Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኪነ ጥበብ መስክ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ለመስጠት ታቀደ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኪነ ጥበብ አካዴሚ ሊገነባ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ከተዋቀሩ ቢሮዎች አንዱ የሆነውና ለኪነ ጥበብ ልዩ ትኩረት የሰጠው፣ የከተማው የባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በአዲስ አደረጃጀት የኪነ ጥበብ ዘርፉን በማዋቀር በዘርፉ የሚካሄዱ የትልልቅ ስቱዲዮዎች ግንባታና መሰል ኢንቨስትመንቶችን የሚደግፉ ማበረታቻዎች ለመስጠት መታቀዱን አስታወቀ፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቢሮው ኃላፊ ፕሮፌሰር ነብዩ ባዩና የቢሮው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት፣ ማክሰኞ መስከረም 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ እንደ አዲስ የተዋቀረው ቢሮው በቱሪዝም፣ በባህልና በኪነ ጥበብ መስኮች በሦስት ዳይሬክቶሬት ደረጃ በማዕከል ሲደራጅ በተለይም በኪነ ጥበብ መስኩ ከ900 በላይ ሠራተኞችን የሚያንቀሳቅስ አዲስ አደረጃጀት በመፍጠር በአዋጅ ራሱን ችሎ መዋቀሩን አብራርተዋል፡፡

አቶ ሰርፀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኪነ ጥበብ ዘርፉ ለመነሻው በ69 ሚሊዮን ብር መበደኛ በጀት ሥራ ሲጀምር ወደፊትም በርካታ የካፒታል በጀት የሚጠይቁ ሥራዎች ያሉበት በመሆኑ በጀቱ ከተጠቀሰውም በላይ ይጨምራል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለኪነ ጥበብ ዘርፉ ከእስካሁኑ የተለየ አትኩሮት መስጠቱን፣ በንግድ ዙሪያ ብቻ ታጥሮ የቆየው የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ጉልህ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ለሚሠማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦችም የማበረታቻ ድጋፎች መስጠት የሚችልበት መዋቅር እንደዘረጋ አቶ ሰርፀ አብራርተው፣ ትልልቅ የፊልምና የሌሎች ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ቀረፃ ማካሄጃ ግንባታዎችን ለማካሄድ ፍላጎት ያላቸው አካላት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በ2011 ዓ.ም. በኪነ ጥበብ ዘርፍ ሲከናወኑ ስለቆዩት ሥራዎች መግለጫ የሰጡት ሁለቱ ኃላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ዘርፉ ለቱሪዝምና ለባህል ዘርፉ መጋቢ ቢሆንም፣ ይህንን አስተዋጽኦውን በሚመጥን ደረጃ ሳይደራጅ መቆየቱ እንዲቀር መደረጉን፣ በመሆኑም ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮም ራሱን የቻለ ተጠሪ አካል ተደራጅቶለት ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ታች ወረዳ ድረስ መዋቅር እንደተዘረጋለት ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባሻገር በከተማ አስተዳደሩ ይዞታ ሥር የሚገኙት አራት ቴያትር ቤቶች ላይ ማለትም፣ የብሔራዊ ቴያትር፣ የራስ ቴያትር፣ የአገር ፍቅር ቴያትር እንዲሁም የሕፃናትና ወጣቶች ቴያትር ቤቶችን ይዞታ የማሻሻል፣ ራሳቸውን ችለው በተቋም ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ፣ የማስፋፊያና የዕድሳት ሥራዎች በቴያትር ቤቶቹ ላይ እየተካሄደ እንደሚገኝ አቶ ሰርፀ ገልጸዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት ፈርሶ ዳግም ሳይገነባ የቆየው የራስ ቴያትር ቤት፣ ከነበረበት መርካቶ አካባቢ ተነስቶ አሜሪካ ግቢ በተባለው አካባቢ በ4‚500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሕንፃ ግንባታውን ማካሄድ የሚቻልበት ቦታ ከከተማው አስተዳደር እንደተሰጠውና በአሁኑ ወቅትም የዲዛይን ማሻሻል ሥራው እየተካሄደ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ነብዩ አስታውቀዋል፡፡ የአገር ፍቅር ቴያትር ቤትም ማስፋፊያ ለማካሄድ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችን በአግባቡ በሚነሱበት ሁኔታ ላይ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ፣ ግንባታው የተጓተተው የሕፃናትና ወጣቶች ቴያትር አዲስ ሕንፃ ግንባታም እንደ አዲስ ስለመጀመሩ፣ በ800 ሚሊዮን ብር የአዲስ አበባ ቴያትርና ባህል አዳራሽን የማሻሻልና ግንባታ የማካሄድ ሥራዎችም መካሄድ እንደሚጀምሩ ተብራርቷል፡፡

እንዲህ ያሉትን ጨምሮ የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ የባህል፣ የቱሪዝምና የኪነ ጥበብ ሥራዎች በዚህ ዓመትም እንደሚካሄዱ ሲገለጽ፣ በተለይም በባህል መስክ በተመድ የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን በዚህ ዓመት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል፣ የኢሬቻ በዓል እንዲሁም የፊቼ ጨምበላላ በዓል በከተማው አስተዳደር ድጋፍና ዕገዛ ጭምር እንደሚከበሩ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ቀደምም የቡሄ ወይም የደብረ ታቦር፣ የአሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላትን ጨምሮ ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ.ም. የተከበረው ብሔራዊ የኩራት ቀንን አብሮ በማዘጋጀት መሳተፉን የቢሮው ኃላፊዎች ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኪነ ጥበብ ዘርፉ የምርምርና የፖሊሲ ሥራዎች ብሎም ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ጆርናሎችና ምሁራዊ መስተጋብሮች የሚከናወኑበት የኪነ ጥበብ አካዴሚ ግንባታ ሊካሄድ መታቀዱንም አቶ ሰርፀ አስታውቀዋል፡፡ ስለአካዴሚው ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት እንደሚብራራ ሲገለጽ፣ የዓድዋ ፕሮጀክት ትግበራም በዚህ ዓመት ትኩረት ከሚደረግባቸው ሥራዎች ውስጥ ተካቷል፡፡ ይህ ሁሉ ተቀናጅቶ ሲተገበር አዲስ አበባ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች ዘንድ በሰፊው የምትጎበኝ ተመራጭ ከተማ እንደሚያደርጓት ኃላፊዎቹ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች