የሚድሮክ ቴክኖሎጂ አባል ድርጅት የሆነው የትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረት የሆነው ሔሊኮፕተር ከወራት በፊት ባጋጠመው ችግር ወድቆ ጉዳት የደረሰበትን ቤት መልሶ ገነባ፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ቤቱን ከመገንባቱ በተጨማሪ ለባለቤቱ ቁሳቁሶች አሟልቶ አስረክቧል፡፡
ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በአደጋው ጉዳት የደረሰበትን ቤት ግንባታ ካጠናቀቀ በኋላ፣ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. የተገነቡትንና የታደሱትን ቤቶች ከእነ ሙሉ ቁሳቁሶቹ ባለቤቱ ተረክበዋል፡፡
ቤቱን ለመገንባት ከ496,568 ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ግለሰቡ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች ለመተካትም በ82,272 ብር የተገዛላቸው ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለቤቱ ግንባታና ቁሳቁሶች ማሟያ ከ578,840 ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ኩባንያው መልሶ የገነባው መኖሪያ ቤት የርክክብ ሥነ ሥርዓት ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የመስተዳድር ኃላፊዎች፣ እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
እንደ አዲስ የተሠራውን መኖሪያ ቤት ቁልፍ ለቤቱ ባለቤት ለአቶ ጥላሁን ወንድማገኘሁ ያስረከቡት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡
ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ በሔሊኮፕተሩ በደረሰበት ድንገተኛ የመውደቅ አደጋ ሳቢያ መኖሪያ ቤት በመፍረሱ፣ በቤተሰቡ ላይ ተከስቶ የነበረውን ችግር እንዲህ ባለው ሁኔታ ያስወገደ መሆኑ በዕለቱ ተገልጿል፡፡ በሔሊኮፕተሩ ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት ላጋጠሙ ተጨማሪ ወጪዎች የሚደረገው ክፍያ የኢንሹራንስ ድርጅት ለኩባንያው ከሚከፍለው ክፍያ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡
ይህ ተግባር በልዩ ፈቃድ የተደረገ በጎ አድራጎት መሆኑን፣ ቀደም ሲል ኩባንያው ኢንሹራንስ የገባ በመሆኑ በፖሊሲው መሠረት ጉዳት ለደረሰባቸው ቤቶችና ንብረቶች፣ እንዲሁም ከጥቅም ውጪ ለሆነው ሔሊኮፕተር ክፍያው በቅርብ ጊዜ በኢንሹራንስ ኩባንያው በኩል የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል፡፡
የትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ ሔሊኮፕተር በገጠመው ችግር ሳቢያ በወደቀበት ጊዜ በውስጡ በነበሩ ሁለት አብራሪዎችና አምስት ተሳፋሪዎች፣ እንዲሁም በወደቀበት ቤት ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱ ይታወሳል፡፡
በዚህ አደጋ ጉዳት ለደረሰበት አደጋ ኒያላ ኢንሹራንስ በግል ኢንሹራንስ ደረጃ ከፍተኛ የተባለውን ካሳ ይከፍላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኩባንያው በገባው ውል መሠረት ይከፍላል ተብሎ የሚጠበቀው ካሳ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆነው የትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረት የሆነ ሔሊኮፕተር ባጋጠመው ችግር ሳቢያ፣ በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የወደቀው ሚያዝያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡