Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ለሚገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች የሳዑዲ ኩባንያ ዝቅተኛ ታሪፍ አቅርቦ ተመረጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ቦርድ ካፀደቃቸው ስምንት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ለሚገነቡትና 250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጩ ለሚታሰቡት ሁለቱ ፕሮጀክቶች፣ የሳዑዲ ኩባንያ ዝቅተኛ ታሪፍ በማቅረቡ በመጀመሪያው ዙር ዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ በመሆን መመረጡን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ቦርድ ባካሄደው ድንገኛ አስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔውን እንዳሳለፈ ገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ከሚመራቸው 13 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ፣ ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቁ 17 ትልልቅ ፕሮጀክቶች በአጋርነት እንዲገነቡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 1.2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቁና ከ750 ሜጋ ዋት ያላነሰ የፀሐይ ኃይል የሚያመነጩ ስምንት ፕሮጀክቶች የተለዩ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ለጨረታ መዘጋጀታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩት፣ ‹‹ጋድ›› እና ‹‹ዲቼቶ›› በተባሉ አካባቢዎች ለሚገነቡት ሁለቱ የሶላር ፎቶቮልታይክ (ሶላር ፒቪ) ኃይል ፕሮጀክቶች የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ‹‹ኤሲደብሊውኤ ፓወር›› የተሰኘ የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያ ባስገባው ዝቅተኛ ዋጋ መመረጡን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ተሾመ ታፈሰ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኃላፊዎቹ ማብራሪያ ኩባንያው ለአንድ ኪሎ ዋት በሰዓት 2.5260 የአሜሪካ ሳንቲም ለማስከፈል ያቀረበው ሒሳብ፣ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች አኳያ ዝቅተኛው ዋጋ ሆኖ በመገኘቱ መመረጡን ገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ለጨረታው 12 ኩባንያዎች ታጭተው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ኩባንያዎች የኃይል ማመንጫዎቹ በሚገነቡባቸው ቦታዎች ጉብኝት በማድረግና ለተጫራቾች በተዘጋጀው ስብሰባ መሳተፋቸው ሲገለጽ፣ አምስት ኩባንያዎችም የጨረታ ሰነድ በማስገባት መሳተፋቸውን ሚኒስቴሩ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና የሳዑዲው ኩባንያ የቴክኒክና የፋይናንስ መሥፈርቶችን በማሟላቱ ሊመረጥ በቅቷል ተብሏል፡፡

ኩባንያው በመካከለኛው ምሥራቅ በበርካታ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ላይ የሚገኝ፣ በሳዑዲ መንግሥት (የሕዝብ ኢንቨስትመንት ፈንድ የተሰኘ መንግሥታዊ ተቋም) የ25 በመቶ የአክሲዮን ድርሻና የ15 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለባቸው የመንግሥትና የግል ኩባንያዎች የጋራ ኩባንያ ነው፡፡ አቡናያን ትሬዲንግ አብዱልቃድር አል ሙሐይዲብና ልጆቹ፣ እንዲሁም ማዳ ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኮሜርሺያል ዲቨሎፕመንት ግሩፕ በተሰኙ ኩባንያዎች አጋርነት የተመሠረተ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮም ኤሲደብሊውኤ ፓወር ፕሮጀክትስ በሚል ስያሜ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ የሚገነቡ ዓይነት ሦስት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን በግብፅ ለመገንባት የሚያስችለውን የፋይናንስ አቅርቦት በማግኘት ለግንባታ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ በሳዑዲ 300 ሜጋ ዋትና በኦማን 445 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከመዋዋሉም በተጨማሪ በሞሮኮ 120 ሜዋ ጋት የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ይሳተፋል ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች