Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየእንቁጣጣሽ ገበያ ድባብ

የእንቁጣጣሽ ገበያ ድባብ

ቀን:

እንቁጣጣሽ ወይም ዘመን መለወጫ በዓል ከሌሎች መንፈሳዊና ሕዝባዊ በዓላት በሕዝቡ ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ ሕፃናት ልጃገረዶች ‹‹አበባዬ ሆይ!›› እያሉ የሚጨፍሩበት፣ የመልካም ምኞት መግለጫ የሚሆነው የአበባ ሥዕል የሚበረክትበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የበጉ፣ የዶሮውና የቂቤው ወዘተ ጋጋታ ሲታከልበት ደግሞ ለበዓሉ የበለጠ ድምቀት ይሰጠዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የዚህንም ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ለመቀበልና አቅሙ የሚፈቀድለትን ለመሸመት ወደተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል፡፡ እኛም የተወሰኑ ሥፍራዎችንም ለመቃኘት ሞክረናል፡፡

ከጎበኘናቸውም የገበያ ሥፍራዎች መካከል በአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል ተብሎ የሚነገርለት መርካቶ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ከሰው ነፍስ በስተቀር የማይሸጥበት ነገር የለም›› በሚባልበት መርካቶ መጀመርያ ጎራ ያልነው ዶሮ ተራ ነው፡፡ እዛም እንደደረስን በግምት የ70 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አንዲት ባልቴት ‹‹አበስኩ ገበርኩ!›› ሲሉ ሰማናቸው፡፡ ምነው እማማ ምን አጋጠመዎት? አልናቸው፡፡ ወርሃዊ የጡረታ አበሌ አንድ ዶሮ እንኳን መግዛት ተሳነው፤›› አሉን፡፡ በቀኝ እጃቸው ጉንጫቸውን እያሻሹ፡፡

እኛም መቃኘታችንን ቀጠልንና አንድ የወንድ ዶሮ ትልቁ 550 ብር፣ መካከለኛ 450 ብር፣ ዝቅተኛ 300 ብር ዋጋ ሲጠራባቸው አስተዋልን፡፡ ዘወርወር ብለን ብንጠይቅም ዋጋቸው በአብዛኛው ተቀራራቢ ነው፡፡ ውድ ነው! ውድ ነው! እያልን ስናጉረመርም የሰሙ አንድ የዶሮ ነጋዴ›› እኛ ምን እናድርግ ከገጠር የገዛነው በውድ ዋጋ ነው፡፡ በዛ ላይ የትራንስፖርት ወጪ ሲታከልበት ደግሞ ወጪያችንን ከፍ ያደርገዋል፡፡ እዚህ ከመጡ በኋላ የሚሞቱብንና ከሽያጭ የሚተርፉም አሉን፡፡ ይኼ ሁሉ ለኪሳራ ይዳርገናል፡፡ የምናተረፈው ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤›› ብለው አማረሩብን፡፡

- Advertisement -

በተዘዋወርንባቸው የገበያ ሥፍራዎች ሁሉ አንድ እንቁላል አምስት ብር ከ50 ሳንቲምና አንድ ኪሎ ሽንኩርት 35 ብር ሲጠራ ሰምተናል፡፡ መሳለሚያ፣ ሾላ፣ አዲሱ ገበያ አካባቢ ትልቁ ሙክት በግ 6000 ብር፣ መካከለኛ 5000 ብርና 4500 ብር፣ አነስተኛ 3000 ብር፣ እንዲሁም ሸጎሌ በሚገኘው የእንስሳት ገበያ ማዕከል ድልብ በሬ 50,000 ብር፣ መካከለኛ 40,000 ብርና 30,000 ብር ዝቅተኛ 20,000 ብር ተጠርቶበታል፡፡ ከተዘረዘሩት ዋጋ በታች የሚጠሩ ሰንጋዎች ነዶ የላቸውም፡፡ ይኼም ሆኖ ዋጋቸው ተመጣጣኝና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያማከለ ሆኖ አላገኘነውም፡፡

ሰንጋ ወይም በሬ የሚገዛ ሸማች አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር እኛ ቅኝት ባደረግንበት ጳጉሜን 4 እና 5 ቀን 2011 ዓ.ም. እምብዛም አላየንም፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማወቅ አለፍ፣ አለፍ ብለን አንዳንድ ነጋዴዎችን ጠይቀን፣ ይህ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ለእንቁጣጣሽ የበሬ ሽያጭ እምብዛም እንደሆነ፣ ኅብረተሰቡ ምርጫ በግና ዶሮ ላይ እንደሆነ፣ ለመስቀል በዓል ግን ከዚህ በተቃራኒ ኅብረተሰቡ ሰንጋ ላይ እንደሚያተኩር ሰምተናል፡፡

በጥራጥሬ ተራም ባቄላ በኪሎ 40 ብር፣ ስንዴና ሽንብራ በኪሎ እያንዳንዳቸው 30 ብር፣ የቡና ስኒ በምታክል ጣሳ ኑግ፣ ፌጦና ጠመዥ በነፍስ ወከፍ 15 ብር ሲሆን፣ ከዚህ በታች የለም፡፡ ቂቤ ተራንም አካለናል፡፡ አንድ ኪሎ ለጋ ቂቤ 350 ብር ብለውናል፡፡ ከዋጋው ንረት በላይ ደግሞ የጥራቱ ጉዳይ አጠያያቂ  ነው፡፡

በሥፍራው ካየናቸው ሸማቾች መካከል ወይዘሮ በለጡ አበበ የተባሉ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ‹‹ባለፈው ሳምንት ከአንዲት ነጋዴ የገዛሁት ሁለት ኪሎ ቂቤ ሳነጥረው ቆሻሻው አየተምዘገዘገ ወጣ፡፡ የቀለጠውም ቂቤ አልረጋ ብሎ ውኃ ሆኖ ቀረ፡፡ ሲቀመስም ምንም ጣዕም የለውም፡፡ አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለመግዛት ቆሚያለሁ፤›› ብለው አጫውተውናል፡፡

‹‹ግርግር ለሌባ ይመቸዋል›› እንደሚባለው ሁሉ በወከባው ሳቢያ ከባዕድ ጋር የተቀላቀለ ቂቤም ሆነ ማር በአጠቃላይ ምግብ ነክ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም የነበረ ልምድ አስተምሮናል ያሉንም አሉ፡፡ የጥራት ቁጥጥር እንደሌለ ቢገነዘቡም አማራጭ በማጣት ምክንያት ከሸመታው ወደኋላ እንዳላሉና ንፁህ ይሆናል ብለው የሚያምኑትን ከደንበኞቻቸው እንደሚገዙ አንዳንድ ሸማቾች ነግረውናል፡፡

አቶ ኑርቢና አህመድ አሁንም ወናፎ ይዘው በ22 አካባቢ ቢለዋና መጥረቢያ እየሞረዱ አዲስ ዓመት የሚያስገኝላቸውን ትሩፋት እያሰቡ ይሠራሉ፡፡

በቀን በትንሹ እስከ ሃያ ቢላዋ ይሞርዳሉ፡፡ ገበያ አለ ከተባለ 30 እና ከዚያ በላይ ቢለዋና መጥረቢያ እየሞረዱ ይውላሉ፡፡ ከአዲስ ዓመት በበለጠ የፋሲካ በዓል ላይ የአስሞራጅ መጠኑ ከፍ ይላል የሚለው አቶ ኑርቢና ይናገራሉ፡፡

አቶ ኑርቢና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ቦሌ ቡልቡላ ለአዲስ ዓመት የተሻለ ገቢ ያስገኝልኛል ያሉትን አካባቢ መርጠው ይሠራሉ፡፡

በአካባቢያቸው የሚሠሩትን የሰልባጅ ንግድ ወደ ጎን ብለው፣ ‹‹አዲስ ዓመት የሙስሊም፣ የክርስቲያን የሁሉም በዓል በመሆኑ ወደ ሞራጅነት አዘንብያለው፤›› ይላሉ፡፡

የአቶ ኑርቢና ቢለዋ መሞረጃ እንደ ዘመን አመጣሹ ባለመሆኑ አብዛኞቹ እንደሚመርጡትና ተፈላጊ እንደሆነ፣ ከዚያም በላይ ግን በወናፎ እያራገቡ ቢላዋና መጥረቢያ አግለው ስለቱ እንዲጎላ የሚያደርጉበት ሙያ በአዲስ አበባና አካባቢዋ እየጠፋ መሆኑ የሚያገኙትን ገቢ ጥሩ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ፡፡

ቢላዋቸውን ሲያስሞርዱ ያገኘናቸው አቶ ጌታሁን ተረፈ እንደተናገሩት፣ በዓመት ሦስት ጊዜ ቢላዋ ያስሞርዳሉ፡፡

‹‹ዘመናዊ የሚባለው የቢላዋ ዓይነት ምርጫዬ አይደለም›› የሚሉት አቶ ጌታሁን፣ በአገሬው ሰው የሚመረተው ቢላዋ ብዙ ጊዜ ሳይዶሎድም የመቆየት፣ ለማስሞረድም አመቺ በመሆኑ እንደሚጠቀሙት ይናገራሉ፡፡

እንደ አገሬው ባህልና ወግ ለቅዱስ ዮሐንስ (ዓዲስ ዓመት) አዲስ ቢላዋ መግዛት፣ በአዲስ ዓመት ቤት ቀለም መቀባት፣ አካባቢን ማፅዳት፣ አዲስ ልብስ መግዛትን ጨምሮ ማስሞረድ የበዓሉ ነፀብራቅ ነው ይላሉ፡፡

 እርሳቸው በሚኖሩበት ቦሌ ሃያት አካባቢ ከዚህ ቀደም በግ ገዝተው በዓሉን እንደሚያሳልፉ አስታውሰው፣ የበግ ዋጋ ስለናረ የአካባቢ ሰው በጋራ በመሆን በሬ ገዝተው ቅርጫ  ለመካፈል አስበዋል፡፡

የገንዘቡ መጠን እንደ በሬው መስባትና እንደየጊዜው፣ እንደ ዓመት በዓሉ ይለያል ብለዋል፡፡ ለምሳሌነት ያነሱት በገና በዓል የዕርድ ሥርዓቱ ስለሚበዛ የገንዘቡም መጠን ከፍ ያለ መሆኑን ነው፡፡

አቶ ዳንኤል ገልሜሳ በሳሪስ በግ ተራ አካባቢ የበግ ነጋዴ ሲሆኑ፣ ጎን ለጎን የዕርድ ሥራን ያከናውናሉ፡፡ ‹‹በባዕላት ሰሞን አንድ በግ 250 ብር እበልታለው›› የሚሉት አቶ ዳንኤል በዘወትር ጊዜ ከእዚያ ባነሰ ገንዘብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰው የመግዛት አቅም አነስተኛ ስለሆነ በግ በመበለት የሚያገኙት ገቢ እያነሰ መሆኑን ያክላሉ፡፡

በሳሪስ በግ ተራ የበግ ዋጋ ከሁለት ሺሕ እስኪ አምስት ሺሕ ድረስ እየተገበያዩ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

ካለፈው ዓመት የዋጋ ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱን፣ ገዢም ብዙም አለመኖሩን፣  ለአዲስ ዓመት የተማሪዎች ደብተር፣ ዩኒፎርም (የደንብ ልብስ) እና ሌሎችም ወጪ ስለሚኖር ሰው የዕርድ ሥርዓቱ ላይ የመቀዝቀዝ ሁኔታ እንደሚያሳይ፣ ከበዓላት ወቅት በበለጠ የአዘቦት ቀናት ላይ የተሻለ ገበያ እንደሚኖር በበዓል ወቅት አንዳንዱ ተበድሮ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

አቶ ከበደ በየነ በሳሪስ ሀዲድ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ለአዲስ ዓመት ከዚያው ከአካባቢያቸው በሁለት ሺሕ አምስት መቶ ብር በግ ገዝተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በግ የሚገዙት ከክልል ከተሞች በመሆኑ በተሻለ ዋጋ እንደሚሸምቱ ገልጸው፣ አሁን ያለው ዋጋው ቢጨምርም ‹‹ይሁን ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል ብለዋል፡፡

ሳሪስ አዲድ ተራ ላይ በግና ፍየል በመሸጥ አሥር ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ አሳምነው ወንደሰን እንዳሉት ከሆነ በዘንድሮ ዘመን መለወጫ ላይ ከኑሮ መወደድ ጋር ተያይዞ የከብቶች ዋጋ እየጨመረ እንደመጣ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው በዓል ላይ 214 በጎችን ለመሸጥ የያዙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ላልተፈለገ ኪሳራ እንደዳረጋቸውና ይህን ከግምት በመክተት በአሁን ዘመን መለወጫ ላይ 111 በጎችን እንዲያዙ አስረድተዋል፡፡

አንድ አነስተኛ በግ 2‚200 ሺሕ ብር እንደሆነና ትልቁ በግም 5‚500 ሺሕ ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም የጅማ በግ እንደሆነ ለማስታወስ ችለዋል፡፡ የፍየል ዋጋም –ከበግ ጋር ሲነፃፀር ትልቅ ልዩነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

አንድ ፍየል 3‚500 ሺሕ ብር እስከ 7‚000 ሺሕ ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል ከአዲስ ዓመት ጋር ተያይዞም አብዛኛኞቹ ወላጆች ብዙ ወጪ ስለሚኖርባቸው ይህን ነገር ለመድፈር እንደማይችሉ አክለዋል፡፡

አቶ ከበደ በየነ እንዳሉት አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የፍየልና የበግ ዋጋ እየጨመረ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከክልል ከተሞች ላይ በመሄድ ከብቶችን እንደሚገዙና ከዋጋ አንፃርም ከአዲስ አበባ ጋር ትልቅ ልዩነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ከኑሮ መወደድ ጋር ተያይዞም ላላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ መስቀለ ግዛው የኤርፎራ ሴት ዶሮዎችን በየዓመቱ ለበዓላት የሚሸጡ ሲሆን፣ አንድ ኤርፎራ ዶሮ ከ200 እስከ 250 ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ከአምናው ዘመን መለወጫ ጋር አኳያ ብዙም ልዩነት እንደሌለው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ከትርፍ ጋር ተያይዞም ብዙም አጥጋቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የአበሻና የፈረንጅ ዕንቁላሎችን እንደሚሸጡ አክለዋል፡፡ አንድ የሐበሻ ዕንቁላል አምስት ብር የፈረንጅ ከሆነ ደግሞ አራት ብር እንሚሸጥ ለማስታወስ ችለዋል፡፡ ሱቆች ላይም  እንደየ አካባቢው የእንቁላል ዋጋ እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡

የሐበሻ ወንድ ዶሮ ከ300 እስከ 450 ብር እንደሆነና የፈረንጅ ወንድ ዶሮ ከ250 እስከ 500 ብር እንደሚሸጥ አቶ ባይሳ ደሙ ተናግረዋል፡፡ አትክልት ተራ አካባቢ ነጭ ሽንኩርት አንድ ኪሎ ከ150 እስከ 160 ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቀይ ሽንኩርት እንደየ አካባቢው የሚለያይ ሲሆን ፒያሳ አትክልት ተራ ላይ  አንድ ኪሎ ከ17 ብር እስከ 20 ብር እንደሚሸጥ ሪፖርተር ማወቅ ችሏል፡፡

በሳሪስ አካባቢም አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ23 እስከ 26 ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎችም ላልተፈለገ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በሳሪስ አካባቢ አንድ ኪሎ ለጋ የምግብ ቂቤ ከ300 እስከ 350 ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የበሰለ ቂቤ ከ280 እስከ 300 እንደሆነ ተነግሯል፡፡

አንድ ችቦም ከአምስት ብር እስከ ሰባት ብር ከአምሳ ሳንቲም ድረስ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ቄጤማ ከአሥር ብር እስከ 20 ብር ድረስ እንደሚሸጥ ተገልጿል፡፡ የባህል አልባሳቶችም ሆኑ የቤት ዕቃዎች በየዓመቱ ዘመን መለወጫን ተገን በማድረግ መወደዳቸውን ለማየት ተችሏል፡፡

(ሔለን ተስፋዬ እና ተመስገን ተጋፋው ለዚህ ጽሑፍ አስተዋጽኦ አድርገዋል)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ