Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሮድካስት ባለሥልጣን የኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበርን ማስታወቂያ አገደ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አክሲዮን ማኅበሩ ዕገዳውን ተቃውሟል

በምሥረታ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር፣ መንግሥት ለሽያጭ ካቀረባቸው 13 የስኳር ፋብሪካዎች ሁለቱን ለመግዛት የአክሲዮን ሽያጭ እያካሄደና ለዚህም ማስታወቂያ እያስነገረ ቢቆይም፣ ይህ ድርጊት ‹‹ብዥታ›› ፈጥሯል በማለት በመገናኛ ብዙኃን ሲተላለፍ የሰነበተው የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያ ለጊዜው እስኪጣራ እንዳይሠራጭ የሚጠይቅ ደብዳቤ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አወጣ፡፡ ይሁንና ችግሩ በውይይት መፈታቱ ታውቋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አባልና የሚዲያ ጉዳዮች አማካሪ አቶ እሸቱ ገለቱ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፣ ለጊዜው ተብሎ የወጣው የማስታወቂያ ሥርጭት ክልከላ እስኪጣራ የሚል ምክንያት የተሰጠው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለብሮድካስት ባለሥልጣን በላከው ደብዳቤ መነሻ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን እንዲዳረስ በማለት የጻፈው ደብዳቤ መነሻው ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር የሚያካሂደው የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያ፣ ‹‹በመንግሥት ወይም በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት እየተካሄደ ይሆናል በሚል እሳቤ ከአገር ውስጥና ከውጭ ስልክ የሚደውሉ፣ እንዲሁም በአካል የሚመጡ መረጃ ፈላጊዎች›› በመበራከታቸው ሳቢያ የተፈጠረበትን ጫና መነሻ በማድረግ የጻፈው ደብዳቤ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ይህንን ምክንያት ያስታከከው ስኳር ኮርፖሬሽን፣ በምሥረታ ላይ የሚገኘው አክሲዮን ማኅበር ‹‹ከስኳር ኮርፖሬሽን ድረ ገጽ ያገኛቸውን ተንቀሳቃሽ ምሥሎችና የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ መለያ የሆነውን የዝሆን ምልክት በሚያሠራጫቸው የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያዎች መጠቀሙ፣ ኅብረተሰቡን ለብዥታ ሳያጋልጠው እንዳልቀረ ይታመናል፤›› ከማለቱም ባሻገር፣ የወንጂ ሸዋና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችንም ሆነ ሌሎቹን ፋብሪካዎች ወደ ግል ለማዛወር ከየትኛውም ባለሀብት፣ ኩባንያ ወይም ማኅበር ጋር የተደረገ ይፋዊ ድርድርም ሆነ ስምምነት እንደሌለው እንዲታወቅለት ጠይቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የአክሲዮን ሽያጭ በግል አክሲዮን ማኅበር አማካይነት እየተከናወነ እንደሚገኝ መግለጽ ሲችል፣ ሕጋዊ ሰውነት ያለውን የአክሲዮን ኩባንያም በግንባር ማነጋገርና ‹‹ብዥታውን›› ማጥራት ሲችል፣ በግልባጭ ቅሬታ ላቀረበበት ኩባንያ አለማስታወቁ ግራ እንደሚያጋባ አቶ እሸቱ ገልጸዋል፡፡ የተሠራላቸው ማስታወቂያ በጊዜያዊነት የማስቆም ጥያቄም ከረቡዕ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚነሳ በብሮድካስት ባለሥልጣን ለአክሲዮን ማኅበሩ መግለጹንና ኩባንያውም በምላሹ የተብራራ መግለጫ እንደሚሰጥበት አቶ እሸቱ አስታውቀዋል፡፡

አክሲዮን ኩባንያው ከመነሻው ጀምሮ አካሄዱን ግልጽ እንዳደረገና በሚያስነግራቸው ማስታወቂያዎችም ዓላማውን በይፋ በማስታወቅ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ እሸቱ አስታውቀው፣ ተፈጠረ ስለተባለው ‹‹ብዥታ››ም በመገናኛ ብዙኃን እንደሰሙ ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑም ሆነ ብሮድካስት ባለሥልጣን ወደ ሚዲያ ከመሄድ ይልቅ፣ ኩባንያውን በማነጋገር አሁን እንደተደረገው መፍታት ይቻል እንደነበር በመግለጽ የተፈጠረው ሁኔታ ግራ እንደሚያጋባ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት 13 የስኳር ኩባንያዎችን ለመሸጥ እንቅስቃሴ መጀመሩንና ከእነዚህ ውስጥም የመጀመርያዎቹን ስድስት ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ወደ ግል ለማዛወር እየሠራ እንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ለግዥ ፍላጎት ካሳዩ በርካታ ኩባንያዎች መካከልም ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ አንዱ ነው፡፡

ከ60 ሺሕ ያላነሱ ባለአክሲዮኖችን በማካተት ወንጂ ሸዋና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት የተነሳው ኢትዮ ስኳር፣ በመንግሥት ተገቢውን የእኩል ውድድር ሜዳ ማግኘት ከቻለ ሁለቱን ፋብሪካዎች በአራት ዓመታት ውስጥ ውጤታማ ለማድረግ መነሳቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች