Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማትና ኢኮኖሚው በ2011

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ ዓመት ብለን ለምንቀበለው 2012 ዓ.ም. ቦታውን የሚለቀው 2011 ዓ.ም. በርከት ያሉ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች የተስተዋሉበት ነው፡፡ ለኢኮኖሚው አመቺ መደላድል ይፈጥራሉ ተብለው በታመነባቸው ሕጎች ማሻሻያ የተደረገበት ዓመት ነው ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በአንፃሩም አገሪቱ ከፍተኛ ሊባል በሚችል የዋጋ ግሽበት የተሸበበችበት፣ አገራዊ ኢኮኖሚውን የተፈታተኑ በርካታ ክስተቶችን ያስተናገደችበት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም ቢሆን በዚህም ዓመት ቀጥሏል፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዞ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመተንበይ አስቸጋሪ መሆኑን የሚጠቅሱ አስተያየቶች የበረከቱበት ዓመት ነበር፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መጠን ከቀዳሚው ዓመታት ወርዶ የታየበት እንደሆነም ይፋ የተደገበት ዓመት ነው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ደግሞ ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በተለየ አሁንም በአትራፊነቱ ቀጥሎ የ2011 የሒሳብ ዓመት የተጠናቀቀበት ነው፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የተመለከተው ዓመታዊ ቅኝት ሌሎች ኢኮናሚያዊ ክዋኔዎችን በተወሰነ ደረጃ በማከል፣ በዓመቱ የታዩ ክስተቶችን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በ2011 የሒሳብ ዓመትም፣ ከሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዘርፉ ያሉ ሁሉም ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አትርፈዋል፡፡ ከቀደሙት ዓመታት ብልጫ ያለው ተቀማጭ ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡ ለብድር ያዋሉትም የገንዘብ መጠን ቢሆን እንዲሁ ጨምሯል፡፡

የየባንኮቹ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው፡፡ በቢሊዮን የሚያተርፉ ባንኮች ቁጥር ወደ አምስት ከፍ ያለበት ዓመት ነው፡፡ ከተቋማቱ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ሳይጨምር 17 ባንኮች ጥቅል ትርፍ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ወደ 31 ቢሊዮን ብር የተጠጋ ሆኗል፡፡ ከዚህ ትርፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ በ2011 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 17.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ 16 የግል ባንኮች ደግሞ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኙት ትርፍ ከ14.8 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ከ16 የግል ባንኮች ውስጥ ደግሞ አዋሽ ባንክ 3.3 ቢሊዮን ብር በማትረፍ የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡

የባንኮቹ የተቀማጭ ገንዘብም ከ30 በመቶ በላይ ብልጫ የታየበት ሆኖ፣ በጥቅል የባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡

በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በርከት ያሉ አዳዲስ ነገሮች የተከሰቱበት በመሆን 2011 የሒሳብ ዓመትን የሚስተካከለው የለም፡፡ በተለይ አገሪቱ ከጀመረችው ለውጥ አንፃር በፋይናንስ ዘርፍ የተጀመረው ሪፎርም የተፈለገውን ያህል እየተለመደ አይደለም የሚለው አስተያየት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህ ቀደም በአሳሪነታቸው ሲተቹ የነበሩ የፋይናንስ ሕጎች እንዲሻሻሉ መደረጉ አንዱ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው ሕግ በቀዳሚነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህ ውሳኔ የዓመታት ጩኸት ጆሮ አግኝቶ አዎንታዊ ምላሽ ያገኘ በመሆኑ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱም ሆኑ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያስደሰተ ነው፡፡

ለዓመታት አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ በባንክ ደረጃ እንዲቋቋም መፈቀዱ፣ በበጀት ዓመቱ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከተ ከፍተኛ በዘርፉ የተደረገ ለውጥ ነው፡፡ ይህንን ድንጋጌ ተከትሎም በአሁኑ ወቅት ወደ ሰባት የሚጠጉ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ለመስጠት የተደራጁ ተቋማት፣ በተለያየ ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ውስጥ አራቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት ወደ አክሲዮን ሽያጭ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በመስኮት ደረጃ እንዲጀመር ምክንያት የሆነው ዘምዘም ባንክ ነው፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት መስጠት አትችልም ተብሎ ተበትኖ የነበረ ሲሆን፣ የአገሪቱ የለውጥ አመራር ሕጉ ተሻሽሎ እንዲሠሩ በመፈቀዱ አገልግሎቱን ለመጀመር በድጋሚ ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ የጠየቀና ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገባ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመጀመርያውን ከወለድ ነፃ ባንክ በአዲሱ ዓመት መጀመረያ ላይ ለመክፈት ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡

በዚህም ረገድ ቢሆን የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የተደረገውን ጥረት ያህል፣ ከተፈቀደ በኋላ በዚህ ዘርፍ አገልግሎት ለመስጠት በርከት ያሉ ቡድኖች በተናጠል የመቅረባቸው ነገር ግን ሥጋት ሆኗል፡፡ የሥጋቱ ምክንያት በተበታተነ መንገድ ከመሥራት አንድ ሁለት ጠንካራ ወለድ አልባ ባንኮችን መፍጠር ይሻል ነበር ከሚል ነው፡፡ እንዲህ መሆኑ ያስቸግራል ቢባልም፣ ከእነሱ ዘንድ የተደመጠው ግን ምንም ችግር የሌለው መሆኑ ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም. በፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ ውስጥ ወይም አዲስ ባንክ ለማቋቋም ከመቼውም ጊዜ በተለየ አዳዲስ ክስተቶች የተስተናዱበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማቋቋም መሟላት ከሚገባቸው መሥፈርቶች መካከል፣ አንዱ የሆነውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ የሚደነግገውን መመርያ ከወጣ በኋላ ላለፉት ስምንት ዓመታት አንድም ባንክ ሳይቋቋም ቀርቷል፡፡

በ2011 ዓ.ም. ግን ለስምንት ዓመታት በዝምታ የተሸበበው ቋጠሮ ተፈትቶ፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ስምንት የሚጠጉ ባንኮችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዘምዘም ወለድ አልባ ባንክ አንዱ ሲሆን፣ አማራና ገዳ ባንክም አክሲዮን በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡

ባለፉት ስምንት ዓመታት አዲስ ባንክ ለማቋቋም ያልተቻለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት 500 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ለመሸጥ አስቸጋሪ ይሆናል በሚል ነው፡፡ ዘንድሮ ባንክ ለመመሥረት አክሲዮን እንዲሸጡ ፈቃድ ያገኙት ባንኮች (በምሥረታ ላይ) ግን ሁሉም ይህንን 500 ሚሊዮን ብር አክሲዮኖች አጠናቀው በ2012 ዓ.ም. ሥራ እንጀምራለን ማለታቸውም የተለየ ክስተት ነው፡፡ ይህም አዲሱ ዓመት አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀሉበት እንደሆነ ጠቋሚ ሆኗል፡፡

ቀደም ብለው የተቋቋሙ የግል ባንኮች በቀደመው የባንክ ማቋቋሚያ መመርያ ይጠየቅ የነበረውን የተከፈለ የ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል አሟልተው ሥራ ለማስጀመር ከወሰደባቸው ጊዜ አንፃር፣ በ2011 ዓ.ም. ባንክ ለማቋቋም አክሲዮን በመሸጥ ላይ ያሉት ባንኮች በወራት ልዩነት 500 ሚሊዮን ብሩን ሞልተን ወደ ሥራ እንገባለን ማለታቸው የተለየ የሚያደርገው ነው፡፡ ከዚሁ አዳዲስ ባንኮች መፈጠር ጅማሬ ሳይወጣ ለዓመቱ ብቻ ሳይሆን፣ ባለፉት 40 ዓመታት በግል ደረጃ ያልተሞከረ ስፔሻላይዝድ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩም የ2011 ዓ.ም. በፋይናንስ ዘርፉ አዲስ ክስተት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህም የአገሪቱ በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች መሠረታዊ ችግር እየሆነ ላለው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፋይናንስ ለማቅረብ የሚሠራ ባንክ አክሲዮን ሽያጭ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ ‹‹ጎህ የቤቶች ባንክ›› ስፔሻላይዝድ ባንክ ሆኖ መቅረቡ ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ ገጽታው በዚህ ባንክ በዋና አደራጅነት ከተጠቀሱት አሥር ግለሰቦች አምስቱ በተለያዩ ባንኮች በፕሬዚዳንትነት የመሩ መሆናቸው ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ለሴቶች ብቻ አገልግሎት ለመስጠት በተለይ ቅርንጫፎቹን በመክፈት ተጠቃሽ የሆነበት ዓመት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አቢሲኒያ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎች መክፈታቸውም አዲስ ነገር ነው፡፡ እንደ ባንኮች ሁሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም በበጀት ዓመት 9.1 ቢሊዮን ብር አረቦን በመሰብሰብ ከቀደመው ዓመት ብልጫ ያለው አፈጻጸም ማሳየታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የአገሪቱ ትልቁ የኢንሹራንስ ኩባንያ ግን ዓመታዊ ትርፉ ከቀደመው ጊዜ ያነሰ የሆነበት ዓመት ሆኗል፡፡ በዚህ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች 11 ሲሆኑ፣ በዚህ ረገድ ንግድ ባንክ ራሱን የቻለ ቅርንጫፍ በመክፈት ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ብሔራዊ ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር ለባንኮች ማከፋፈሉም አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አመራሮቹ በራሳቸው ፈቃድ ሥራ የለቀቁት በ2011 ዓ.ም. ነው፡፡ በተለይ አራቱ ከፍተኛ አመራሮች በምክትል ፕሬዚዳንትነት የኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አመራሮች አንዳንዶቹ ወደ ግል ባንክ በመሄድ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እየሠሩ ነው፡፡

በተመሳሳይ ከግል ባንኮች ለንብ ኢንተርናሽናል ባንክና ለደቡብ ግሎባል ባንክ አዳዲስ ፕሬዚዳንቶች የተሰየሙበት ዓመት ነው፡፡ የባንኮች ማኅበርን ሲመሩ የቆዩት አቶ አዲሱ ሃባ ከኃላፊነት ከለቀቁ በኋላ መጨረሻ ላይ እሳቸውን ተክተው አቶ አቤ ሳኖ የባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ዘግይቷል ተብሎ ትችት እየቀረበ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ቦታ በመባል የሚታወቀው የምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት ቦታ እስካሁን ያልተሾመበት የመሆኑ ጉዳይ አነጋጋሪ እስከ መሆን ደርሷል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጠናቀቂያ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ቢኖረውም፣ ይህ ዕቅድ ምን አስገኘ ምን አሳጣ የሚለውን ለማመላከት ያልተቻለበት ዓመት ነው፡፡ አገር እንደ ዋዛ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እንድታጣ አድርጓል በሚል ጣት የሚቀሰርበት ሜቴክ፣ አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያመላክተው መረጃም በዓመቱ አስደማሚ ተብለው ሊጠቀሱ የሚችል የብድር ስረዛ ጥያቄ ያቀረበበት ነው፡፡

ሜቴክ እስካሁን አስከተለ የተባለው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብክነት እንዳለ ሆኖ፣ ድርጅቱን ለማስቀጠል ከታሰበ መንግሥት ዕዳውን እንዲሰረዝለት ተጠይቋል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ሜቴክን የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው የሥራ ኃላፊ በግልጽ ይፋ እንዳደረጉት፣ የሜቴክ ዕዳ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ እንዲያውም ከዚህ ውስጥ የተወሰነው እንዲሰረዝለት መንግሥትን ጠይቋል፡፡

ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲነገር አገሪቱ ያለባት ዕዳ በዋናነት ይነሳል፡፡ ለዓመታት በተዛባና በተስፋፋ ሥሌት ከልክ በላይ የተበደረችው ብድር ህልውናዋን እስከ መፈታተን ደርሷል፡፡ የለውጡ መሪዎች ኃላፊነት ሲቀበሉ ደግሞ ዕዳ የሚከፈልበት ወቅት ሆነና እየተለመነም ቢሆን የማይቀረውን ዕዳ በመክፈል እየተጓዙ ነው፡፡ አንዳንዱንም የአገሪቱን ዕዳ ከአበዳሪዎች ጋር በመደራደር እንዲራዘም በማድረግ፣ እንደ አገር የከበደ ችግር እንዳይፈጠር ተደርጓል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅርቡ ይፋ የተደረገው መረጃ ኢትዮጵያ 1.5 ትሪሊዮን ብር ዕዳ የተሸከመች አገር ስለመሆኗ በግልጽ የተሰማበት ዓመት ነው፡፡ የዕዳ ነገር ከተነሳ መንግሥት በዚህ ዓመት ወደ 9.4 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ መዋሉ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብርታት የአንዳንድ ብድሮች የመክፈያ ጊዜ ባይራዘምና በልመና በተገኘ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን በተወሰነ ደረጃ መሸፈን ባይቻል ኖሮ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የበለጠ ችግር ውስጥ ይገባ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ይህንኑ የሚያረጋግጥ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

የመንገድ ልማትና ተስፋ

ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ በ2011 ማጠቃለያ ላይ መልካም ነገር የተሰማበት ነው፡፡ በቀዳሚው ዓመት ለአንድም አዲስ የመንገድ ፕሮጀክት በጀት አልተያዘም ነበር፡፡ በቀዳሚው በጀት ዓመት ለአዲስ መንገድ ግንባታ የተያዘ በጀት ባለመኖሩ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት ግን እንደ አዲስ የሚጀመሩ 91 ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ተሰምቷል፡፡ እነዚህ መንገዶች እስከ ማጠናቀቂያ ጊዜያቸው ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

የሕግ ማሻሻያዎች

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደፊት ለማራመድ ያግዛሉ የተባሉ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆኑ የተሻለ አገር ለመፍጠር የተባሉ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ማሻሻያዎች ደግሞ በገለልተኛ የሕግ ባለሙያዎች እንዲዘጋጁ ዕድል መሰጠቱ በታሪካዊነቱ እንዲወሳ ያደርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር ብቻ ከሃያ በላይ መመርያዎችን ያሻሻሉና አዳዲስ ሕግጋትን ወደ ሥራ ያስገቡ መሆኑ ለአብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ማሻሻያዎቹ በመልካም የሚታዩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በ‹‹ዱዊንግ ቢዝነስ›› ያላትን ደረጃ ለማሻሻል ይረዳት ዘንድም፣ የተስተካከሉ ሕግጋት የወጡት በዚሁ ዓመት ነው፡፡ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን የተቀላቀለችበት ዓመትም ይኸው ነው፡፡

ነጥብ በመጣል የዘለቀው የወጪ ንግድ

እንደ ቀደሙት ጥቂት ዓመታት ሁሉ ለበጀት ዓመቱ የተያዘለትን ዕቅድ ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሰውኑ ከቀደሙት ዓመታት ያነሰ አፈጻጸም እያስመዘገበ የቀጠለው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ፣ ዘንድሮም ነጥብ በመጣል በጀት ዓመቱን አጠናቋል፡፡ ቁልቁል እየወረደ ያለው የወጪ ንግድ የ2011 አፈጻጸሙ ሲታይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛ የተባለውን ገቢ ያስተናገደበት ሆኗል፡፡

በ2011 የነገሠው የዋጋ ግሽበት

በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ግሽበት የታየበት ዓመት ቢኖር 2011 ዓ.ም. እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ትክክለኛ መረጃዎችም ይህንኑ ያሳያሉ፡፡ በዓመቱ በየወሩ የሚታየው የዋጋ ግሽበት አሳሳቢ እየሆነ ስለመሄዱ በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ፣ ይኸው የኑሮ ውድነት እያስከተለ ያለው የዋጋ ዕድገት ማቆሚያው የት ነው? የሚል እሳቤ ያላቸው ጥያቄዎች መሆናቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያመላክታሉ፡፡ እስከ ሰኔ ድረስ የነበረው የዋጋ ግሽበት ከ15 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ይህ ታይቶ የማይታወቅ ነው የተባለ ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም. ውጤታማ ሥራ ስለማስመዝገባቸው ሊጠቀሱ ከሚችሉት ተቋማት መካከል አንዱ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው የገቢዎች ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህ ተቋም አገራዊ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል በሚባልበት፣ እንዲሁም ግብር የመክፈል ባህሉ ገና በሆነበት አገር በ2011 በጀት ዓመት ከ220 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል፡፡ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ ግብር የመክፈል ባህል እንዲዳብር አገራዊ ንቅናቄ በመፍጠርም፣ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው የተደረገበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ገንዘብ ሚኒስቴር ከታክስና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ከ20 ያላነሱ ነባር መመርያዎችና ሰርኩላሮች የተሻሻሉበት፣ አዳዲስ መመርያዎችም ወጥተው ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረገበት ዓመት ነው፡፡

የ2010 በተለይም 2011 የበጀት ዓመት በተለየ የሚታዩበት ሌላው ጉዳይ ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድን የተመለከቱ ተደጋጋሚ ዜናዎች የተሰሙባቸው ዓመታት ናቸው፡፡ በ2011 ዓ.ም. ይህ ጎልቶ የወጣበት ሲሆን፣ ከጉምሩክ ባለሥልጣንና ከገቢዎች ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች በ2011 ዓ.ም. ብቻ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ የወጡና ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ ግምታቸው ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ከሚገኙ ድርጊቶች አንዱ ኮንትሮባንድ መሆኑ ታምኖ፣ ይህንን ሕገወጥ ተግባር በአገር አቀፍ ደረጃ በተዋቀረ ግብረ ኃይል ለመከላከል ቃል የተገባውና ወደ ሥራ የተገባው በ2011 በጀት ዓመት ነው፡፡ በቅርቡም ይህንን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል በመከረ አንድ መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአጭር ቃል፣ ‹‹የአገር ነቀርሳ›› ብለው መግለጻቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት አመላክቷል፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከትንንሽ ዕቃዎች ጀምሮ በርካታ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘዋል፡፡ ካናቢስ ከተባለው ዕፅ ጀምሮ በዲፕሎማቲክ ስም ሊገባ የነበረ ዕቃ ወደ አገር ሊገባ ሲል ተይዟል፡፡

ኮንትሮባንደ ለዋጋ ግሽበት የሚኖረውን ተፅዕኖ በመረዳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ኮሚቴ እስከማቋቋም ደርሰዋል፡፡ አሁንም ይህ የዋጋ ግሽበት እንዳልረገበ የሚታይ ሲሆን፣ መንግሥት በበኩሉ ይህንን ለማርገብ እወስዳለሁ ያላቸውን ዕርምጃዎች ግን እየታዩ አይደሉም፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ንግድ ሚኒስቴር አሁን ለሚታየው የዋጋ ውድነት በአመዛኙ ከነጋዴው ጋር ያያያዘው ሲሆን፣ ሕገወጥ ደላሎችና የኮንትሮባንድ ንግድም የችግሩ ምንጭ ናቸው ብሏል፡፡ ገበያ በማረጋጋት በመንግሥትን ወክለው እንዲሠሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ ቀዳሚ የሆነው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዓመቱ መጨረሻ ላይ ችግሩ በአመዛኙ የነጋዴዎች፣ የደላሎችና የሕገወጥ ግለሰቦች ስለመሆኑ ገልጿል፡፡ የችግሩ መንስዔ ናቸው የተባሉ አካላት ላይ ወሰድኩት ያለው ዕርምጃ ውጤቱ ባይጠቀስም፣ እንደ ተለመደው በዓመቱ ማጠቃለያ ላይ ‹‹ሕገወጦች ላይ ዕርምጃ እንወስዳለን›› የሚለውን መፈክሩን ግን ዘንድሮም አልዘነጋም፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሽያጭ

ከመንግሥት ሪፎርም ጋር ተያይዞ ለግል ባለሀብቶች ክፍት ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ኢትዮ ቴሌኮም ቀዳሚ ነው፡፡ ከዚህ ተቋም ድርሻ ለመግዛት ታዋቂ የሚባሉ ኩባንያዎች ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ የድርሻ ሽያጩን ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ተሰብስበውለት አልቋል፡፡

አወዛጋቢ ከሚባሉ ጉዳዮችም መካከል የከባድ ተሽከርካሪዎች ከቀን እንቅስቃሴ መታገድ ይወሳል፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያዎችን ይሰበሰብ የነበረው ‹‹ለሁሉ›› የአገልግሎት ክፍያዎቹ ወደ ሌሎች ተቋማት እንዲዛወሩ የተደረገበት ዓመት ነው፡፡ በተለይ ውኃ፣ መብራትና መሰል ክፍያዎች ወደ ንግድ ባንክ እንዲዛወሩ ስምምነት የተደረገው ዘንድሮ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የባንኩን የውስጥ ሲስተም እየፈተነው ስለመሆኑ እየተገለጸ ሲሆን፣ ሲስተሙን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ስድስት ወራት ይፈጅብኛል ብሏል፡፡

የኤፈርት ኩባንያዎች

የኤፈርት ኩባንያዎችን ለመሸጥ ውሳኔ ስለመተላለፉ የሚገልጸው መረጃ ሌላ አነጋገሪ ጉዳይ ነበር፡፡ ከኤፈርት ኩባንያዎች መካከል ሦስት የሚሆኑትን ለመሸጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በትግራይ ክልላዊ መስተዳድር ሥር እንዲሆኑ የተወሰነውም ዘንድሮ ነው፡፡ ጥረትም በተመሳሳይ ኩባንያዎች በአማራ ክልላዊ መንግሥት እንዲተዳደሩ አድርጓል፡፡

ማኅበራዊ ኃላፊነትና ቢዝነስ

 የተጠናቀቀው 2011 በተለየ የሚታይበት ከዚህ ቀደም በተለመደ ሁኔታ፣ በተለይ የቢዝነስ ተቋማትና ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በቀረበላቸው ጥያቄና በፍላጎት እጃቸውን የዘረጉበት ዓመት በመሆን ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እንዲህ ባለው ተግባር ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ባንኮችና ሌሎች የግል ኩባንያዎች አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

‹‹ትብብር ካለ እንዲህም ይደረጋል›› የሚባለው እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ሌላው ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት በጎ ተግባር በአዲስ አበባ ከተማ ታይቷል፡፡ ይህም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ባደረጉት ጥሪ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት መገልገያና ዩኒፎርም ለማልበስ የተለያዩ ኩባንያዎች ያደረጉት ድጋፍ ነው፡፡ ከአስተዳደሩ የተገለጸው በተፈለገው መጠን ደብተሮችና እስኪርቢቶዎች መገኘታቸውንና ዩኒፎርም ለማልበስ እንደሚቻል መረጋገጡ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች