በሥራ ላይ ያሉትን 18 ባንኮች በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርን በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚዳንት የሚያገለግሉ አዳዲስ አመራሮች ተሰየሙ፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ዓርብ ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ምርጫ፣ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል፡፡ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን መመረጣቸው ታውቋል፡፡
አቶ አቤ ሳኖ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው እስከተመረጡበት ድረስ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ማኅበሩን ለሁለት የምርጫ ዘመን ሲያገለግሉ የቆዩት የቀድሞ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሀባ ከባንኩና ከማኅበሩ በመልቀቃቸው ምክንያት በተካሄደው ምርጫ፣ አዲስ የተመረጡት አመራሮች ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል፡፡
የባንኮች ማኅበር ከተመሠረተበት ጊዜ ወዲህ አቶ አቤ አራተኛው ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የመጀመርያው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የቀድሞ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ለይኩን ብርሃኑ ነበሩ፡፡ እሳቸውን ተክተው ደግሞ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ደግሞ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት አቶ አዲሱ ሀባ ናቸው፡፡