Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ህዳሴ ግድብኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የውኃ አሞላል አስመልክቶ ግብፅ ያቀረበችውን ፕሮፖዛል እንደማትቀበለውና እንደማትደራደርበት አስታወቀች

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የውኃ አሞላል አስመልክቶ ግብፅ ያቀረበችውን ፕሮፖዛል እንደማትቀበለውና እንደማትደራደርበት አስታወቀች

ቀን:

ፕሮፖዛሉ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን የመጠቀም መብት የሚያሳጡ ቅድመ ሁኔታዎችን አካቷል ተብሏል

ኢትዮጵያ ግድቡ ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲሞላ ሐሳብ አቅርባለች

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልን በተመለከተ በግብፅ መንግሥት በኩል የቀረበው ፕሮፖዛል የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የሚያሳጡ ቅድመ ሁኔታዎች የተካተቱበት በመሆኑ፣ ፈፅሞ እንደማትቀበለውና በአጀንዳነትም እንደማትወያይበት በማሳወቋ ድርድሩ ለሌላ ጊዜ ተላለፈ፡፡

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልን በተመለከተ ለመምከር እሑድ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በግብፅ ከተማ ካይሮ ተገናኝተው ለሁለት ቀናት ያደረጉት ውይይት ያለ መግባባት የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ውይይቱን በባለሙያዎች ደረጃ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሱዳን ለመቀጠል ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የመሩት የልዑካን ቡድን አባልና የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን ሰባሳቢ ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በግብፅ በተካሄደው ድርድር ላይ የውይይት አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የግድቡን የውኃ አሞላል በተመለከተ ግብፅ ያቀረበችው ፕሮፖዛል ነበር፡፡

ከዚህ ውይይት ቀደም ባሉት ሳምንታት የግብፅ የውኃ ሀብት ሚኒስትር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ ግብፅ ያዘጋጀችውን ፕሮፖዛል ለኢትዮጵያ አቻቸው አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት ጌድዮን (ኢንጂነር)፣ የሰነዱ ይዘት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳና የግብፅን ፍላጎት ብቻ ለማስጠበቅ የተቀረፀ ሆኖ በመገኘቱ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ለግብፅ ግልጽ ተደርጎ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ሰሞኑን በግብፅ በተካሄደው ድርድር ላይ ይኸው ሰነድ በአጀንዳነት ሲቀርብ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ሰነድ የማትቀበለውና እንደማትወያይበት ግልጽ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በግብፅ በኩል ከቀረበው ሰነድ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያሳጣ ሆኖ የተገኘው ይዘት፣ “የግድቡ የውኃ ሙሌት ሒደት ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ተፈጥሯዊ የውኃ መጠን በማይቀንስ መንገድ ይሆናል፤” የሚለው የኢትዮጵያን በውኃ ሀብቷ የመጠቀም መብት የማያከብር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጌድዮን (ኢንጂነር) እንዳብራሩት ይህንን ይዘት መቀበል ማለት፣ የህዳሴ ግድቡን ለመሙላት በዓባይ ገባር ወንዞች ላይም ኢትዮጵያ ልማቶችን ማካሄድ አትችልም እንደ ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በዓባይ ገባር ወንዞች ላይ የሚካሄድ ልማትም ሆነ የህዳሴ ግድቡ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ተፈጥሯዊ የውኃ መጠን ሊያስጠበቅ የማይችል መሆኑ ለማንም ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ በግብፅ በኩል እንዲህ ያለ ፕሮፖዛል መቅረቡ ግብፅ የራሷን ጥቅም ብቻ ለማረጋገጥ ያዘጋጀችው ስለመሆኑ ያስረዳል ብለዋል፡፡

 በሌላ በኩል የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት በዝቅተኛ የአየር ንብረት ወቅት የግብፅን የአስዋን ግድብ ውኃ ከተወሰነ መጠን በላይ መቀነስ የለበትም የሚል ቅድመ ሁኔታ በግብፅ ፕሮፖዛል ላይ መካተቱ፣ ሌላው የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት በሌላ አገር ጥቅም አለመጓደል ላይ የተንጠለጠለ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላልን አስመልክቶ በግብፅ በኩል የቀረበው ሰነድ የሦስቱ አገሮች መሪዎች እ.ኤ.አ. በ2015 በሱዳን የተፈራረሙትን የትብብር መግለጫ ስምምነት (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕል) የሚጥስ እንደሆነ፣ ጌድዮን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ሰሞኑን በግብፅ በተገናኙበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ግብፅ ባቀረበችው ሰነድ ላይ ለውይይት እንደማትቀመጥ ከእነ ዝርዝር ምክንያቱ ተገልጾ አቋም መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ የሰሞኑ ስብሰባ ላይም በቅርቡ የተሾሙት የሱዳን የውኃ ሀብት ሚኒስትር እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኢትዮጵያን አቋም ደግፈው መቅረባቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ውኃ ሙሌትን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን አቋም ሲያስረዱም፣ “ግድቡን ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መሙላት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ማለትም ግብፅና ሱዳንን ከግምት በማስገባት፣ ግድቡ ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መሙላት እንደሚቻል ዝርዝር ሳይንሳዊ ማጣቀሻዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ፕሮፖዛል ለሁለቱም አገሮች እንዲቀርብ ተደርጓል፤” ብለዋል፡፡

ሰሞኑን በተካሄደው የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ መግባባት ላይ ባለመደረሱ፣ የሦስቱም አገሮች የባለሙያዎች ቡድን በአጠቃላይ 15 ባለሙያዎች እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 30 እስከ ኦክቶበር 3 ቀን ድረስ በሱዳን ተገናኝተው የግድቡን ውኃ አሞላል አስመልክቶ ሦስቱም አገሮች ባቀረቡዋቸው ፕሮፖዛሎች ላይ ተወያይተው የሚደርሱበትን ውሳኔ፣ ለሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ቀርቦ ውይይት እንዲካሄድበት መግባባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ስብሰባው በዚህ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ የግብፅ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ድርድሩን እንዳደናቀፈች አድርገው ለመሳል ወደ ሚዲያዎች የመሮጥ የተለመደ ተግባራቸውን የፈጸሙ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በግብፅ የቀረበውን ፕሮፖዛል ግን በግልጽ ያልተናገሩት መልሶ ራሳቸውን የሚጎዳ እንደሚሆን ስለሚረዱት እንደሆነ፣ ከዚህ ተግባራቸው መቆጠብ ባለመቻላቸው በኢትዮጵያ በኩል እውነታውን በመግለጽ ይህንን የግብፆችን የሚዲያ አጠቃቀም ማጨናገፍ እንደሚገባ እንደሚያምኑ ጌድዮን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...