ዳሸን ባንክ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚታዩ የባንክ ቅርንጫፎች በተለየ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ያደራጀውንና በሼክ መሐመድ አል አሙዲ ስም የሰየመውን ልዩ ቅርንጫፍ በማስመረቅ ለአገልግሎት አበቃ፡፡
ባንኩ ከብሔራዊ ባንክ ፊት ለፊት በሚገኘው የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የከፈተውን ይህንን ልዩ ቅርንጫፍ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) መርቀው የከፈቱ ሲሆን፣ በቅርንጫፉ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት ጎብኝተዋል፡፡ ልዩ ቅርንጫፉ ከተለመዱት መደበኛ ቅርንጫፎች በተለየ ዲዛይን የተደራጀ ነው፡፡ የተለያዩ ተቋማት፣ የቢዝነስ ዘርፎችና ግለሰቦች የሚስተናገዱበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቅርንጫፉ ደንበኛ ተኮር ሆኖ የተዋቀረ መሆኑንና እያንዳንዱ ደንበኛ አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ቅርንጫፉ ሲቀርብ፣ ለብቻው የሚስተናገድበት ዕድል እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለዕድሜ ባለፀጎች፣ ለውጭ ኢንቨስተሮች፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሚፈልጉ፣ ለኮርፖሬት ደንበኞች፣ ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና ሌሎችም አገልግሎቶች ዴስኮች በማዘጋጀት ያስተናግዳል፡፡
ከምርቃቱ ጎን ለጎን ባንኩ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ 718,000 ብር፣ እንዲሁም ለእናት ወግ በጎ አድራጎት ድርጅት 296,000 ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው ዳሸን ባንክ በአሁኑ ወቅት 415 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሠራጭተው በሚገኙ በአሥር የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ከ360 በላይ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም)፣ ከ870 በላይ ፖስ ማሽኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
እንዲሁም በ70 አገሮች፣ በ169 ከተሞች፣ በ464 ዓለም አቀፍ ባንኮች ትስስር ፈጥሮ በመሥራት ላይ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ሦስት ባንኮች አንዱ ነው፡፡ በተጠናቀቀው በሒሳብ ዓመትም ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.3 ቢሊዮን ብር ያተረፈ መሆኑን፣ የባንኩን ዓመታዊ ክንውን የሚያመለክተው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት ያመለክታል፡፡