Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መድን ኩባንያዎች ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ አሰባሰቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሕወይት መድን ላይ የተጣለው ታክስ እንዲነሳ ተጠይቋል

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2011 ዓ.ም. ከ9.1 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን አሰባሰቡ፡፡ ይህ አኃዝ 17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጠቅላላው ያሰባሰቡትን ዓረቦን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከ9.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበው ዓረቦን 8.6 ቢሊዮን ብር በማስመዝገብ ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡

የመድን ኩባንያዎቹ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ 516.4 ሚሊዮን ብር ዓረቦን እንዳሰባሰቡ መረጃው አመላክቷል፡፡

ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን በ5.6 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ከ2010 ዓ.ም. አኳያ የ456.2 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማስመዝገቡ ታይቷል፡፡ በአንፃሩ የሕይወት ነክ ኢንሹራንስ ዘርፉ በ2011 ዓ.ም. የ19.3 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ሒሳብ ዓመቱን ሸኝቷል፡፡

ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ከተሰበሰበው 8.6 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ውስጥ 38.4 በመቶውን መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻውን ሲይዝ፣ 16ቱ የግል ኩባንያዎች 61.6 በመቶውን የገበያ ድርሻ ተጋርተዋል፡፡

ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ በ2011 ዓ.ም. ከፍተኛውን ዓረቦን በማሰባሰብ በቀዳሚነት የተቀመጠው የግል ኩባንያ አዋሽ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ ከዚህ ዘርፍ 691.3 ሚሊዮን ብር ዓረቦን አሰባስቧል፡፡ ይህ ገቢም በኢንዱስትሪው ያለውን የገበያ ድርሻ ከግል ኩባንያዎች አኳያ ሲታይ በቀዳሚነት እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ይዞ የነበረው ኒያላ ኢንሹራንስ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከጠቅላላው የኢንሹራንስ ሽፋን ባሻገር የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋንን በተመለከተ በ2011 ዓ.ም. የተሻለ አፈጻጸም ስለመመዝገቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ቢገልጹም ምጣኔው ግን አነስተኛ  ሆኖ ይታያል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ 17 ኩባንያዎች፣ አሥሩ ብቻ ሕይወት ነክ የኢንሹራንስ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ቀሪዎቹ ሕይወት ነክ ባልሆነ የኢንሹራንስ አገልግሎት ዘርፍ ላይ በማተኮር ይንቀሳቀሳሉ፡፡

ከኩንያዎቹ ሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፣ አሥሩ ኩባንያዎች ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰቡት ዓረቦን ከ2010 ዓ.ም. አኳያ ሲታይ፣ በ83 ሚሊዮን ብር ወይም በ19.3 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡  

ከሕይወት ኢንሹራንስ የተሰባሰበው ዓረቦን፣ ሕይወት ነክ ካልሆነው መድን ዘርፍ ከተገኘው በእጅጉ ያነሰ ሲሆን፣ ሕይወትና ሕይወት ነክ ካልሆነው መድን ዘርፍ በድምሩ ከተሰበሰበው 9.1 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ፣ የኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላካች ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን በ2011 ዓ.ም. ከሕይወት ዘርፍ የተገኘው ዓረቦን መጠን ከ19 በመቶ በላይ አድጓል ቢባልም፣ ከጠቅላላው የአገሪቱ የመድን ሽፋን አንፃር ሲታይ ግን ድርሻው አሁንም ከሰባት በመቶ በታች ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ ገጽታ አገሪቱን የተለየ የሚያደርጋት ሆኖ መዝለቁ ይጠቀሳል፡፡

ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው መረጃ አንፃር የሕይወት ኢንሹራንስ ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ መያዙ ነው፡፡ የየአገሩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚሰበስቡት ዓመታዊ ዓረቦን ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ከሕይወት ኢንሹራንስ የሚሰባሰብ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ግን አሁንም ከአምስትና በስድስት በመቶ መዝለል ሳይችል ዓመታትን ዘልቋል፡፡

ከዓለም አቀፍ የኢንሹራንስ ሽፋን አንፃር የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በኢትዮጵያ እንዲህ የመሆኑ ጉዳይ ለምን? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሲሆን፣ የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ ጉዳዩ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ተገቢ የሆነ ሥራ ባለመሥራቱ ነው ይላሉ፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ የተመለከቱና ሊያበረታቱ የሚችሉ አሠራሮች ያለመኖራቸው፣ እንዲሁም የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ገበያ ለማስገባት ውስንነት የሚታይባቸው በመሆኑም ነው ይላሉ፡፡

የሕይወት ኢንሹራንስ ለማሳደግ የሚያስችል ፖሊሲ የለም የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹አሁንም ቢሆን ለሕይወት ዘርፍ ትኩረት የተነፈገው መሆኑንም ያክላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በኩል ቢሆን እሱን ለማበረታታት የሚስችሉ ሥራዎች ስለማይታዩ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ዕድገት ተገድቧል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አሁንም ቢሆን በሕይወት ኢንሹራንስ ተመዘገበ የተባለው ውጤት አዲስ ነገር ተሠርቶ አይደለም የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ ቀደም ብለው የተሸጡ ፖሊሲዎች እንጂ አዳዲስ ውሎች ተሽጠው ያመጡት ውጤት እንዳልሆነም ያምናሉ፡፡ ‹‹በዓመቱ የመጣው አዲስ ውል ጥቂት ነው፡፡ ድሮ የነበሩ ውሎች ናቸው፤›› በማለት በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያለውን ክፍተት አመላክተዋል፡፡  

በመሆኑም ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ ብሔራዊ ባንክም ሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተባብረው መሥራት እንደሚኖርባቸው የጠቆሙት አቶ ፍቅሩ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የተሻለ አገልግሎት ይዘው መምጣት እንደሚኖርባቸው ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያለው ገበያ ያልተነካና ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባ፣ መንግሥት የታክስ ማበረታቻ መስጠት እንደሚጠበቅበት አውስተዋል፡፡

የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ጅምር ላይ በመሆኑ የሁሉም አካላት ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ የሕይወት ኢንሹንስ ዘርፍ ኩባንያዎቹን የማያጓጓበት አንዱ ምክንያት፣ የሚገዛው አገልግሎት ለዋጋ ንረት የተጋለጠ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ‹‹የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ [ገንዘብህን] ከምታስቀምጥ ባንክ ሄደህ በጊዜ ገደብ ወይም በረጅም ጊዜ ቁጠባ ሒሳብ ብታስቀምጠው ይሻላል፤›› በማለት የሕይወት መድን ያሉበትን ፈታኝ ሁኔታዎች እኚሁ ባለሙያ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የሕይወት ኢንሹራንስ እንዲስፋፋ የሚያግዝ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ በሌላው ዓለም እንደሚደረገውም በሕይወት ኢንሹራንስ ላይ የተጣለውን ታክስ ቢያነሳም ዘርፉን እንደሚያግዘው ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሊሠሯቸው የሚገቡ እንደ ጡረታና የጤና መድን ሥራዎች ከመንግሥት እጅ መውጣት እንዳለባቸው ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡ ዘርፉን ለመጠቀም ከመንግሥትም ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችም የሚጠበቁ በርካታ ሥራዎች እንደሚኖሩም ተጠቅሷል፡፡   

በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከተሰበሰበው 516.4 ሚሊዮን ብር ውስጥ 134.9 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባሻገር፣ ቀሪዎቹ ዘጠኝ ኩባንያዎች በጥቅል ከሕይወት ኢንሹራንስ የሰበሰቡት ዓረቦን 38.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ የግል ኩባንያዎች ካሰባሰቡት ገቢ አሁንም በቀዳሚነት የተቀመጠው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም. ከዚህ ዘርፍ ማሰባሰብ የቻለው 107 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም በግል የኢንሹራንስ ኩባንያ ደረጃ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን በማሰባሰብ ተጠቃሽ አድርጎታል፡፡ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ከአዋሽ ቀጥሎ ከፍተኛውን ዓረቦን ማሰባሰብ የቻለው ኒያላ ኢንሹራንስ ነው፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በዓመት ውስጥ ከሕይወት ኢንሹራንስ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 74.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ በዚህ ዘርፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያሳው ዕድገት በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በኢንዱስትሪ ከፍተኛ የተባለው ዓረቦን መሰብሰብ አስችሎታል፡፡

ኩባንያው በ2010 የሒሳብ ዓመት ከሕይወት የኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 69.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን 54 በመቶ ዕድገት በማሳየት 107 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ማሰባሰቡ መቻሉም በዘርፉ ለዓመታት ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ይዞ ከቆየው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋርም እየተቀራረበ መምጣቱን ያሳየ ሆኗል፡፡

ዓመታዊ የዕድገት መጠኑ ደግሞ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት መብለጥ የቻለበት ዓመት ሆኗል፡፡ ኩባንያው በ2011 ዓ.ም. በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያስመዘገበው ዕድገት ከሌሎቹ ስምንት የግል ኩባንያዎች አንፃር ብቻ ሳይሆን ከመንግሥታዊውም የኢንሹራንስ ኩባንያ ብልጫ ያለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከሕይወት ኢንሹራንስ 134.9 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ በኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሆነ ዓረቦን ቢሰባስብም ከቀዳሚው ዓመት ያደገው በ16 በመቶ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛውን ዕድገትና ያስመዘገበው ሌላው የኢንሹራንስ ኩባንያ ዓባይ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ አምና ስድስት ሚሊዮን ብር የነበረውን የዓረቦን መጠን 50 በመቶ በማሳደግ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ሲያደርስ፣ ኢትዮ ላይፍ ደግሞ በሕይወት ኢንሹራንስ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምውን የ40.9 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሆኗል፡፡

እንደመረጃው በዚህ ዘርፍ ከአፍሪካ ኢንሹራንስና ንብ ኢንሹራንስ ቅናሽ ያሳየበት ዓመት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ አሥር ኩባንያዎች ከሕይወት ኢንሹራንስ ያሰባሰቡት የዓረቦንን መጠን 516.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ 26.1 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ድርሻ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሲይዝ አዋሽ ኢንሹራንስ ደግሞ 20.7 በመቶ ድርሻ በመያዝ ተከታዩን ሥፍራ ይዟል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ ደግሞ 14.4 በመቶ የገበያ ድርሻ ይዟል፡፡ ሰባቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ከ1.6 እስከ 8.7 በመቶ የገበያ ድርሻ እንደያዙ ተመልክቷል፡፡  

በ2011 የሒሳብ ዓመት አራት የግል ኩባንያዎች ዓመታዊ የዓረቦን መጠናቸው ከቀዳሚ ዓመት ያነሰ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት በኢንዱስትሪ ትልቁን ድርሻ ይዞ የቆየው ኒያላ ኢንሹራንስም በተለይ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው ዓረቦን መጠን ከሌላው ጊዜ በተለየ ቅናሽ የታየበት ሆኗል፡፡

በጥቅሉ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከባንክ በተለየ ዝቅተኛ አፈጻጸም እየታየበት ለዘርፉ ተገቢ የሆነ ትኩረት ያለመስጠት ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ በተለይ በሌላው ዓለም የተለመዱ የኢንሹራንስ አሠራሮችም እዚህ እንዲተገበሩ አሁን ያለውን የኢንሹራንስ ፖሊሲ መከለስ የሚያስፈልግ መሆኑን ነው፡፡   

በአሁኑ ወቅት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደ ባንክ ያለመስፋታቸው አንዱ ችግር ይኼው የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ሳቢ እንዲሆን ካለመሠራቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነም የባለሙያው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ በአንፃሩ ግን አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም እንደ ባንክ ብዙ ካፒታል የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በኢንሹራንስ ዘርፍ ለመግባት ኢንቨስተሮች እየተሳቡ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አሁን ያሉት ኩባንያዎች አዲስ ገበያ ከመፍጠር ይልቅ መነጣጠቅ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አምና አንዱ ጋር የነበረ ደንበኛ ዘንድሮ ሌላው ጋር ዋጋ ቀንሶ ይወስደዋል እንጂ አዲስ ገበያ ያለመፈጠሩ ነገርም ኢንዱስትሪው በተፈገለው ደረጃ እንዳይራመድ አድርጎታል፡፡

አዲስ ገበያ የመፍጠር ሥራ ላይ ክፍተት መኖሩን የጠቆሙት አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹ነገር ግን ቢዝነሱ ገና አልተነካም፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች