በዋና ዋና ከተሞቿ እያስፋፋች የመጣችው የሕክምና ቱሪዝም ከአሥር ዓመታት ወዲህ በጀመረችው እንቅስቃሴ ሳቢያ ከፍተኛ ዕድገት ያሳየችበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቱርክ በጣት የሚቆጠሩና በአገሪቱ ከሌሉ የሕክምና መሣሪያዎች በቀር፣ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ያሟሉ የግልና የመንግሥት የሕክምና ተቋማት በብዛት ይገኙባታል፡፡
በሕክምና ቱሪዝም መስክ የኢኮኖሚዋን 5.4 በመቶ እንደመደበች የሚነገርላት ቱርክ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በርካታ የውጭ ዜጎች በተለይም ምዕራባውያን ለድንቃድንቅ ከተሞቿና ቅርሶቿም ብቻ ሳይሆን፣ ሕክምና ፍለጋ የሚጎበኟት ለመሆን በቅታች፡፡ በመሆኑም በርካታ የቱርክ ሕክምና ተቋማት ይህንኑ ለማሳየት፣ ብሎም በህንድና በታይላንድ የተያዘውን የሕክምና ቱሪዝም ለመጋራትና መዳረሻ ለመሆን እየሠሩ ነው፡፡ ከእነዚህ መሰል ተቋማት አንዱ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ተጎብኝቶ ነበር፡፡
በቱርክ ከሚገኙ ትላልቅ የሕክምና ተቋማት መካከል አንዱ በሆነውና ስሙ በቱርክ ጎልቶ በሚጠቀሰው የአጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ ሲሆን፣ በተቋሙ የበርካታ አገሮች ዜጎች ያገለግላሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ በትውልድ ኢትዮጵዊው ዶ/ር አራርሳ ከዲር ናቸው፡፡ በሙያቸው የሰመመን ሕክምና ስፔሺያሊስት ወይም የአንስቴሺያ ስፔሺሊስት ናቸው፡፡ በመስኩ ማገልገል ከጀመሩም ከአምስት ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ በውጤታቸው ከፍተኛነት ነፃ የትምህርት ዕድል በማግኘት ከ19 ዓመታት በፊት ወደ ቱርክ ያቀኑት ዶ/ር አራርሳ፣ ቱርክ ቤትም ትዳርም ሆናቸዋለች፡፡
በአርሲ ዞን ዴራ ከተማ ተወልደው ያደጉት ዶ/ር አራርሳ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዳማ ከተማ አጠናቀው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ግቢ ጀማሪ ተማሪ በነበሩበት ነበር በውጤታቸው ተመርጠው የነፃ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙና ወደ ቱርክ እንዲያቀኑ መንገዱ የተጠረገላቸው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሰባት አመልካቾች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርጠው እ.ኤ.አ. በ2000 ወደ ቱርክ በማቅናት በዚያው ሕይወታቸው የተቃኘው ዶ/ር አራርሳ፣ ትምህርታቸውን በሚማሩበት ወቅት እግረ መንገዳቸውን የትዳር አጋራቸውንም ተጣምረዋል፡፡ አብራቸው ከምትማር ቱርካዊት የጀመሩት አፍላ የወጣትነት ፍቅራቸው፣ ለትዳር በቅቶ ለሁለት የሆድ ፍሬዎች አድርሷቸዋል፡፡ ባለቤታቸውም እንደ እሳቸው የሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡
የሕክምና ትምህርታቸውን ምርጫው እንደሆነ በገለጹልን የሰመመን ሕክምና ዘርፍ ሠልጥነው እንደወጡም፣ በገቡት ግዴታ መሠረት ወደ ቱርክ ገጠራማ አካባቢዎች ተመድበው ሠርተዋል፡፡ በቱርክና በሶሪያ ድንበር ጠረፍ አካባቢ ለሁለት ዓመት ያገለገሉት ዶ/ር አራርሳ የጽኑ ሕሙማንና የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም እሳቸውን ጨምሮ ስምንት በሰመመን ሕክምና ስፔሻላይዝ ያደረጉ ሐኪሞች እንዲሁም ከፍ ከፍ ያሉና በፕሮፌሰር ደረጃ ልምድና ዕውቀቱ ያላቸው ነባር ሐኪሞችም በሰመመን ሕክምና መስክ አብረዋቸው በአጂባደም ሆስፒታል ይሠራሉ፡፡ በጠቅላላው ከ23 ሺሕ በላይ ሠራተኞች በአጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ ሥር በሚንቀሳቀሱ 21 ሆስፒታሎችና 16 የጤና ክብካቤ ማዕከላት ውስጥ ይሠራሉ፡፡ ዶ/ር አራርሳም ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በሚያስንቀው አቱኒዛዴ ሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከሕይወታቸውም ከሙያቸውም እያዋዙ ያወጉን ወጣቱ የሕክምና ሰው፣ ስለአገራቸው ፀጋና ሀብትም ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ ወደ አገር ቤት መጥተው እንደነበር በሚገልጹበት ወቅት፣ እግረ መንገዳቸውን በጨዋታ መሀል ስለፍራፍሬ ሲወሳ አንድ የሚገርማቸውን ጉዳይ ጣል አደረጉ፡፡ ይኸውም በቱርክ አቮካዶ ውድ በመሆኑ አንዱ ፍሬ አንድ ዶላር ወይም እስከ ስድስት የቱርክ ሊሬ ወይም እስከ 30 ብር የሚሸጥ በመሆኑ ለዝቅተኛውም ለሀብታሙም ቱርካዊ የቅንጦት ምግብ ሆኗል አሉን፡፡
ሌላም ጉዳይ አወጉን፡፡ የቤተሰብ ናፍቆት፡፡ በቱርክ የመጀመርያዎቹ ጥቂት ጊዜያት ቆይታቸው ወቅት ሆድ ይብሳቸው እንደነበር እንዲህ ገለጹልን፡፡ ‹‹ለአንድ ዓመት ምግቡን ለመልመድ ተቸግሬያለሁ፡፡ ለሁለት ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ብዬ አልቅሻለሁ፤›› ይሁንና የቱርኮች እንግዳ አልማጅነትና ተቀባይነት፣ በተለይም ለጥቁሮች ቀና በመሆናቸው፣ በቶሎ መላመዳቸውን ዶ/ር አራርሳ አስታውሰው ነገሩን፡፡
እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች እያዋዙ በሚገልጹት ቁም ነገር መካከል ኢትዮጵያም እንደ ቱርክ የሜዲካል ቱሪዝምን እንዴት ማስፋፋት እንደሚጠበቅባት አብራሩልን፡፡ እርግጥ ነው በየጊዜው ስለሜዲካል ቱሪዝም ጉዳይ በመንግሥትም፣ በግል ባለሀብቶችም፣ ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲነሳ ሲቦካ ቢቆይም አንድም የረባ ውጤት ሳይታይ በዲስኩር ዓመታት አልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሕክምና ባለሙያው ተስፋቸው ሩቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ ብቻም ሳይሆን፣ ካላት የአየር ፀባይና ሁኔታ አኳያ ለኑሮ ተስማሚ የአየር ሁኔታ በመታደሏ ጭምር ለውጭም ለአገር ውስጥም ታካሚዎች ምቹ የሚያደርጓት በርካታ መሠረታዊ ሀብቶች አሏት፡፡ ይህ ማለት ግን የሜዲካል ቱሪዝምን ማስፋፋት ትችላለች ማለት እንዳልሆነ የሚያውቁት ዶ/ር አራርሳ፣ የሠለጠኑ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ለሕክምና አሰጣጥ የሚያግዙ መሠረታዊ ግብዓቶች በተለይም ዘመኑ የሚጠይቃቸው ቁሳቁሶችና አቅርቦቶች ብሎም ተቋማት መሟላት አለባቸው፡፡
በቱርክ እንደሚታየው ከሆነ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የሚያስንቁ ሆስፒታሎች በብዛት የሜዲካል ቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡባቸው ተቋማትን ገንብተዋል፡፡ ለአብነትም በኢስታንቡል ጋዜጠኞች የጎበኟቸው አልቱኒዛዴና ማስላክ የተሰኙት የአጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ የሚያስተዳድራቸው ሆስፒታሎች፣ ከመደበኞቹ የሕሙማን ክፍሎች ባሻገር፣ ‹‹ኪንግ ስዊት››፣ ‹‹ቪአይፒ ስዊት›› የተባሉትን ጨምሮ፣ ሌሎችም ውድ ክፍሎች ለሕሙማን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ሕሙማንን ሊጠይቁ የሚመጡ ዘመድ አዝማዶች፣ የሚያርፉባቸው መኝታ ክፍሎች፣ መታጠቢያ፣ እንግዳ ማረፊያ፣ ማብሰያና መመገቢያ ክፍሎች ሁሉ ያሏቸው ናቸው፡፡ ይህ ዋናው ጉዳይ ባይሆንም፣ ለታካሚው ግን ጊዜያዊ ዕፎይታና ሰላም በመስጠት መንፈሱን ያረጋጋሉ ተብለው ይታሰባሉ፡፡ የተጎበኙት ሆስፒታሎች ከ200 እስከ 250 አልጋዎች ያሏቸው፣ ምናቸውም ግን ሆስፒታል የማይመስሉ ናቸው፡፡
ሁሉም ዓይነት የውስጥ ደዌም ሆነ ሌሎች በሕክምናው መስክ ውስብስብ የሚባሉ የጤና ዕክሎች የሚታከሙባቸው የአጂባደም ሆስፒታሎች፣ ከልብ ንቅለ ተከላ በቀር ሁሉንም ዓይነት ሕክምናዎች እንደሚሰጡ የተቋሙ የልዩ ልዩ ሕክምና ክፍል ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሕፃናት ካንሰር ሕክምናን ጨምሮ የኩላሊትና የጉበት ንቅለ ተከላ፣ የጭንቅላት እጢና ካንሰር፣ የመተንፈሻ አካላት ካንሰር፣ የኅብለ ሰረሰር ችግር፣ የጡት፣ የማኅፀንና የሌሎች ካንሰር በሽታዎችን የሚያክሙባቸው በርካታ ማሽነሪዎች ከተሟላ የሕክምና ቡድን ጋር አደራጅተው ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡
እንዲህ ያሉ አስፈላጊ ግብዓቶች፣ ባለሙያዎች፣ ተቋማት እስካልተሟሉ ድረስ የሜዲካል ቱሪዝምን ማሰቡ ዘበት ቢመስልም፣ ዶ/ር አራርሳ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሳካና ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ያምናሉ፡፡ በሰበብ አስባቡ ለሕክምና ወደ ውጭ መመላለሱ፣ የአገርን አንጡራ ሀብት ማራቆቱና መንከራተቱ እንዲበቃ ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡ ቀስ በቀስ ተጀምሮ የግድ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎታቸው በባለሙዎች፣ በሕክምና ቁሳቁስና መሰል ችግሮች የማይችሉ ካልሆኑ በቀር፣ ለሕክምና ወደ ውጭ መሄድ መቅረት እንዳለት የሚያሳስቡት ዶ/ር አራርሳ፣ በሕክምናው መስክ እንደሌሎች ሙያዎች ሁሉ በብዛት የሠለጠኑ ብቃትና ችሎታቸው ያላቸው ስመ ጥር ሐኪሞች ስላሏት እነሱን መጠቀም ይገባታል ይላሉ፡፡
‹‹የግልና የመንግሥት ጥምረት ታክሎበት ወደ ውጭ እየሄዱ መታከም መቅረት አለበት፡፡ ከሃያ እና ከአሥር ዓመታት በፊት የቱርክ ባለሥልጣናት ወደ ውጭ እየሄዱ ይታከሙ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምናው ሊሰጥ ካልቻለና ፋሲሊቲ ከሌለ፣ ሐኪሙና ዕውቀቱ ከሌለ ግን እየወጡ መታከሙ አይቀሬ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ በቱርክ መንግሥት ከተከለከሉ እንደ ልብ ንቅለ ተከላ ያሉና እንደ ፕሮቶን ሕክምና መስጫ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በማጣት ሳቢያ ሊያክማቸው የማይችላቸውን ካልሆነ በቀር አብዛኞቹን ሕክምናዎች በራሱ እንደሚሰጥ የየሕክምና ክፍሉ ኃላፊ ፕሮፌሰሮች አብራርተዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል በማስላክ ሆስፒታል የኒውሮሎጂ ሕክምና ክፍል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ኢልሃን ኤልማኪ ትኩረት የሚስብ ገለጻ አደርገው ነበር፡፡ ይኸውም ልጃቸው ለሁለለኛ ደረጃ ትምህርቱ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ባቀናበት ወቅት ባያቸው ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ገጽታዎች መደሰቱን፣ እሳቸውንና የተቀረውን የቤሰተብ አባላትም ኢትዮጵያን መጎብኘት እንደሚገባቸው የሚያነሳሱ ፎቶዎችን እንደላከላቸው ሲያብራሩ፣ ልጃቸው በኢትዮጵያ ቆይታው ወቅት የተነሳቸውን ፎቶግራፎች በማሳየት ነበር፡፡ በሱፍ አበባ በተጌጠ ማሳ ውስጥ፣ በጥንታውያኑ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ የተነሳቸውን ፎቶግራፎች እያሳዩ ‹‹እኔም መሄዴ አይቀርም›› አሉን፡፡ ይህን እንደ መግቢያ አስቀድመው፣ በኒውሮሎጂ ሕክምና መስክ ከጭንቅላት እስከ ኅብለ ሰረሰር ባለው ክፍል ስለሚካሄዱ ውስብስብ ሕክምናዎች አወጉን፡፡ ያከሟቸውን ሕሙማን ቅድመ ሕክምናና ድረ ሕክምና ገጽታዎች በማሳየትም በሥራቸው ምን ያህል እንደሚደሰቱ አጫወቱን፡፡ በአብዛኛው በጭንቅላት እጢ፣ በወገብ አጥንት መጣመምና መሰበር፣ በአንገት መቆልመምና በሌሎችም ችግሮች የሚሰቃዩ የአገር ውስጥና የውጭ ታካሚዎች በዶ/ር ኤልማኪና አጋሮቻቸው ክትትል ያገኛሉ፡፡
ከኢትዮጵያ በየወሩ ስድስት ሕሙማን መታከም በጀመሩበት የአጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ፣ የአንዲት ወጣት ኢትዮጵያዊት ጉዳይም ለየት ያለ የሕክምና ክትትል የጠየቀ ክስተት መሆኑ ተነገረን፡፡ ወጣት ዮሀና በላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪ ስትሆን፣ ‹‹ኩሺንግ ሲንድሮም›› የተባለ የሆርሞን ችግር ነበረባት፡፡
ይህ በሽታ ሁሉ ነገሩ ሊታወቅ ባለመቻሉ ወደ ቱርክ በመሄድ በአጂባደም ሆስፒታል አማካይነት እንደታወቀና የሕክምና ክትትሏም ውጤት እንዳስገኘ ገለጻና ማብራሪያ ከተሰጠባቸው መካከል ይጠቀሳል፡፡ የተበዛባው የሆርሞን ዕድገት ለከፍተኛ የሰውነት ውፍረት የዳረጋት ወጣት ዮሀና፣ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ሕክምና በማግኘቷ ለውጥ ማሳየቷ ተገልጿል፡፡ ሐኪሟና የኢንዶክሪኖሎጂ ሕክምና ዘርፍ ሜዲካል ዳይሬክተር፣ ፕሮፌሰር ኤንደር አሪካን እንደሚሉት፣ የሀና በሽታ መንስዔ ካርቱዞል የተሰኘው ሆርሞን፣ በጭንቀት ወቅት ከልክ በላይ ሲመረት በሕክምናው አጠራር ኩሺንግ ሲንድሮም የሚባለው እንደሆነ ከፍተኛ የሆድ አካባቢ ውፍረት፣ የእጆች መቅጠን፣ ብሎም ከፍተኛ የደም ግፊትና ሌሎችም በርካታ ሕመሞችን የሚያስከትል ውስብስብ በሽታ ነው፡፡
እንደ ዶ/ር አራርሳ ምክር እንዲህ ያሉ በአገር ውስጥ ሕክምና ተመርምረውም ሊደርስባቸው ያልቻሉ ካልሆኑ በቀር ወደ ውጭ ሄዶ መታከሙ ለኢትዮጵያም ጉዳት ነው ይላሉ፡፡ ወጣት ዮሀና ሰባት ጊዜ ተመርምራ የሕመሟ መንስዔ በአገር ውስጥ ሊታወቅ ስላልቻለ በውጭ አገር ለመታከም ሪፈር እንደተጻፈላት ገልጻለች፡፡ በመሆኑም እንደ ዮሀና በቀላሉ የማይታወቅ ሕመም ያለባቸውን ጨምሮ፣ ከፍተኛ ዝናና ሥልጣን ያላቸውም ሚስጥራቸው ተጠብቆ የሚታከሙባቸው የአጂባደም ሆስፒታሎች ባለፈው ዓመት ብቻ ከ800 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ አስገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ዓይነቱን አገልግሎት በማስፋፋት የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ዶ/ር አራርሳ ይመኛሉ፡፡