በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡት 11 ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በመስኮት ከሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው የቁጠባ የገንዘብ መጠን ከ21.9 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡
ባንኩ ይህንን ያስተዋወቀው ቅዳሜ ጳቅሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ከመስኮት አገልግሎት ውጪ የመጀመርያውን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠውን ራሱን የቻለ ቅርንጫፍ በከፈተበት ወቅት ነው፡፡ በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል በሚባለው አካባቢ ለአገልግሎት የበቃውን ቢላል የሚል ስያሜ የተሰጠውን ቅርንጫፍ ምርቃት አስመልክቶ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና፣ ‹‹እስካሁን ባንኩ ከ1,398 በላይ በሚሆኑ የባንኩ ቅርንጫፎች ከወለድ ነፃ የባንክ አልግሎት እየሰጠ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በእነዚህ ቅርንጫፎች እስካሁን ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አገልግሎቱን ማግኘታቸውን፣ በእነዚህ ደንበኞች አማካይነት ከ21.9 ቢሊዮን ብር በላይ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት በቁጠባ ማሰባሰብ መቻሉን አመልክተዋል፡፡ አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ ደንበኞች የሸርዓ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የፋይናንሰ አቅርቦትን በሙራበሃና ለኤክስፖርተሮች ልዩ የቅድመ ብድር በስፋት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ የተመረቀው ቢላል ልዩ ቅርንጫፍ ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ተደራጅቷል፡፡ ቅርንጫፉ እስላማዊ መርህን የተከተለ የተቀማጭ ገንዘብ፣ የፋይናንስ የኢንቨስትመንትና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ አሟልቶ የሚሰጥ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ቅርንጫፉ አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ ደንበኞች የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው፣ እንዲሁም ተቀማጭ ገንዘባቸው ከመደበኛው የባንክ አሠራር ወይም ሒሳብ ጋር ሳይቀላቀል የሚከናወን ነው፡፡ የራሱ የሆነ ቴክኖሎጂ የሚጠቀምና የተለየ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ኖሮት አገልግሎቱን የሚሰጥ እንደሆነም፣ ከፕሬዚዳንቱ ገለጸ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ባንኩ እንደ ቢላል በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ብቻ የሚሰጡ ሌሎች ቅርንጫፎችን በመክፈት፣ አገልግሎቱን በስፋት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጋር የተያዙ ሌሎች ሥራዎችን እየሠራ ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰውም በቅርቡ ለሃጂና ኡምራ መንፈሳዊ ጉዞ የሚያገለግል ለቤይክ የተሰኘ የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ነው፡፡ የዚህ አገልግሎት መጀመር ጉዟቸውን ወደ መካና መዲና የሚያደርጉ የእምነቱ ተከታዮች፣ ለጉዞ የሚያስፈልጓቸውን ወጪዎች በረዥም ጊዜ ቁጠባ ማጠራቀም እንዲችሉ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች አገልግሎቱን በስፋት መጠቀም እንደጀመሩም አቶ ባጫ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ አገልግሎቱን ለደንበኞቻችን መስጠት መጀመሩ ወለድ መቀበልና መክፈል ለማይፈልጉ የኅብረተብ ክፍሎች የፋይናንስ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እያገዛቸው መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አገልግሎቱን ከዚህም በላይ የተሟላ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
አዲሱ ቢላል ቅርንጫፍ መከፈት አስመልክተው አቶ ባጫ ባደረጉት ገለጻ፣ በመደበኛውና አሁን ባለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ጥርጣሬ ኖሯቸው ከባንክ ርቀው ያሉ ወገኖችን በተሻለ ለማስተናገድም ያስችላል ብለዋል፡፡
ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በዚህ ዘርፍ በመስኮት ደረጃ የሚሠሩ ባንኮች እየተበራከቱ ሲሆን፣ በቅርቡም ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የሆነ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችን ለመመሥረት እየተዘጋጁ ያሉ ባንኮች የአክሲዮን ሽያጭ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡት 11 ባንኮች በዚህ ዘርፍ ያሰባሰቡት ገንዘብ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ እስካሁን በዚህ አገልግሎት ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑ ታውቋል፡፡