን ሳያስነካ ማካሄድ እንደሚቻል ሒልተን ሆቴልን በምሳሌ አንስተው፣ ሙሉ በሙሉ ባለቤትነት ወደ ግል የሚዛወርበትን የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ድርጅትን ሽያጭ ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ያሉ አማራጮች ቢኖሩም፣ መንግሥት ግን ትኩረቱ የሕዝብ ንብረት የሆኑትን ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ንብረትነት ማዛወሩ ላይ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ተችተዋል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተልዕኮና ውጤታማነት በትርፍ ቢለካ እንኳ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም ይጠቀሳሉ ያሉት አቶ ክቡር፣ የልማት ድርጅቶች ከብሔራዊ ጥቅም እንጂ ከርዕዮተ ዓለም ጋር መያያዝ እንደሌለባቸው በማሳሰብ፣ የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ድርጅቶች የሚያደርጉት ጫና ነው በማለት ኮንነዋል፡፡ መንግሥት ድርጅቶቹን ወደ ግል ሲያዛውር አብሮ ሉዓላዊነቱን ያጣል ያሉት አቶ ክቡር፣ ለዚህም የሚሻሻሉ ሕጎችና ደንቦችን አውስተዋል፡፡
የዓለም ባንክና መሰሎቹ የሚያቀርቡትን ውትወታና የርዕዮተ ዓለም ጫና በመቃወም በራሳቸው መንገድ ውጤታማ ሆነዋል በማለት ቻይናውያንን ሲጠቅሱ፣ የእነዚህን ተቋማት ምክረ ሐሳብ በመቀበል 11‚000 የመንግሥት ድርጅቶችን የሸጡት ሩሲያውያን ግን ከነበሩበት ወርደው ችግር እንደገጠማቸው አመላክተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ድርጅቶቹን ለመሸጥ ምን መብት አለው? ሽያጩ አንዴ ከተሸጡ የማይገኙ ድርጅቶችን የሚያሳጣን ነው፡፡ የውጭ ዕዳ ለመክፈል ይሸጡ ማለት ቀልድ ነው፤›› በማለት መንግሥትን ተከራክረዋል፡፡
መንግሥት ከአገር ውስጥ የተበደረውን ገንዘብ በራሱ መንገድ ማወራረድ ይችላል የሚል ሐሳብ ያንፀባረቁት አቶ ክቡር፣ ‹‹አንበሳ ምን ይበላል ቢሉ ተበድሮ፣ ምን ይከፍላል ቢሉ ማን ጠይቆ?›› የሚለውን ብሒል በማውሳት የመንግሥት ተቋማት ከመንግሥት ተቋማት መበደራቸው እንደ ችግር ሊነሳ እንደማይገባው ይልቁንም መሰረዝ የሚችልባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን የኢትዮጵያን ችግር ብቻውን ይፈታዋል ወይ ሲሉ የጠየቁት አቶ ክቡር፣ መንግሥት ሌሎች አማራጮችን ማየት ይገባዋል በማለት ሞግተዋል፡፡ ‹‹በእውነት ስለኢትዮጵያ የምናስብ ከሆነ ይኼ አካሄድ አይጠቅመንም፡፡ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ተታለናል፡፡ የራሳችንን ሐሳብና አካሄድ እንከተል፤›› ብለዋል፡፡ ከፕራይቬታዜሽን ባሻገር የተሞከሩ ዕርምጃዎች ስለመኖራቸው እንዲገለጽላቸው የጠየቁት አቶ ክቡር፣ የፖሊሲ አማራጮች ካሉ ይነገር ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ካፒታል ያፈራችው በራሷ ነው፡፡ ብድር አለብን፡፡ ብድር ለመክፈል ግን ትልልቅ ድርጅቶችን መሸጥ አይጠበቅብንም፤›› ሲሉ በፕራይቬታይዜሽን ላይ ያላቸውን የልዩነት አቋም አጠናክረዋል፡፡
ብሩክ (ዶ/ር) መንግሥትን ብድር ማን ክፈል ብሎ ይጠይቀዋል ለሚለው የአቶ ክቡር ምሳሌ የመልስ ምት የሰጡት በምሳሌያዊ ንግግር አጅበው ነበር፡፡ ‹‹ወይ መሬት ያለ ሰው?›› ያሉት ከፍተኛ አማካሪው፣ አገር ከገባችባቸው ግዴታዎች አኳያ የብድር ጉዳዮች ያመጡት ጣጣ በርካታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማንም የዓለም ባንክንም ሆነ የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ባንዲራ አያውለበልብም፡፡ የ‹ፕራግማቲዝም› ጉዳይ ነው፤›› በማለት ለአቶ ክቡር ሙግት አጸፋ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም የአገር ህልውና በኢትዮ ቴሌኮም መሸጥ አለመሸጥ እንደማይወሰን፣ የሉዓላዊነት ጥያቄ የተወሰነው በዓድዋ ድል እንጂ በልማት ድርጅት ሽያጭ አይደለም ብለዋል፡፡
መንግሥት የኢኮኖሚ መርህ ላይ የተመሠረተ አካሄድ እንደሚከተል፣ የግሉ ዘርፍ የሚመራው ኢኮኖሚ ይፈጠር ከተባለም የውጭውም ሆነ የአገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን መግባት እንዳለባቸው ያብራሩት ብሩክ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ለውጭ ብቻ ብሎ የዘጋው አካሄድ እንደሌለና ይልቁንም ለሁሉም ክፍት ማድረጉን፣ እንዲያውም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንና ድርጅቶችን እንደሚያበረታታ አብራርተዋል፡፡
አቶ ክቡር ከብሩክ (ዶ/ር) ጋር ያደረጉት የሁለት ጎራ ሙግት፣ በተሳታፊዎች ዘንድም ተጋብቶ ገሚሱ ክቡር ገናን ሲደግፉ የተቀሩት ደግሞ ብሩክ (ዶ/ር) ያቀረቡትን የመንግሥትን ሐሳብ ደግፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ን በመወከል፣ እንዲሁም የፕራይቬታይዜሽን አማካሪ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ መንግሥት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ድርጅቶችን ለሽያጭ ማቅረቡ ከሉዓላዊነት ሥጋት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም በማለት የግላቸውን ሐሳብ ያንፀባረቁ ሲሆን፣ እንዲያውም ‹‹ሰኞ ይሸጥ ቢባል ቀድሞ መሸጥ ያለበት ኢትዮ ቴሌኮም ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአንፃሩ የቴሌኮም አገልግሎት እንደ አዲስ በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሲዋቀር ጀምሮ በቦርድ ማገልገላቸውን፣ ኋላም በስዊዘርላንድና በተለያዩ አገሮች ማገልገላቸውን በማስታወስ አስተያየት የሰጡት አቶ ተረፈ የራስ ወርቅ ናቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ የአቶ ክቡርን ሐሳብ እንደሚደግፉ፣ ቴሌኮም የርዕዮተ ዓለምም ሆነ የፍልስፍና ጉዳይ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም የፈረንሣይ ቴሌኮም 80 በመቶ በመንግሥት ባለቤትነት እንደሚተዳደርና የተቀረውም ድርሻ በስቶክ ገበያ እንደሚወሰን አብራርተዋል፡፡ የሲንጋፖር ቴሌኮም ዘርፍ መቶ በመቶ በመንግሥት ባለቤትነት እንደሚተዳደርም አስታውሰዋል፡፡
ይሁንና ኢትዮ ቴሌኮም ብቸኛ ከመሆን ይልቅ ተወዳዳሪ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፣ ድርሻውን ከመሸጥ ይልቅ ፈቃድ ገዝተው እየገቡ የሚሠሩ የቴሌኮም አገልግሎት ድርጅቶችን አማራጭ ማድረጉ እንደሚበጅ አሳስበዋል፡፡
እንዲህ ያሉ የግራና ቀኝ ሐሳቦች የተስተናገዱበት የማኅበራዊ ጥናት መድረክ፣ በፕራይቬታዜሽን ላይ እስካሁን ከተደመጡ ሕዝባዊ ክርክሮች ጉልህ የሥጋት ድምፆች የተስተጋቡበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ መንግሥትም እንዲህ ያሉ ተቃርኖዎች በመነሳታቸው ዳግመኛ ሊያጤናቸው የሚያስገድዱ ሐሳቦች እንዳሉ አመላካች ነው ያሉም አሉ፡፡