Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከስንዴ ሸመታ መቼ ይሆን የምንገላገለው?

ከቀናት በኋላ አሮጌ የምንለውን 2011 ዓ.ም. ተሰናብተን አዲሱን ዓመት ልንቀበል ነው፡፡ እያጠናቀቅን ያለነው 2011 ዓ.ም. ለሸማቾች የተመቸ ዓመት አልነበረም፡፡ ገበያው ይጎረብጥ ነበር፡፡ ከቀደሙት ጊዜያት የከፋ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የተስተዋለበት ዓመት ነው፡፡

የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ አኃዛዊ መረጃዎች እየመሰከሩ ያሉትም ከፍተኛ የዋጋ ዕድገት የታየበት ዓመት ስለመሆኑ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በባለ ሁለት አኃዝ ላይ ሆኖ ለረዥም ጊዜ የዘለቀበት ዓመት ቢኖር ዘንድሮ ነው፡፡ ከፍ ያለውን ግብይት ዋጋ ዝቅ ለማድረግ ይኼ ነው የሚባል ጥረት ተደርጓል ለማለትም ይቸግራል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ መንስዔዎች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዋናነት ሊቀመጥ የሚችለው ምንም ዓይነት እጥረት በሌለበት ሁኔታ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡ በአጭሩ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው ጭማሪ ከፍ ያለውን ቦታ ይይዛል፡፡ ስለሌሎች ግድ የሌላቸው ነጋዴዎች የሚፈጽሙት ያልተገባ ተግባር መባባሱ አንዱ ምክንያት ቢሆንም፣ መንግሥትም የችግሩን ጥልቅት ተገንዝቦ ለዕርምጃ መዘግየቱ ገበያውን መንታፊ ጩሉሌዎች እንዳሻቸው እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የግብይት ሒደቱ በገበያ ዋጋ እየተመራ አይደለም፡፡ ጨዋነት አይታይበትም፡፡ ደላሎች ጉልበት ያፈረጠሙበት ነው፡፡  

እንዲህ ካሉት እውነታዎች ባሻገር ለዋጋ ግሽበቱ መንስዔ ናቸው የተባሉትን ሌሎች ጉዳዮች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ግን የዋጋ ንረቱን በተመለከቱ አስተያየቶችን በተደጋጋሚ ስንጠቅስ አንስተናቸዋልና ማሰልቸት እንዳይሆን ብለን እንለፋቸው፡፡ ለማንኛውም ዘንድሮ የታየው የዋጋ ግሽበት ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ስለመምጣቱ አሁንም አስረግጠን መግለጽ ግድ ይላል፡፡

የ2011 ዓ.ም. የገበያና የሸመታ ጉዳይ ከተነሳ እንደ ሸማችም ሆነ እንደ ዜጋ ቁጭት ካሳደሩብኝ የዓመቱ አንኳር ወሬዎች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ ለስንዴ ሸመታ አወጣች የተባለው የገንዘብ መጠን ነው፡፡

ለምለሚቱ የምንላት አገራችን ዘንድሮ ብቻ ለስንዴ ግዥ ከአሥራ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ አውጥታለች፡፡ ልብ በሉ አሥራ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ ከውጭ አገር ስንዴ ተገዝቷል፡፡ አሁንም ልብ መባል ያለበት ነገር ኢትዮጵያ የገቢ ንግድ ወይም ከውጭ ከምታስገባው ምርቶች ሁሉ ስንዴ ያላግባብ የውጭ ምንዛሪ የሚፈስበት ምርት እየሆነ ስለመምጣቱ ማሳያ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አያያዝ አገሪቱ ከነዳጅ ግዥ ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታፈስባቸው ምርቶች አንዱ ስንዴ የማይሆንበት ምንም ምክንያት ላይኖር ነው ማለት ነው፤ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያን በሚያህል ለስንዴና ለሌሎች የምግብ ሰብሎች የተመቸ መሬት ላላት ሥራ ፈላጊዎች በተበራከቱበት አገር የስንዴ ሸመታዋ መጠን እየጨመረ መምጣቱ አንገት ያስደፋል፡፡ ለዘመናት በእርሻ የምትታወቅ አገር መሬቷን ፆም እያሳደረች በዶላር ስንዴ ትገዛለች መባሉን እየሰማን መቆየታችንም ልንወቀስበት ይገባል፡፡ እንዴት? ለምን? አይባልም፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በሌለ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ለስንዴ እየተባለ የሚገዛው ስንዴ ወደ ገበያ የሚያሠራጩትን ያህል ገበያው ያለመረጋጋቱ ነገር ያስደምማል፡፡ በአገራችን በየትኛውም የገበያ ሥራ ብትሄዱ የስንዴ ዋጋ ሰማይ ነክቷል፡፡ ስንዴዋ ተፈጭታ ዱቄት ሆና ስትሸጥ ደግሞ አጀብ የሚያሰኝ ዋጋ ይወጣላታል፡፡ ከዚያ በኋላ በፈለገው ዋጋ ቢሠላ ከአንድ ብር መብለጥ የሌለበት ዳቦ ሁለትና ሦስት ብር ይሸጣል፡፡ እሱም ከተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ጉዳይ ላይ የሸፍጥ ጨዋታ የተቀላቀለበትም በመሆኑ የስንዴ ጉዳይ ብዙ ሊያነጋግር የሚችል አጀንዳ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡

ስለዚህ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ትሆናለች የተባለችው አገር ስንዴ ከውጭ ገዝታ በአገር ውስጥም ያመረተችውን አክላ ለገበያ ብታቀርብም፣ የሸማቹን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ ያለመቅረቡ ነገር በዚህ አገር ገበያ ጉዳይ የበለጠ እንድንገረም ያደርገናል፡፡

በቂ ይሆናል የተባለ ስንዴ ከቀረበ ዋጋው ለምን አልተረጋጋም? በ11 ቢሊዮን ብር የተገዛ ስንዴ ገበያ ለማረጋጋት አቅም ያጣው ለምንድነው? እንዲያው በተራ ሥሌት በዚህን ያህል የተገዛ ስንዴ በነፍስ ወከፍ ቢደርሰን ጥጋብ ያልሆነበት ምክንያት ዛሬም ሊፈታ አለመቻሉ ለምን?

ከሰሞኑ እንደሰማነው መንግሥት በድጎማ የሚያቀርበውን ስንዴ ኩንታሉን በ550 ብር ገዝተው ዱቄቱን ለዳቦ ቤቶች ማቅረብ የነበረባቸው የዱቄት ፋብሪካዎች፣ ኩንታሉን ስንዴውን ከተገዛበት ሦስትና አራት እጥፍ ሲሸጡ ተገኙ መባሉ ደግሞ ችግሩ የገበያ ሥርዓታችን ቁንጥጫ የሚያስፈልገው መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የገበያ ሥርዓቱን ማስጠበቅ ያለመቻል ችግር ነው፡፡

ለማንኛውም ኢትዮጵያ የስንዴ ገበያ የስንዴ ምርትና የዳቦ መሸጫ ዋጋ ጉዳይ ሰይጣናዊ ምትሃት ያለው እየመሰለኝ ነው፡፡ ነገር ግን ከስንዴ እስከ ዳቦ ድረስ ያለው አጠቃላይ የግብይት ሁኔታ አገርን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ የሚነግረን ሲሆን፣ ለስንዴ ምርት የተመቸው መሬታችንም በድርጊታችን የሚታዘበን ይሆናል፡፡

እንዲያው ነገሩን በደንብ ካጤንነው ለስንዴ ወጣ የተባለው አሥራ አንድ ቢሊዮን ብር ተይዞ ከንፈር ተነክሶ በሰፊው ስንዴ ለማምረት ቢሞከር ኖሮ የት ሊደርስ ይችል እንደነበር ሲታሰብ ደግሞ፣ ሁኔታዎችን አገናዝቦ የተሻለውን የማምረት ችግር ስለመኖሩ ሊያሳይ ይችላል፡፡ ባለን ሀብት በአግባቡ ያለመጠቀምና ሁሌም ሳይለፉ በሚገኝ ቢዝነስ ላይ ያተኮርን መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ዛሬ ቢዝነሱ ሁሉ የዕለት የምትገኘዋ ላይ ሆኖ ረዥም አሳቢና አገር ወዳድ ባለሀብቶች አጣን እንጂ በስንዴ ምርት አይደለም አገርን አፍሪካን ለመታደግ በቻልን ነበር፡፡ ግብርና የኢትዮጵያ መሠረት መሆኑን አምኖ በዚህ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ መጠየፍ በራሱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሁሉም ፎቅ ገንቢ ሁሉም አስመጪና ላኪ ሆኖ አገር የትም አትደርስም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በዚሁ በቶሎ በሚተረፍበት ቢዝነስ ላይ የሙጥኝ ማለት ላኪውም የሚልከው ላይኖረው፣ አስመጪውም ዕቃ ለማምጣት የሚፈልገው ዶላር ጠፍቶ እኩል ማጨብጨብ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ አገርን ለማስቀጠልና ለመጪው ትውልድም ከታሰበ የግብርና ኢንቨስትመንት ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ልጆችንም ችግኝ መትከል ምን እንደሆነ ያስጨበጥነው ግንዛቤ በግብርና ላይ ኢንቨስት የሚያደርግ ትውልድ እንዲኖረን ከተፈለገ ማሳየት ያለብን ዛሬ ነው፡፡

 በእርግጥ ከውጭ የሚገባ ስንዴን በሦስት ዓመት ውስጥ ለማስቀረት ስለመወሰኑ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን የሰማን ቢሆንም፣ እየሆነ ያለው ያስቆጫል፡፡ ቢያንስ ስንዴ ዘርተን የዳቦን ዋጋ ማውረድ የዚህ ትውልድ ድርሻ ይሁን፡፡ ኢንቨስተሮቻችን ሀብታቸው በረከት የሚኖው እንዲህ ያለውን ሥራ በመሥራት ነውና 2012 ዓ.ም. ቢሊዮን ብሮች ለስንዴ መግዣ ዋለ የሚለውን ዜና የማንሰማበት፣ ቢያንስ ስለመቀነሱ የምናዳምጥበት ይሁን፡፡ ዋጋ ተወደደ የማንልበት አዲስ ዓመት ይሁን፡፡

ይህ እንደሆነ ደግሞ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያሻል፡፡ በስንዴና መሰል ምርቶች ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች እንዲበረታቱ ማድረግም ግድ ይላል፡፡ ዕውቅና በመስጠትም እንደ በጎ ሰው ያሉ የሽልማት ድርጅቶች የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ላበረከቱት ለውጥ፣ ዜጎች ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ድርጅቱ አሁን የጀመረውን መልካም ነገር እንዲህ ባለው ዘርፍ ላይም ቢያደርግ አበርክቶው ከፍ ይላል፡፡ ሌሎች ማበረታቻዎችን በማሰብ ከስንዴ ሸመታ ለመዳን በብርቱ መሠራት አለበት፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት