ገራንባ ቦትሊንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በታሸገ ውኃ ፋብሪካ ግንባታ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት መሆኑ የተነገረለትን ፋብሪካ፣ ‹‹ሳውዝ ስፕሪንግ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የታሸገ ውኃ ማምረት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ እሑድ መስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ፋብሪካውን በይፋ እንደሚያስመርቅ ገልጿል፡፡
ከ410 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ይህ ፋብሪካ በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ሲዳማ ዞን፣ ከአዲስ አበባ 345 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አርጎቤና ወረዳ ነው፡፡ የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እስካሁን በዚህን ያህል ኢንቨስትመንት የተገነባ የታሸገ ውኃ ፋብሪካ ያለመኖሩን አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የገራንባ ቦትሊንግ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ጌታነህ (የቀድሞ የኅብረት ባንክና የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት) እንዳብራሩት፣ በኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛዎች የተሻለ የታሸገ ውኃ ለማምረት ሲባል ከቦታ እስከ ማምረቻ መሣሪያው መረጣ ድረስ የተሄደበት ሒደት ከፍተኛ ወጪ እንዲጠይቅ አድርጎታል፡፡
‹‹ይኼ ወጪ ከሌሎች የውኃ ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲተያይ በጣም ከፍተኛ ነው፤›› በማለት ያከሉት አቶ ብርሃኑ፣ ለወጪው መጨመር አንድ ምክንያት ኩባንያው የተከለው የማምረቻ ማሽን በመጠጥ ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቀው ክሮንስ የተባለ የጀርመን ማሽን መገዛቱ ነው፡፡
ለማሽኑ ግዥ የወጣውን ገንዘብ ከኢንዱስትሪ አንፃር በማገናዘብ ከፍተኛ ሊባል የሚችልበትን ምክንያት ሲያስረዱም ‹‹ክሮንስ የተባለው ማሽን የተገዛበት ዋጋ በሌላ አገር የሚመረቱ ተመሳሳይ የሆኑ ማሽኖችን ብንገዛ ሁለት ሦስት ፋብሪካዎችን ሊከፍትልን ይችል ነበር፤›› ብለዋል፡፡
ፋብሪካው የገጠመው ማሽን ወጪን በተመለከተ የገራንባ ቦትሊንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ብሩክ ኃይሌ እንዳከሉት ደግሞ፣ ለማሽኑ ግዥና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ወጪዎች እስከ አራት ሚሊዮን ዩሮ ጠይቋል፡፡
እንደ ሌሎች የውኃ ማምረቻዎች የተለመደውን ማሽን ገጥሞ ከማምረት የኢንቨስትመንት ወጪውን ከፍ አድርጎ ክሮንስን ለመምረጥ ስለሻቱበት ምክንያት አቶ ብርሃኑ፣ ‹‹ዋውና ታሳቢ የተደረገው ከተፈጥሮ ማዕድን ማምረትና ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብን ታሳቢ በመደረጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኩባንያው በኢንዱስትሪው ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት የወሰነው ምርቱን ለውጭ ገበያ ጭምር ለማቅረብ በመሆኑ፣ ይህን ለማሳካት ደግሞ እንደ አንድ መሥፈርት የሚጠየቀው የማምረቻ ማሽኑ ጥራት እንደሆነ፣ ስለዚህም የግድ እንዲህ ያለው ማሽን መገዛት ስላለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ የማምረቻ ማሽኑ ከክሮንስ የተገዛበት ዋጋ ከፍተኛ ስለመሆኑ ለማመላከት፣ ኩባንያው ለማምረቻ የገዛው ማሽን ከሌላ አገር ቢገዛ ሁለት ወይም ሦስት ማምረቻዎች ለመግዛት የሚያስችል እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ምርቱን ለአውሮፓ አገሮች ለማቅረብ የታቀደ በመሆኑም፣ ከመሥፈርቶቹ አንዱ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች የጥራት ደረጃና የታሸገ ውኃ ምርቱ የሚመረትበት አካባቢ ጭምር በመሆኑ፣ ይህንን ለማሳካት ኩባንያው የወሰደው ዕርምጃ ነው ተብሏል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የክሮንስ ኩባንያ ወኪሎች ተገኝተው ስለኩባንያቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ስለፋብሪካውና የምርት ሒደት፣ እንዲሁም ፋብሪካውን ዕውን ለማድረግ ተሠሩ በተባሉት ተግባራት ዙሪያ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ መጀመርያ የምንጭ ውኃ ለመጠቀም የቻይና ባለሙያዎችና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋክልቲ ባለሙያዎች ምንጩን ለማጎልበት ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡
የፋብሪካውን ይዘት በተመለከተ በተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ በውጭና በአገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተራራው ላይ የሚገኘውን የምንጭ ውኃ የማበልፀግ ሥራ ከተከናወነ በኋላ፣ ፋብሪካውን ከምንጩ ጋር ለማገናኘት 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ ተዘርግቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የልዩ ሕንፃዎች ግንባታ፣ የማሽን ተከላ፣ የሠራተኛ ቅጥርና ሥልጠና፣ በውጭ አገር ባለሙያዎች የኮሚሽኒንግ ሥራ የሙከራ ምርት የማምረት ተግባሮች ከመከናወናቸውም በላይ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የጤናና የፋርማሲቲዩካልስ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ምርቱን ለገበያ ለማምረት የሚያስችል ማረጋገጫ ስለማግኘቱም የኩባንያው ኃላፊዎች አስረድተዋል፡፡
አሁን ሳውዝ ስፕሪንግ በተሰኘ የንግድ መለያ (ብራንድ) አራት ዓይነት መጠን ያለው የተፈጥሮ የምንጭ ውኃ አሽጎ ለገበያ ለማቅረብ ሥራ ጀምሯል፡፡ በቅርቡም ባለ 0.33 ሊትር፣ 0.6 ሊትር፣ 1.2 ሊትርና ሁለት ሊትር እሽጎች ወደ ገበያ ያሠራጫሉ ተብሏል፡፡
ኩባንያው ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል መባሉ ብቻ ሳይሆን የግንባታው ጊዜም የተራዘመ ነበር፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎች ከሰጡት ገለጻ መገንዘብ እንደተቻለው፣ ግንባታው ተጠናቅቆ ለምርት ለመብቃት እስከ ሰባት ዓመታት ፈጅቷል፡፡ አቶ ብሩክ፣ ‹‹ሥራውን ቀስ በቀስ እየሠራን ቆይተናል፡፡ የሚያስቸኩል ነገር አልነበረንም፡፡ ዋናው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የታሸገ ውኃ ለማቅረብ በመሆኑ ጊዜ መፍጀቱ በመልካም ታይቷል፤›› ብለዋል፡፡
ለፋብሪካው ግንባታ ሰባት ዓመታት የፈጀበት ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ ከውጭ ምንዛሪ ማግኘት ጋር የተያያዘ መሆኑን አቶ ብሩክ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማሽኑን ለመግዛት የጠየቅነው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ስለሆነ፣ የተጠየቀውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሁለት ዓመት ወረፋ መጠበቅ ነበረበት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ድርጅቱ ለ310 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደፈጠረም ታውቋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ፋብሪካው በሰዓት 16 ሺሕ የታሸጉ ውኃዎችን የማምረት አቅም እንዳለው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማምረት አቅሙን በእጥፍ በማሳደግ በሰዓት 32,000 የታሸጉ ውኃዎችን ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ለአገርም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች የኢንዱስትሪ ግንባታ ፕሮጅክቶችን ለማካሄድ ምኞት እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለማስወገድና ማኅበረሰቡ የሚያደርጉትን ጥረት አቅም በፈቀደ መንገድ ማገዝ እንዲቻል ኩባንያው ከእያንዳንዱ እሽግ ውኃ ሽያጭ 0.02 ሳንቲም በማጠራቀም፣ ለተጠቀሰው የማኅበረሰብ ችግር መፍቻ እንዲያውል መወሰኑም ተገልጿል፡፡
የፋብሪካው ከመሀል አገር መራቅና ኩባንያው ምርቱን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለማሠራጨት ካለው ዕቅድ አንፃር፣ እንዲሁም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የቦታው ርቀት ወጪውን ከፍ አያደርገውም ወይ ለሚለው ጥያቄም አቶ ብሩክ በሰጡት ምላሽ፣ ከከተማ ውጪ እንዲህ ባለ ቦታ የሚገኝ ውኃ በብዙ ምክንያቶች ተመራጭ በመሆኑና የምናስበውም በማዕድን የበለፀገ ውኃ ለማቅረብ ስለሆነ የቦታ ርቀቱ አሳሳቢ አይሆንም ብለዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ፋብሪካው የተገነባበት የሲዳማ ዞን አለመረጋጋት የነበረበት ስለነበር፣ በኢንቨስትመንታቸው ላይ ችግር አይፈጠረም ወይ የሚለው ይገኝበታል፡፡ አቶ ብርሃኑ በአካባቢው አለመረጋጋት በሰዎች ላይ የደረሰ አደጋ መኖሩን ገልጸው፣ ‹‹የእኛን ፋብሪካ ግን ማኅበረሰቡ ጠብቆ ያቆየው ሲሆን፣ አሁን ግን ሰላም በመሆኑ ፋብሪካውን አሁን ለማስመረቅ ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡ በሲዳማ አካባቢ የነበረው አለመረጋጋት በኩባንያው ላይም ተፅዕኖ እንዳሳደረ ተገልጿል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ፋብሪካው ምርቱን ማውጣት የነበረበት ከሦስት ወራት በፊት እንደነበር ነው፡፡ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እስካሁን ለመቆየት መገደዳቸውንም አስረድተዋል፡፡
ሳውዝ ስፕሪንግ ፋብሪካ ለምርቱ የሚጠቀምበት ውኃ ገራንባ ከተባለ ተራራ ላይ የሚገኝ ምንጭ ሲሆን፣ ይህ ተራራ 3,000 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ነው፡፡
የገረንባ ቦትሊንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ብሩክ ኃይሌ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሚባለውን ቢኤንድሲ የተባለው የአልሙኒየም ማምረቻና ማቅለጫ ባለቤት ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በታሸገ ውኃ ምርት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር ከ90 በላይ ደርሷል፡፡